Site icon ETHIO12.COM

ኦሮሚያ – ወዴት?

በወለጋ፣በምዕራብ ሸዋና በአንዳንድ የክልሉ ገጠራማ አካባቢ እየሆነ ያለውና መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል ግራ የሚያጋባው ጉዳይ ለሰሚ፣ ለነጋሪና ለተመልካች ውል የሌለው ሆኗል። ዕለት ዕለት የሚፈጸመው የአጋች ታጋች ድራማ ሕዝብ ደም እያስለቀሰ ነው። ግድያን ሳይጨምር ከምትታለብ ላም ጀምሮ ንበታቸውን የተቀሙና ማሳቸውን ማጨድ ያልቻሉ ምስኪን የኦሮሞ ልጆች ስለምን ይህ እንደሚፈጸምባቸው ፊት ለፊት ወጥቶ የሚያስረዳና ሃላፊነት የሚወስድ አካልም የለም። ትግሉ ለማንና እንዴት እንደሆነም ዜጎችን አስጨንቋል።

በምዕራብ ሸዋ ሁለት ወንድማማቾች ተያዙ። በእያንዳንዳቸው ስም አንድ መቶ ሺህ በድምሩ ሁለት መቶ ሺህ ብር እንዲከፈላቸው አጋቾቹ ጠየቁ። የተገኘው መቶ ሺህ ነበርና “ያለን ይህ ነው” ብለው መቶ ሺህ አድርሱ እተባሉት ስፍራ አደረሱ። ታላቁ ሲለቀቅ፣ የተጠየቀው ሁለት መቶ ሺህ በመሆኑና የተላከው ገንዘብ የአንድ ሰው ዋጋ በመሆኑ ታናሽየው ተገደለ። ይህን ለሰሚ የሚከብድ ድራማ ሲሰራ በቅርብ የነበሩ ምስክሮች እንዳሉት ይህ ሁሉ የሚሆነው ለምን ሲባል እንደሆነ ምክንያት አይቀርበበትም።

ይህ ቀበሌው፣ ወረዳው፣ ሰፈሩና መንደሩ፣ የሟቾቹ ማንነት በሚታውቅ ቤተሰብ ላይ የደረሰ አንድ ማሳያ ነው። በም ዕራብ ሸዋ ጮቢ ከተማ ሀያ ዓምስት ሚሊዮን ብር የወጣበት የንጹህ ዉሃ መጠጥ ወድሟል። ሰባ አምስት ከመቶ የከተማዋ መሰረት ልማት አምድ ተደርጓል። ነዋሪዎች ተዘርፈዋል። ሸኔ ለሶስት ቀናት ተቆጣጥሮ ቤተ ክርስቲያን ወድሟል። ይህ ምን የሚሉት ትግል ነው? ለማን ነው ትግሉ? የማንን መሰረት ልማት በማውደም ነው ትግሉ የሚካሄደው? ማንስ ነው ይህንን መመሪያና ትዕዛዝ የሚያስተላልፈው? ይህ ሁሉ የሚሆነው በፖለቲካ ትግል ስም ከሆነ ሃላፊነት ወስዶ የሚያስረዳና ለውድመቱ ሃላፊነት የሚወስድ አካል መኖር እንደሚገባው ግራ የገባቸው እይገለጹ ነው።

በሌላ በኩል ችግሩን የሚያጎላውና መድሃኒት አልባ ያስመስለው ይህ ሁሉ ሲሆን አመራሩ የት ነበር? ካድሬው ምን ይሰራ ነበር? ደህንነቱ የት ተኝቶ ከርሞ ነው? ብሎ መጠየቅ እንጂ ምላሽ ማግኘት አለመቻሉ መሆኑን ነዋሪዎች እያመለቱ ነው። ሕዝብ እህሉን ወደ ገበያ እንዳይልክና እንዳይገበያይ ተከልክሎ፣ ያደለበው እየታረደበት፣ የዘራው እየታጨደበት፣ መከራ ውስጥ መሆኑንን ማንም “ኦሮሞ ነኝ የሚል” የሚያውቀው ሃቅ ሆኖ ሳለ “እኔ አካባቢ አልመጣም” በሚል ዝምታ መመረጡ ነገን አሳሳቢ እንደሚያደርግባቸው የሰጉ ዕለት ዕለት የሚናገሩት ጉዳይ ነው።

“ወያኔ በወረራ የያዛቸውን አካባቢዎች እየዘርፈና መዝረፍ ያልቻለውን እያወደመ አገር ዱቄት እንዳደረገ ዓይነት አንድ ወረዳ ማውደም በፖለቲካ ትግል ሂሳብ ታይቶም ተሰምቶም አያውቅም። የማንም ዓላማ አራማጅ ቢሆን ይህ የተፈጸመው በኦሮሞ፣ ኦሮሞ ላይ መሆኑ ጉዳዩን እጅግ ግራ የሚያጋባ አድርጎታል። ምን እየሆነ ነው?” የሚልና ” እነማን፣ የየት አካባቢ? ወይም ከየት የተነሱ ናቸው ይህንን የሚፈጽሙት” በሚል የሚነሳው ጥያቄም ከዕለት ዕለት እያየለ ነው።

በኦሮሚያ ያሉ ልሂቃን፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ አባገዳዎችና አደ ስንቄዎች ይህንን ተግባር ለማስቆምና ወደ ውይይት ለመውሰድ ለምን ጥረት አያደርጉም? በሚል ጥያቄ ለሚያነሱ ” ተሞክሯል። ችግሩ መሪ ያላቸው አይመስሉም። የሚታወቀው አደረጃጀታቸው የሚለውና በተግባር የሚሆነው እጅግ የተለያየ ነው። አንዳንዶቹ ሙሉ በሙል ዝርፊያ ላይ የተሰማሩ ሆነዋል። ተው የሚል መካሪ ሲነሳ ይገደላል። ነገሩ በራሳቸው መካከልም ልዩነት ፈጥሯል …” ወዘተ የሚል ምላሽ እንደሚሰጥ ነው የሚነገረው።



ከሁሉም በላይ ኦሮሞ ላይ ኦሮሞ ወንጀል እየሰራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲያውግዙ፣ ነገሩን ለማርገብ ሲሞክሩ አይሰማም። ልክ የድርጊቱ ተባባሪ የሆኑ ያህል አብዛኞቹ ጆሮ ዳባ ማለታቸው ሕዝቡን እያሳዘነው እንደሆነ የሚገለጸው በምሬት ነው።

ከፖለቲካ ትግል ይልቅ ወደ ዝርፊያና የማፍያ አካሄድ እያዝነበለ ያለው የኦሮሚያ ፖለቲካ ” ኦሮሚያ ወዴት ወዴት?” የሚያሰኝ ሆኗል። “ሰዎች መኪናቸውን ይነጠቃሉ። ይታፈናሉ። ቀለብ ስፈሩ ይባላሉ። ገንዘብ ይወሰድባቸዋል። የፈለጉትን ሃሳብ መደገፍ አይችሉም። እርሻቸው የሚታጨድባቸው፣ ያደለጉት የሚበላባቸው፣ ላሞቻቸው ትየተወሰዱባቸው ጥቂት አይደሉም። ይህ እስከመቼ ይቀጥላል? መጨረሻውስ ምን ሊሆን ይችላል?” የሚሉ ወገኖች “የመፍትሄ ያለህ” እያሉ ነው። ቦታ እየቀያየሩ ዝርፊያ ላይ ያተኮሩት ታጣቂዎች ወደ አካባቢ አርበኛነት እየተቀየሩ እንደሆነም እየተወራ ነው። በዚህ ከቀጠለ ኦሮሚያ ” የጎበዝ አለቆች” እንዳይቀራመቷት ስጋት አለ። አሳባቸውን የሰጡን እንዳሉት ” ተረኛ ነው እየተባለ የሚወቀሰው ኦርሚያ ቀጣዩ የጎበዝ አለቆች መናኸሪያ ባለ ተራ እንዳይሆነሰጋለሁ” ብለዋል።

ስጋቱ ያለው በተወሰኑ አካባቢዎች ቢሆንም የሚሰፋበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል የሚገልጹ ጥቂት አይደሉም።

Exit mobile version