Site icon ETHIO12.COM

የዩክሬን ቀውስ ተባብሷል፤ ሩስያ ላይ ጭና ለመፍጠር አውሮፓውያን መስማማት አልቻሉም

– ሩስያን ከዓለም የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ስርዓት ስዊፍት ማስወጣትንና ወይም ኖርድ ስትሪም ሁለት የተባለውን የሩስያያ ጀርመን የጋዝ ማስተላለፊያ ቧምቧን ማስቆምን ይጨምር አሁንም ግልጽ አይደለም።

የኅብረቱ አባል ሀገራትና መንግሥታት መሪዎች በመርህ ደረጃ በሩስያ ላይ የቅጣት እርምጃዎች ለመውሰድ ቢስማሙም ምን ዓይነት እርምጃዎች ይሁኑ በሚለው ላይ ግን መግባባት አልቻሉም። የዚህም ምክንያቱ ከአባል ሀገራት መካከል ከሩስያ ጋር ቅርብ የኤኮኖሚ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መኖራቸው ነው።በዚህ ረገድ ጀርመን ኦስትሪያ እና ሀንጋሪ ይጠቀሳሉ።

በዩክሬን ጉዳይ ፣አውሮጳና አሜሪካ ከሩስያ ጋር የጀመሩት ውዝግብ ተካሮ ቀጥሏል።ሩስያ ዩክሬንን ልትወር ትችላለች የሚል ስጋት አለን የሚለው ኔቶ በሩስያ ላይ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን አስታውቋል። ሩስያ ግን ዩክሬንን የመውረር እቅድ የለኝም እያለች ነው። ሩስያ ከዩክሬን ጋር በሚያዋስናት ድንበር ላይ ቁጥሩ አንድ መቶ ሺህ የሚደርስ ወታደር ካሰፈረች ወዲህ የምዕራቡ ዓለምና የሩስያ ውዝግብ ተካሯል፤ውጥረቱም ተባብሷል። የአውሮጳ ኅብረት ና አሜሪካ ሩስያ ዩክሬንን ትወራለች የሚል ስጋት እንዳላቸው ደጋግመው ሲናገሩ ቆይተዋል። በአንጻሩ ወታደሮችዋን ዩክሬን ድንበር ላይ ያስጠጋችው ሩስያ ግን ዩክሬንን አልወርም ብትልም ያመናት ያለ አይመስልም።

ምንም እንኳን ሩስያ ጥቃት የመፈፀም እቅድ እንደሌላት ብትናገርም ጥያቄዎችዋ ካልተሟሉ ግን ምንነታቸውን በግልጽ ያልጠቀሰቻቸውን እርምጃዎች ልትወስድ እንደምትችል ማስጠንቀቅዋ አልቀረም።ከሩስያ ጥያቄዎች ዋነኛው የፀጥታ ዋስትና ሲሆን ይህም የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት በምህጻሩ ኔቶ ወደ ቀድሞ የሶቭየት ኅብረት ግዛቶች እንዳይስፋፋ የሚጠይቅ ነው።

ይህም ኔቶ ዩክሬንን በአባልነት ላለመቀበል ቃል እንዲገባ ያቀረበችውን ጥያቄ ያካትታል። ሩስያ ዩክሬንን መውረርዋ የማይቀር እንደሆነ ግልጽ እየሆነ መጥቷል የሚለው የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት ከረር ያሉ ማስጠንቀቂያዎችን ከማስተላለፍ በተጨማሪ የጦር መርከቦችንና ተዋጊ አውሮፕላኖችን ወደ ምስራቅ አውሮጳ እየላኩ ነው ብሏል።

የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚኒስቴር ፔንታገን በበኩሉ አውሮጳ ይዘምታሉ የተባሉ 8500 የአሜሪካን ወታደሮች በተጠንቀቅ እንዲጠባበቁ ትዕዛዝ አስተላልፏል። የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጉዳዩ ላይ ቁልፍ ከሆኑ የአውሮጳ አጋሮቻቸው ትናንት መክረዋል። በዚህ መሀል ምዕራቡ ዓለም እንደሰጋው የሩስያ

ወታደሮች ድንበር ተሻግረው ዩክሬንን ቢወሩ ምን ይፈጠራል የሚለው አሳስቧል።

ትናንት በጉዳዩ ላይ የመከሩት የአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባወጡት መግለጫ ሩስያ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ጥቃት ከሰነዘረች ከባድ መዘዞች እንደሚጠብቋት አስጠንቅቀዋል።

የኅብረቱ የውጭ ጉዳዮች ሃላፊ ጆሴፕ ቦሬል እንዳሉት ችግሩን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ካልተሳካ አውሮጳ እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅቷል።

« ሩስያ በዩክሬን ድንበር ላይ ወታደሮችን የማከማቸቷን ጉዳይ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። ዲፕሎማሲው ሳይሳካ ሩስያ ዩክሬን ላይ ጥቃት ከፈጸመች እርምጃ ለመውሰድ በደንብ ተዘጋጅተናል።በርግጠኝነት እርምጃችን ፈጣን፣ወሳኝ ነው የሚሆነው፤በአውሮጳ ኅብረት ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ጭምር።»
ይህ አባባል ከአውሮጳ ኅብረት በኩል ሲሰማ የመጀመሪያው አይደለም። ኅብረቱ ደጋግሞ የተናገረው ማሳሰቢያ ነው።ሆኖም ሩስያ እንደተሰጋው ዩክሬንን ከወረረች የሚደርስባት መዘዝ ምን ይሆን ለሚለው በታኅሳስ መጀመሪያ ላይ በተካሄደ የኅብረቱ ጉባኤ ላይ የተነገረውን ማንሳት ይቻላል።

በዚህ ጉባኤ ላይ የኅብረቱ አባል ሀገራትና መንግሥታት መሪዎች በመርህ ደረጃ በሩስያ ላይ የቅጣት እርምጃዎች ለመውሰድ ቢስማሙም ምን ዓይነት እርምጃዎች ይሁኑ በሚለው ላይ ግን መግባባት አልቻሉም። የዚህም ምክንያቱ ከአባል ሀገራት መካከል ከሩስያ ጋር ቅርብ የኤኮኖሚ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መኖራቸው ነው።በዚህ ረገድ ጀርመን ኦስትሪያ እና ሀንጋሪ ይጠቀሳሉ።

እንደነዚህ ሀገራትም ባይሆን ፖርቱጋል እና ኔዘርላንድስም በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ናቸው። በሩስያ ላይ የቅጣት እርምጃ ለመውሰድ ደግሞ ሁሉም አባል ሀገራት መስማማት አለባቸው።በዚህ የተነሳም የአውሮጳ ኅብረት አሁን በርግጠኝነት የሚወስዳቸው የማዕቀብ እርምጃዎች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ግልጽ አይደለም።

ማዕቀቦቹን ያዘጋጁት የአውሮጳ ዲፕሎማቶች እንደሚሉት ቅጣቱ ሩስያ ዩክሬንን በወረረች በ48 ሰዓታት ውስጥ ተግባራዊ መሆን አለበት።ይህም ግልጽ ያልተደረገ የማዕቀብ እቅዶችን ካወጡት ከዩናይትድ ስቴትስና ከብሪታንያ ጋር መቀናጀት አለበት ተብሏል። እናም ይጣላሉ የተባሉት ማዕቀቦች ሩስያን ከዓለም የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ስርዓት ስዊፍት ማስወጣትንና ወይም ኖርድ ስትሪም ሁለት የተባለውን የሩስያያ ጀርመን የጋዝ ማስተላለፊያ ቧምቧን ማስቆምን ይጨምር አሁንም ግልጽ አይደለም።

በዚህ መሀል ጀርመን ውዝግቡ እንዲረግብ መነጋገሩ አስፈላጊ ነው ብላለች የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ

«የምንገኝበት ሁኔታ የሚያመለክተው ለኔ ዋናው ነገር ውዝግቡን የሚያረግቡ ሁሉንም እርምጃዎች መውሰድ እንዳለብን ነው።ውይይቱን መቀጠል መቻል፤ እርስ በርሳችን መነጋገር እንዳለብን ለሩስያ መንግሥት ግልጽ ማድረግ እንዳለብን ነው። አራቱን የዲፕሎማሲያዊ ድርድር ማካሄጃ መንገዶችን መጠቀም አለብን።ከዚሁ ጋርም ለሁሉም ሁኔታዎች ተዘጋጅተናል። »
ጀርመን ባለፈ ታሪኳ ምክንያት ወደ አካባቢው ወታደር መላክ እንደማትፈልግ አስታውቃለች።ታዲያ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የምትገኘው ጀርመን ሃላፊነትዋን እንዴት ትወጣ ይሆን የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አልቀርም።አምባሳደር ክሪስቶፍ  ሆይስገን  የቀድሞዋ የጀርመን መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የረዥም ጊዜ የጸጥታ ፖሊሲ አማካሪና በተመድ የቀድሞ የጀርመን አምባሳደር እንዲሁም  «የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ»  የወደፊቱ ሊቀመንበርም ናቸው። ሆይስገን ጀርመን ለዩክሬንና ሩስያ ጉዳይ መፍትሄ በማፈላለግ ተሞክሮ ያላት ሀገር መሆንዋን  ያስታውሳሉ ።
«ጀርመን በጣም አስፈላጊ የሆነ ሚና እየተጫወተች ነው።ይህንንም ሃላፊነታችንን ባለፈው ጊዜ ተወጥተናል። ሩስያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ የቀድሞዋ የጀርመን መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከያኔው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኦሎንድ ጋር የቀድሞው የዩክሬን ፕሬዝዳንት ፔትሮ ፖሮሽንኮና የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት በማምጣት የሚኒስኩ ስምምነት እንዲፈርሙ በማድረግ ጥቃቱን አስቁመናል።»
በዩክሬን ጉዳይ ላይ ለዶቼቬለ ቃለ መጠይቅ የሰጡት አምባሳደር ሆይስገን እንደሚሉት ሩስያ ከ8 ዓመት በፊት በዩክሬን ላይ የፈጸመችው ወረራ አሁን እንዲደገም አይፈለግም ።ሩስያ ይህን የምትዳርግ ከሆነ ግን መዘዙን በትክክል ልትረዳ ይገባል ብለዋል። 

«የመራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የዲፕሎማቲክ fጉዳዮች አማካሪ ነበርኩ።በ2013፣2014፣2016 ሩስያ ዩክሬንን ስትወር ነበርኩ።ስለዚህ አሁን ያለውን ሁኔታ ስንመለከት የዛሬ 8 ዓመት የሆነውን  እናስታውሳለን ።ማዕቀብ ሲጣል ሩስያ ጥቃቷን ቀንሳለች።ይህ እንዲደገም አንፈልግም። አሁን እኛ የምንፈልገው ፑቲን በዩክሬን ላይ ለመውሰድ ዝግጁ ነን ያሉትን እርምጃ ሩስያ በእርግጥ የምትወስድ ከሆነ ምን ሊገጥማት እንደሚችል በትክክል እንድታውቅ ነው።»  
እስካሁን ከአውሮጳ ኅብረት በኩል ሩስያ በዩክሬን ላይ ወረራ የምታካሂድ ከሆነ ኅብረቱ የሚወስደው ማዕቀብ ምን እንደሚሆን ግልጽ አይደለም። በሌላ በኩል ብሪታንያና ዩናይትድ ስቴትስ ክየቭ የሚገኙ ዲፕሎማቶቻቸውን እያስወጡ ነው።ይህንንም የክየቭ መንግሥት ተቃውሟል። ጀርመን ግን በራሳቸው ጥያቄ እንውጣ የሚሉ ዜጎቿን ብቻ ከዩክሬን እንደምታስወጣ ነው 

ያሳወቀችው። በዚህ መሀል ባለፈው ቅዳሜ የጀርመን የባህር ኃይል አዛዥ ምክትል አድሚራል ኬይ አሂም ሾነንባህ «ዩክሬን የክሬምያን ባህረ ሰላጤ መልሳ አትይዝም እንዲሁም ፑቲን ክብር ሊሰጣቸው ይገባል»ሲሉ ከተናገሩ በኋላ ከሃላፊነታቸው ተነስተዋል። ይህን ጨምሮ የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት በሩስያ ላይ ይጣላል ስለሚባለው ማዕቀብ የተለያየ አቋም መያዛቸው ምዕራባውያን ሀገራት ምን ያህል አንድ ናቸው? ምን ያህልስ በራሳቸው ይተማመናሉ?የሚሉ ጥያቄዎች እያስነሳ ነው ።እርስዎስ ምን ይመስልዎታል የተባሉት አምባሳደር ሆይስገን ሲመልሱ  
«የጀርመን የባህር ኃይል አዛዥ ያሉትን ካሉ በኋላ በዚያኑ እለት ከስራቸው ተነስተዋል።ይህም በጀርመን መንግሥት ውስጥ አንድነት እንዳለ ያሳያል። በአውሮጳ ኅብረትም ከዩናይትድ ስቴትስ ጋርም ኅብረት እንዳለ ያሳያል።እንደሚመስለኝ በነገራችን ላይ አሜሪካውያን ወዳጆቻችን ጉዳዩን በሚያስተባብሩበት መንገድ በጣም ደስተኛ ነን።»ብለዋል።
ምዕራባውያን ተባብረው የተነሱባት ሩስያ በዩክሬን ጉዳይ ሰበብ ለተባባሰው ውጥረት ዩናይትድ ስቴትስንና ኔቶን ተጠያቂ አድርጋለች።የሩስያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ 
«ውጥረቱ እየተባባሰ የሄደው ዩናይትድ ስቴትስና ኔቶ በሚያሰራጩት መረጃና በሚወስዷቸው ተጨባጭ እርምጃዎች ምክንያት የተፈጠረ መሆኑን እንድትገነዘቡት እንፈልጋለን።መረጃን በሚመለከት ፣ ሁላችንም እንደሰማነው ስጋት የሚፈጥሩ መረጃዎችን ማሰራጨት ማለቴ ነው።ይህም የሀሰትና የተጭበረበሩ መረጃዎችን በስፋት ማሰራጨትን ይጨመራል።ተጨባጭ እምጃዎች ስል ደግሞ ኔቶ ወደ ምስራቅ አውሮጳ  መሳሪያና ወታደሮችን ለማስፈር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ያሳወቀበት መግለጫው ነው።ይሄ ሁሉ ውጥረት ወደ ባሰ ደረጃ እንዲያመራ እያደረገ ነው።»
ያሉት ፔስኮቭ ሩስያም ጸጥታዋን ለማስከበርና ጥቅሞችዋን ለማስጠበቅ አስፈላጊ እርምጃዎችን መውሰዷ እንደማይቀር አስታውቀዋል።ዩክሬንም በበኩልዋ ለጥቃት እየተዘጋጀት ነው ብለዋል።ኔቶ ዩክሬን ጥቃት ከመሰንዘር ትቆጠብ ዘንድ መልእክት እንዲያስተላልፍም ጥሪ አቅርበዋል።።
«የሀገራችን መሪ፣ እንደ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ እና የሀገሪቱን የውጭ ፖሊሲ እንደሚበይን ሰው የጋራ ደህንነታችን እንዲረጋገጥ ጥቅማችንንም ከጥቃት ለመጠበቅ አስፈላጊ እርምጃዎችን ይወስዳሉ።በነገራችን ላይ የዩክሬን ባለስልጣናት ራሳቸውን ነጻ ሪፐብሊክ ብለው ከሚጠሩት ከዶኔትስክና ከሉሀንስክ ጋር በሚዋሰኑበት ድንበር ላይ ትልቅ ኃይል እያደራጁ ነው።ይህ ኅይልን የማሰባሰብ ተግባር ለመከላከያ ዘመቻው የተደረጉ ዝግጅቶች ናቸው።እደዚህ ዓይነት አደጋ መኖሩ እውነት ነው።ለኔቶ ልናስተላልፍ የምንፈልገው መልዕክት በሚያወጧቸው የተለያዩ መረጃዎች ክየቭ ጉዳዩን ለመፍታት ኃይል የመጠቀም ሃሳቧን እንድትተው ጥሪ እንዲያቀርብ እንጠይቃለን።ከዚህ ሌላ ለወደፊቱ እንደዚህ ዓይነት ውጥረቶችን የማስቀረት ዓላማ ላላቸው ላቀረብናቸው ጥያቄዎች ማለትም ለጸጥታችን ዋስትና በጽሁፍ መልስ እንዲሰጠን እየጠበቅን ነው።»
ዶቼቬለ አምባሳደር ሆይስገንን የሩስያው መሪ የፍላጎት ምን ሊሆን ይችላል ? ለምንስ ነው ለዩክሬንስጋት የሆኑት የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር።

«ከድኅረ ሶብየት ኅብረት በኋላ በቀድሞዎቹ የሶቭየት ግዛቶች ያለውን ሁኔታ ስንመለከት በጆርጅያ፣ ዩክሬን፣ባለፈው ዓመት በቤላሩስ እንዲሁም ከጥቂት ሳምንታት በፊት በካዛክስታን ፣ሰዎች በድኅረ ሶቭየት ዓለም ምንም ደስተኛ አይደሉም።ፑቲን ደግሞ ይህ ወደ ሩስያም ይዛመታል ብለው ይፈራሉ።በተቃዋሚዎቻቸውም ላይ ጠንካራ እርምጃ እየወሰዱ ነው። መገናኛ ብዙሀን ብሔረተኛ ሁሉም ብሔረተኛ ሆነዋል።እናም ፑቲን በጣም ብሔረተኛ በሆነ መንገድ ህዝባቸውን ደስተኛ ሆኖ እንዲቆይ ለማድረግ እየሞከሩ ነው።በሌሎች ሀገራት እንዳሉት ዓይነት ተቃዋሚዎች እንዲነሱባቸው አይፈልጉም። »
ታዲያ የፑቲን ዓላማ ምንድነው ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱም በአካባቢያቸው በሚገኙ ሀገራት ላይ የቀድሞ የሶቭየት ኅብረት ዓይነት ተጽእኖ መፍጠር ነው የሚፈልጉት ብለዋል።
«ፑቲን በአንድ ወቅት የሶቭየት ኅብረት መፈረካከስ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ካታስትሮፍ ታላቅ ውድቀት ነው ብለዋል።እናም የሶቭየት ኅብረት አምሳያ ተጽእኖ መፍጠር ነው የሚፈልጉት። ለርሳቸው በርግጥ ዩክሬን ዴሞክራሲያዊት ሀገር መሆንዋን ማየት ፣ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ያሏት ፤ ዴሞክራሲያ ምርጫ የምታካሂድ ሀገር ፕሬዝዳንትዋንም የምትቀይር ከቀድሞውም የተሻለች ሀገር መሆንዋ ፑቲን የሚፈሩት አንድ ነገር ነው። ፑቲን የአውሮጳ ኅብረትንና አጎራባች ሀገራትን እንዳይረጋጉ ለማድረግ እየሞከሩም ነው።የዚህም ምክንያቱ የኛ ምሳሌያዊነት ሲሳካ ማየት አለመፈለጋቸው ነው።»
ያም ሆኖ ግን እንደ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ሁሉም አማራጮች ለፑቲን ክፍት መደረግ አለባቸው የሚሉት ሆይስገን ከሩስያ ጋር የምንነጋገርበትን መንገድ በማመቻቸት ፑቲን ከችግሩ መውጣት የሚችሉበትን መንገድ ማሳየትም አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።


ኂሩት መለሰ እሸቴ በቀለ DW Amharicx

Exit mobile version