Site icon ETHIO12.COM

የመከላከያ ሰራዊትና የክልል ጸጥታ ሃይሎች እርምጃ እንዲወስዱ ታዘዙ

መንግስት በህግ “አሸባሪ” ተብሎ ከተፈረጀ ቡድን ጋር ምንም ዓይነት ድርድር እንደሌለ ቢያስታውቅም፣ አንድ ግለሰብን ጠቅሶ ከአሸባሪ ሃይል ጋር ድርድር ለማድረግ ስምምነት መደረሱ በተዘገበበት ዕለት፣ የመከላከያ ሰራዊትና የክልል ጸጥታ ሃይሎች እርምጃ እንዲወስዱ የታዘዙበት አቅጣጫ መቀመጡ ተገለጸ።

መንግስት ሽብርተኛው ህወሃት ለሚያደርገው ትንኮሳ የክልልና የመከላከያ ሃይል አስፈላጊ ያለውን እርምጃ እንዲወድ አቅጣጫ ያስቀመጠው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተመራው የፌደራል ጸጥታ ምክር ቤትና የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች ስብሰባ ነው። በስብሰባው በሀገራዊ ጸጥታ አግባብ ላይ የቀጣይ አቅጣጫ ላይ ትኩረት ምን ሊሆን እንደሚገባ በመነጋገር ሽብርተኛው የህወሃት ቡድን ለሚያደርገው ትንኮሳ የመከላከያ ሰራዊትና የክልል ጸጥታ ሃይሎች በጥናት ላይ ተመስርተው እርምጃ የሚወስዱበት አቅጣጫ ተቀምጦላቸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተመራው የፌደራል ጸጥታ ምክር ቤትና የክልል ርእሳነ መስተዳደሮች ስብሰባ ሀገሪቱ አሁን ያለችበት አንጻራዊ ሰላምና ጸጥታን አጠናክሮ ማስቀጠል፣ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ማስቆምና በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠሩ ኢመደበኛ አደረጃጀቶችን ቅርጽ ማስያዝ እንደሚገባ ሙሉ በሙሉ ከስምምነት ላይ መድረሱና ለተግባራዊነቱ እንቅስቃሴ እንዲጀመር ወስኗል። ይህ የአገሪቱ ከፍተኛው የጸጥታ ምክር ቤት በተለይ ሽብርተኛው የህወሃት ቡድን የሚያደርገውን ትንኮሳን ተከትሎ እርምጃዎች የሚወሰድበት አግባብ አኑሯል።

የፌደራል ጸጥታ ምክር ቤትና የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች ሙሉ ተሳትፎ በተካሄደው በዚህ ልዩ ስብሰባ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣በሀገሪቱ ቀጣይ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮች ከወዲሁ መስመር የማስያዝና የማስተካካያ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ማጣቀሻ መረጃዎችን አስደግፈው መናገራቸውን የመንግስት መገናኛዎች ዘግበዋል። ዝርዝሩን ግን አላካተቱም።

የህገወጥ የመሳሪያ ዝውውር፣ የኮንትሮባንድና መሰል እንቅስቃሴዎች በስብሰባው በጥልቅ የተገመገሙ ሲሆን፣ በውስጥ ያሉ ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ ቀጠናው ላይ ሰላምን ማስጠበቅና ሀገራዊ ግንኙነትን ማጠናከር ላይ አቅጣጫዎች እንደተቀመጡም ታውቋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ በበኩላቸው የአሸባሪ ቡድኖችን እንቅስቃሴ በመገምግም እርምጃ መውስድ የሚቻልበት ሁኔታ ተመርምሮ እርምጃ መውሰድን እንዲቻል አቅጣጫ እንደተሰጠ መግለጻቸውን ሪፖርቶቹ ያስረዳሉ። የተቀመጡ አቅጣጫዎችም ሆነ የተደረሰባቸው ስምምነቶችን የፌደራልም ሆነ የክልል የጸጥታ አካላትና አስተዳደሮች በየደረጃው ተግባራዊ እንደሚያደርጉትም ታውቋል።

ይህ ምክር ቤት ቀደም ሲል ባህር ዳር፣ በቅርቡ ሰመራ ላይ የመከረና ሙሉ ማጥቃት እንዲጀመር ተመሳሳይ አቅጣጫ አስቀምጦ እንደነበር ይታወሳል።

Exit mobile version