Site icon ETHIO12.COM

የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ህብረቱ ቀናነት እያሳየ መሆኑንን አመላክች ምላሽ ሰጡ

የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም ዕድል ለመስጠት የወሰዳቸውን በጎ እርምጃዎች እንደሚያደንቁ እና በግጭቱና በድርቅ ምክንያት የሰብአዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የአውሮፓ ህብረት ድጋፍ እንደሚያደርግ የህብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አስታወቁ። ነግግራቸው የህብረቱ አቋም ቀና መሆኑንን የሚያመላክት እንደሆነ ተመልክቷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ዶ/ር አኔታ ዌበር ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ላይ ወይይት አድርገዋል።

በዚሁ ወቅት አቶ ደመቀ መኮንን ለልዩ ልዑኳ በሰጡት ማብራሪያ፥ የህወሃት የጥፋት ቡድን በአዲስ መልክ በአፋር በኩል ግጭቱን በማስቀጠል በሰብዓዊና ቁሳዊ ሀብቶች ላይ ጉዳት በማድረስ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

አያይዘውም በህወሃት የተከፈተው ግጭት ወደ ትግራይ ክልል ለሚደረገው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት መሰናክል እየፈጠረ መሆኑንም ገልፀውላቸዋል። የአውሮፓ ህብረትና ሌሎች ሰላም-ወዳድ አካላት በወራሪው ቡድን ላይ ጫና እንዲያደርጉበትም ጠይቀዋል።

አቶ ደመቀ በማብራሪያቸው በምስራቅና በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በሶማሌ ክልል፣ በኦሮሚያ ደቡባዊ አካባቢዎች እና በደቡብ ክልል በተከሰተው ድርቅ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ለችግር መጋለጡን አውስተው፥ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢ ተቋማትና የልማት አጋሮች ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

አያይዘውም መንግስት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ያሉ ኢትዮጵያውያን የሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው የፀና አቋም ያለው መሆኑን አቶ ደመቀ አረጋግጠውላቸዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ግጭት እንዲፈታ መንግሥት የወሰዳቸውን አዎንታዊ እርምጃዎች በተመለከተም ለልዩ ልዑኳ ያስረዱ ሲሆን፥ እርምጃዎቹ መተማመን መገንባትን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል። አክለውም የአውሮፓ ህብረት መንግሥት ለወሰዳቸው አዎንታዊ እርምጃዎች ተገቢውን እውቅና እንዲሰጥም ጠይቀዋል።

ዶ/ር አኔታ ዌበር በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም ዕድል ለመስጠት የወሰዳቸውን በጎ እርምጃዎች እንደሚያደንቁ ጠቅሰው፥ በግጭቱ እና በድርቁ ምክንያት የሰብአዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የአውሮፓ ህብረት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድርን በተመለከተም የአውሮፓ ህብረት በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት እየተካሄደ ያለው የሶስትዮሽ ድርድር የሶስቱንም ሀገሮች ብሔራዊ ጥቅም በሚያስከብር መልኩ ውጤት ላይ እንዲደረስ የአውሮፓ ህብረት የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል ዶ/ር አኔታ ዌበር።

ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኝ ፍላጎት ያለው መሆኑን በወሰዳቸው ውሳኔዎች ማሳየቱን ገልጸዋል።

አያይዘውም በሀገራዊ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ምክክር በማድረግ የጋራ ሀገራዊ መግባባትን እንዲፈጥሩ እየተደረገ ያለውን ሂደትም አብራርተውላቸዋል።

የአፍሪካ ህብረት የምስራቅ አፍሪካ ልዩ ልዑክ ኦሊሰጎን ኦባሳንጆ ለሚያደርጉት ጥረትም አስፈላጊው ትብብር እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድርን ለማስቀጠል በኢትየጵያ በኩል ዝግጁነት ያለ መሆኑን ጠቁመው፣ ነግር ግን የህዳሴ ግድብ ጉዳይ የልማት ጉዳይ በመሆኑ ፖለቲካዊ አጃንዳ ማድረግን ኢትዮጵያ እንደማትቀበል አቶ ደመቀ እንደገለጹላቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ ፋና ዘግቧል።

Exit mobile version