Site icon ETHIO12.COM

አማራ ክልል – ሃሰተኛ መረጃ የታከለበትና የተቆራረጠ ሰነድ በማራባት ክልሉን ለማተራመስ እየተሰራ መሆኑንን አስታወቀ

ከሐዋሳ የውይይት መድረክ የተገኘ ሰነድ ነው” ተብሎ እየተዘዋወረ ያለው ሰነድ በተለይም በአማራ ክልል ውይይት እየተካሄደበት ካለው ሰነድ የተለየ ከመሆኑም በላይ፤ አሁን እየተዘዋወረ ያለው ሰነድ የአማራ ሕዝብ በዚህ ጦርነት የከፈለውን ዋጋና የነበረውን አስተዋጽኦ የሚያሳየውን ክፍል ሆን ብሎ ቆርጦ በማስቀረትና ከአውዱና ከይዘቱ ውጪ ‹ኤዲት› በማድረግ እየተሰራጨ ያለ ሰነድ መሆኑን አረጋጠናል፡፡

መነሻና መዳረሻችን የሕዝባችን ክብርና ጥቅም ማስከበር ነው!❞ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ❝መነሻና መዳረሻችን የሕዝባችን ክብርና ጥቅም ማስከበር ነው❞ ሲል ጽሕፈት ቤቱ በወቅታዊ ጉዳይ ያወጣው መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል:-

ሳንወድ ተገድደን ከአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ጋር የገባንበት ጦርነት ሁሉን አቀፍ ጦርነት ነው፡፡ ጦርቱ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ ወዘተ… ቀውሶችን ማዕከል ነው፡፡ በዚህ ጦርነት በጠላት ጀርባ ታዝለው የገቡ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችና አጋሮቻቸው እጃቸው ረዝሞ ታይቷል፡፡ በዚህም ይህ ጦርነት ከትህነግ አሸባሪ ቡድን ጋር ብቻ እየተደረገ ያለ አለመሆኑም ታውቆ ያደረ ሀቅ ነው፡፡

በኅልውና ጦርነት ትህነግ ሳተላይት አሸባሪዎችን ጥቅም ላይ አውሏል፡፡ እነዚህ የጥፋት አጋር የሆኑት ተላላኪዎቹ ማለትም አሸባሪው ኦነግ ሸኔ፣ የጉሙዝ ታጣቂ፣ የቅማንት ታጣቂ፣ የአገው ሸንጎ ወዘተ… ታጣቂዎች ጋር የጥፋት ሕብረት ፈጥሮ ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ስለመውጋቱ በተደጋጋሚ የተገለጸ እውነታ ነው፡፡ ከዚህ አለፍ ሲልም፤ ከግብፅና ሱዳን ጋር በግልፅ እንዲሁም ከአሜሪካ እና ምዕራባውያን ሀገራት በግልፅና በስውር እየተደረገ ያለ ጦርነት ስለመሆኑ አይደለም እኛ ኢትዮጵያዊያን መላው ዓለምም ቢሆን ግንዛቤ የወሰደበት ሀቅ ነው፡፡

አሸባሪው የትግራይ ወራሪ የከፈተብን ጦርነት የፈጠረው አደጋ በመላ ኢትዮጵያውያን ላይ ስለመሆኑ አንዳች አጠያያቂ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ይሄን አውዳሚ ጦርነት በመመከት ዙሪያ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በጋራ የተረባረቡበትና ከሞላ ጎደል በሀገራችን ላይ ተደቅኖ የነበረውን የኅልውና አደጋ በጋራ ታግለው ለመቀልበስ የቻሉት፡፡ ስለሆነም የተገኘው ድል የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ የተረጋገጠበት፣ በሂደቱም ሕብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ያጠናከርንበት፣ በሁሉም ዘርፍ በጋራ ከቆምን የማንወጣው ችግር እንደማይኖር ያስመሰከርንበት፣ በተለይም በዚህ ጦርነት ዳያስፖራው ከመቼውም ጊዜ በተለየ ለሀገሩ ያለውን ቀናዒነት ያረጋገጥንበት ሆኖ ታይቷል፡፡

ይሁን እንጂ በዚህ ጦርነት ኢትዮጵያዊ አንድነት፤ ታሪክ የማይዘነጋው ድልና ሕዝባዊ ተሳትፎ የተንጸባረቀበት ቢሆንም፤ እንደማንኛውም ተግባር በሂደቱ የተስተዋሉ ውስንነቶች ነበሩ፡፡ በመሆኑም መላ ኢትዮጵያዊያን ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ስለተጎናፀፉት ድልና በሂደቱም ስለተስተዋሉ ድክመቶች፤ እንዲሁም ስለቀጣዩ የትግል ምዕራፍ ዙሪያ መምከርና የጋራ አቋም መያዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በዚህም መሰረት ከአመራሩ ጀምሮ ወደ ሕዝቡ የሚደርስ የውይይት መድረኮች በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡ በወሳኝነት ውይይቶቹ ከከፍተኛው አመራር እስከታችኛው አመራር ድረስ የደረሱና የተጠናቀቁ ሲሆን፤ በቀጣይም በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ መላ ሕዝቡ የሚወርድ ይሆናል፡፡

ለዚህ ውይይት የሚሆን ሰነድ በማዕከል ደረጃ ተዘጋጅቶ የወረደ ሲሆን፤ ክልሎች ደግሞ የቀረበላቸውን ሰነድ መነሻ አድርገው ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ተነስተው የራሳቸውን ክልላዊ የማወያያ ሰነድ አዘጋጅተው ወደ ውይይት ገብተዋል፡፡ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤትም በዚሁ አግባብ ከማዕከል የወረደውን መነሻ የውይይት ጽሑፍ መሰረት አድርጎ፤ የአማራን ሕዝብ፣ ክልላዊ መንግሥትን እና መሪ ፓርቲው በዚህ ጦርነት የነበራቸውንና ዛሬም እያሳዩ ያለውን ተሳትፎ፤ በሂደቱ የተስተዋሉ ችግሮችና በቀጣይም ሊከተሏቸው ስለሚገባቸው አቅጣጫዎች በሚገባ ተንትኖ ወደ ውይይት ገብቷል፡፡

ይሁን እንጂ አንዳንድ ወገኖች መስሏቸው፤ ሌሎቹ ደግሞ ምንጊዜም ቢሆን የአማራን ሕዝብ፤ መሪ ድርጅትና መንግሥት በተለያዩ አጀንዳዎች በመጥመድ በሴራ ፖለቲካ ሀገር በማመስ የጠላት አጋር የመሆን ዓላማ ያላቸው መሆኑ፣ ‹ውይይት እየተካሄደበት ያለውን ሰነድ አዛብተውና ከአውዱ ውጭ ኤዲት አድርገው› በማኅበራዊ ሚዲያ ሐሰተኛ መረጃ ሲያሰራጩና መሪ ድርጅታችንና የክልሉን መንግሥት ሲያብጠለጥሉ እየተመለከትን ነው፡፡

ይሁን እንጂ “ከሐዋሳ የውይይት መድረክ የተገኘ ሰነድ ነው” ተብሎ እየተዘዋወረ ያለው ሰነድ በተለይም በአማራ ክልል ውይይት እየተካሄደበት ካለው ሰነድ የተለየ ከመሆኑም በላይ፤ አሁን እየተዘዋወረ ያለው ሰነድ የአማራ ሕዝብ በዚህ ጦርነት የከፈለውን ዋጋና የነበረውን አስተዋጽኦ የሚያሳየውን ክፍል ሆን ብሎ ቆርጦ በማስቀረትና ከአውዱና ከይዘቱ ውጪ ‹ኤዲት› በማድረግ እየተሰራጨ ያለ ሰነድ መሆኑን አረጋጠናል፡፡ ይህ ጉዳይ ጠላቶቻችን ሆን ብለው የአማራን ሕዝብ ለማስቆጣትና ክልሉን የትርምስ ማዕከል ለማድረግ አስበው እየሠሩ ስለመሆኑ በቂ ማሳያ ነው፡፡

በመጨረሻም የአማራ ክልል ሕዝብና መንግሥት እንዲሁም መሪ ድርጅቱ ብልጽግና ከትግራይ ወራሪ ጋር በተካሄደው ጦርነት ከባድ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ሕዝባችን አርበኝነት ውርሱ ስለመሆኑ በተግባር አስመስክሯል፡፡ ይህንን እውነታ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የሚመሰክሩት ሀቅ ነው፡፡ ሀገራዊ ሰነዱም ይሄን እውነታ በተገቢው ለታሪክ ይሆን ዘንድ ከትቦታል፡፡ በአንጻሩ በሂደቱ የታዩ ስህተቶችና የወደፊቱ የትግል አቅጣጫዎችም በተለይም በክልላዊ ሰነዱ በተገቢው ተመላከተዋል፡፡ ይሄን እውነታ በእስከዛሬው ውይይት የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች የሚያረጋጡት ሲሆን፤ እስካሁን በውይይቱ ያልተሳተፉ ወገኖችም በቀጣይ በሚኖሩ መድረኮች ስለሚሳተፉ እውነታው በመድረክ ሲቀርብ ያኔ ሀቁን ይረዱታል ብለን እናምናለን፡፡ የዚያን ጊዜ ሁላችንም ጠላቶቻን ምን ያክል እንደማይተኙልን የተሟላ ግንዛቤ ይኖረናል፡፡ ዛሬም ሆነ ነገ ለአማራ የማይተኙ ደመኛ ጠላቶች እንዳሉብን አምነን በጠላት የሴራ አጀንዳዎች እንዳንጠለፍ የወትሮ ዝግጁነት ሊኖረን ይገባል፡፡ በዚህ አጋጣሚ እንደመሪ ድርጅት መነሻና መዳረሻችን የህዝባችን ክብርና ጥቅም ማስከበር ብቻ እንደሆነ ማረጋገጥ እንወዳለን፡፡

መነሻና መዳረሻችን የሕዝባችን ክብርና ጥቅም ማስከበር ብቻ እንደሆነ ማረጋገጥ ነው!

የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት
ባሕር ዳር-ኢትዮጵያ
ጥር 06/2014 ዓ.ም

Exit mobile version