Site icon ETHIO12.COM

ድህነት እና አስተሳሰብ ያላቸው ትስስር ምን ይመስላል ?

ምን መሰለህ? አንዴ አስተሳሰብ ድህነትን ከፈጠረ በኋላ ድህነት ደግሞ አስተሳሰብን እየወለደ ይቀጥላል፡፡ ከዛ በኋላ መውጫ ቢስ አዙሪት ይፈጠራል፡፡ አሁን መጀመሪያ የቱ መጣ የሚለውን ነገር ስታስብ የዶሮ እና እንቁላል ይመስላል ነገሩ፡፡ ግን እኔ ዝም ብዬ ሳስበው መጀመሪያ ሰው ሁሉ ደሀ ነበረ ወይስ ሰው ሁሉ ሀብታም ነበረ?

የሚለውን ጥያቄ ወደ ኋለ ሄደን ላንመልሰው እንችላለን፡፡ በአጠቃላይ ሰው ሁሉ ሀብታም ነበረ ባንል እንኳ ሰው ሁሉ ደሀ እንዳልነበረ መናገር ይቻላል፡፡ ከዛ የሚመጣው ምንድን ነው? ሁለት ሰዎች የአስተሳሰብ እና ቁሳዊ ሀብት ደሀ ቢሆኑ፤ ለአንዱ አስተሳሰቡን ብትቀይርለት ለአንዱ ደግሞ ጎደለኝ የሚለውን ቁስ ብትቀይርለት እና ከአምስት አመት በኋላ ብትመጣ ምንድን ነው የምታገኘው? ጥናቶች የሚያሳዩት ምንድን ነው? በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ሎተሪ የደረሳቸው ሰዎች ከሁለት አመት በኋላ ስትመለከታቸው ከ90 % በላይ የሚሆኑት የበለጠ ደሀ ሆነው ታገኛቸዋህ፡፡

በብሩ የተነሳ ግማሹ ይጣላል፣ ግማሹ ይፋታል፤ ቀውስ ውስጥ ይገባሉ፤ የነበራቸውን እንኳ ያጣሉ፡፡

ሌላ ሌላ ዐይነት ድኅነት ውስጥም ይገባሉ ማለት ነው?

በትክክል፣ እነኚህ ድኅነቴን አመልጥባቸዋለሁ የምትላቸው ነገሮች ድህነትህን ሊገልጡብህ፣ ሊያባብሱብህ ይችላሉ፡፡ ሰዎች ይህንን ድህነታዊ የሆነ የእጥረት አስተሳሰብ ስትቀይርላቸው በቀላሉ ሕይወታቸው ሊቀየር ይችላል፡፡ በነገራችን ላይ ደሀ ብለን ስናስብ ልብሱ የተቀዳደደ፣ የሚበላው ያጣ ምናምን ብቻ ልንል እንችላለን፡፡ ግን በጣም ቤተ መንግስት የሚመስል ቤት የሚኖሩ፣ ሜርሴዲስ መኪና የሚነዱ፣ በቁሳዊ ሀብት እጅግ በጣም የበለፀጉ ደሀ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

ከልጆቻቸው ከጎረቤቶቻቸው ከሕይወት ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት፣ ለራሳቸው የሚሰማቸው ስሜት ለመኖር እንኳን በብዙ አደንዛዥ እፅ ተሸፋፍነው ነው፡፡ እሱ ድህነት አይደለም ወይ? ደግሞ በጣም ውስን ሀብት ኖሯቸው በአንፃሩ በጣም የበለፀገ ሕይወት የሚኖሩ ሰዎች አሉ፡፡

በአጠቃላይ ግን ድህነት በአስተሳሰብ ላይ ተፅዕኖ የለውም ወይ? የምንል ከሆነ መልሱ “አለው” ነው፡፡ ልጆችህን ጥሩ ጥሩ ትምህርት ቤት መላክ አትችልም፤ ለብዙ ጥሩ ጥሩ ነገሮች ላትጋለጥ ትችላለህ፡፡ ድህነት በሰው ልጅ ላይ ውስንነት ይፈጥራል፡፡ ነገር ግን ድህነት በሰው ላይ ከሚፈጥረው ውስንነት ይልቅ አስተሳሰብ በሰው ላይ የሚፈጥረው ውስንነት ይበልጣል፡፡

ሁኔታዬ አስተሳሰቤን ሊለውጠው ቢችልም አስተሳሰቤ ግን ሁኔታዬን ይበልጥ ሊለውጠው ይችላል ስለዚህ መንገዱ ሁለትዮሽ ነው ፡፡ ድህነት አስተሳሰብን ሊለውጥ አስተሳሰብም ድህነትን ሊለውጥ ይችላል፡፡ ስለዚህ አንዱን ልትለውጥልኝ የምትችል ከሆነ ሁኔታዬን ከምትለውጥልኝ ይልቅ አስተሳሰቤን ብትለውጥልኝ እመርጣለሁ ፡፡

ይሄ ምርጫ ከመጽሐፍ ቅዱሱ ጠቢቡ ሰለሞን ልመና ጋር የሚመሳሰል መስለኛል ፡፡

አዎ እንደውም እሱ “ጥበብ አይነተኛ ነገር ነው” ይላል ጥበብ የበላይ የሆነ ነገር ነው፡፡ የትኛውንም ነገር በጥበብ ልትለውጥ ትችላለህ፡፡ ወደ ሌላ ርዕሰ ጉዳይ ልውሰድህና የአእምሮና አካል ትስስር (Mind-Body Connection) እስከምን ድረስ ነው? በተለይ ጤናማ ከመሆንና ጤናማ ካለመሆን ጋር በተያያዘ ፡፡ አንዳንድ መጽሐፍት የበሽታና ህመም ምንጩ በሙሉ አእምሮአችን ነው” ይላሉ፡፡

እንደውም አንድ ቅርብ ጊዜ ያነበብኩት “Emotions Buried Alive Never Die” የሚል መጽሐፍ ላይ “መሰረታዊው የህመም ምክንያት ያለ ቅድመ ሁኔታ ማፍቀር አለመቻል ወይም በቅድመ ሁኔታ ማፍቀር ነው” ይላል፡፡ አንተ እንዴት ትመለከተዋለህ? አንድን እውነት ለማስተላለፍ ሌሎች እውነቶችን በሙሉ መግደል የለበትም፡፡

አእምሮአችን ወይም አስተሳሰባችን በጤናችን ላይ ትልቅ ተፅዕኖ አለው ፡፡ እሱ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ሰውነታችንም ግን በአስተሳሰባችን ላይ እኩል ተፅዕኖ አለው ፡፡ አሁን ለምሳሌ በጠኔ ውስጥ ሆኜ፣ በጣም ተርቤ ሁሉ ነገሬ ደህና ሆኖ፣ ዶክትሬት ድግሪ ኖሮኝ ለሶስት ቀን ምግብ ባልበላ ዶክትሬት ድግሪ እንዳለው ሰው ማሰብ አልችልም፡፡

ከዛ በኋላ ምግብ እስከማገኝ ድረስ ያ ሁሉ እኔነቴ ዋጋ ላይኖረው ይችላል ፡፡ ለምርምር ወደ አርባምንጭ ሄጄ ወባ ቢይዘኝ ወባ የአስተሳሰብ ውጤት አይደለም የፍቅር እጦትም አይደለም ፡፡ ፕላዝሞዲየም የሚባለው የወባ ተውሳክ ገብቶ ቀይ የደም ሴሎችን ድምጥማጥ ያጠፋል፤ እንደ ወባው አይነት ራስን እስከ መሳትም ሊደረስ ይችላል፡፡ ሰውነቴ በትክክል እስካልተያዘ ድረስ አስተሳሰቤ ሰማይ የነካ ቢሆንም ምንም ለውጥ የለውም ፡፡

ስለዚህ ምግብ፣ እረፍት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ ጤነኛ የሆነ አከባቢ ውስጥ መኖር መሰረታዊ ነገሮች ናቸው፡፡ አሁን ይሄ ኮምፒውተር ቻርጅ ካላደረከው ምን ይጠቅምሀል? ከልክ በላይም ሆነ ከልክ በታች ቻርጅ ብታደርገው አገልግሎት አይሰጥም ፡፡ ስለዚህ ሚዛኑ ምንድን ነው? ሁሉ ነገር በፍቅር አይደለም፡፡

በፍቅር ተጥለቅልቀህም ሶስት ቀን ካልተኛህ ታብዳለህ፡፡ ስለዚህ የሰውነታቸው ጤንነት ወሳኝ ነው ለአስተሳሰብም ጭምር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰውነታችን ሁሉ ነገር ተሟልቶለት ውጥረት ውስጥ ብንሆን፣ አስተሳሰባችን ልክ ባይሆን ሰውነታችን ላይ ችግር ይፈጥራል፡፡

ለምሳሌ፣ “ዲፕሬሽን” ውስጥ፣ ውጥረት ውስጥ ያለ ሰው የሚያመነጨው ሆርሞን አጥንት ላይ ጉዳት ያደርሳል፣ በሽታ የመከላከል አቅምን ይቀንሳል፣ ለተለያየ አይነት “ኢንፌክሽን” አጋልጦ ይሰጣል፡፡ አእምሮአችንም አካላችን ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ “ሳይኮኢሚዮኖሎጂ” አሁን በጣም አስደናቂ የምርምር ዘርፍ ሆኗል፡፡

ጤንነታችን በስነ-ልቦናዊ ሁኔታችን በእጅጉ ይወሰናል፡፡ ለምሳሌ፣ የፈተና ሰሞን ለምንድን ነው ጉንፋን የሚበዛው? ፈታና ውጥረት ነው ፡፡ ውጥረት ደግሞ በሽታ የመከላከል አቅምን ይቀንሳል ሁልጊዜ የፈተና ሰሞን ጉንፋን የሚይዛቸው የሚታመሙ ሰዎች አሉ ፡፡ በጥቅሉ አእምሮአችን የአካላችንን ጤንነት ይወስናል፤ አካላችንም የአእምሮአችንን ጤንነት ሊወስን ይችላል፡፡

ሲግመንድ ፍሮይድ የሕይወት ግብ ደስታ ነው” ይላል በዚህ ብዙ ሰዎችም ይስማማሉ ብዬ አስባለሁ ከዚህ አኳያ ደስታ አስተሳሰብ እና ጤና ያላቸው ትስስር ምን ይመስላል ቀደም ሲል ስለ “ዲፕሬሽን” አንስቻለሁ “ዲፕሬሽ” ሀዘን ነው፡፡ “ዲፕሬሽን” ውጥረት የሚያመነጩዋቸው ሆርሞኖች ፀረ ጤና ናቸው ፡፡ ለረጅም ጊዜ ሰውነታችን ውስጥ ሲቆዩ ስኳር፣ ደም ግፊት፣ ውፍረት፣ የአጥንት መሳሳት ወዘተ ያስከትላሉ፡፡ በአንፃሩ ደስታ ውስጥ ስንሆን አንጎላችን የሚያመነጫቸው ሆርሞኖች የዛ ተቃራኒ ውጤት አላቸው፡፡

ለምሳሌ፣ በጣም በምንስቅበት ወቅት የሚመነጩት ኢንዶርፊን፣ ኢንካታሊንስ የሚባሉ ሆርሞኖች ከሄሮይን እና ከኮይን በጣም በብዙ እጥፍ ጠንካራ የሆኑ ሰውን የማስደሰት እና ሀይል የመስጠት አቅም ያላቸው ሆርሞኖች ናቸው፡፡ ለዚህ ነው ከሳቅን በኋላ ሰውነታችን እፅ የወሰደ ያህል የሚፍታታው፡፡ ለዚህ ነው ለሚያስቁን ሰዎች ገንዘብ የምንከፍለው፡፡ ኮሜዲያኖች በጣም ሀብታሞች ናቸው፡፡

ደስተኛ ሰዎች ረጅም እድሜ ይኖራሉ፤ ደስተኛ ሰዎች ለሰውም ረጅም እድሜ ይሰጣሉ፡፡ ሌላው የደስታ ጥቅም ምንድን ነው? በደስታ ውስጥ ስንሆን በከፍተኛ ሁኔታ የማሰብ እና የመፍጠር አቅማችን ይጨምራል፡፡ በተቃራኒው ሀዘን፣ ብስጭት፣ ውጥረት ውስጥ ስንሆን ቀደም ሲል የዘረዘርናቸው የማሰብ፣ የመፍጠር ወዘተ የአእምሮ ስራዎች በሙሉ እስራት ው

ስጥ ይገባሉ፡፡

ሶማሌ ክልል ውስጥ ቢወጣ ኢትዮጵያን ሊጠቅም የሚችል ሀብት ምንድን ነው? ብለህ ስትጠይቅ እሰማለሁ በትክክል ካስታወስኩ መጽሐፍህ ውስጥም ይህንን ሀሳብ አንስተሀል እሰኪ ስለዚህ ሀብት ንገረን አዎ ! ብዙ ጊዜ በተለይ ስልጠና ስሰጥ “ሶማሌ ክልል ውስጥ ቢወጣ ኢትዮጵያን ሊጠቅም የሚችል ትልቅ ሀብት ምንድን ነው ?” ብዬ እጠይቃለሁ ሰዎች “ነዳጅ ነው” ይላሉ እኔ ደግሞ አልስማማም፡፡

ነዳጅ ቢወጣ ልንባላ ሁሉ እንችላለን፡፡ ሀገራዊ አልሆነም፡፡ ሶማሌ ክልል ውስጥ የሚገኘው ትልቁ ሀብት የሶማሌ ህዝብ ነው፡፡ የሶማሌዎች ጭንቅላት ነው ትልቁ ሀብት፡፡ በነገራችን ላይ ትግራይ ውስጥም፣ ጉራጌ ውስጥም፣ ኮንሶ ውስጥም፣ ሁሉም ቦታ ተመሳሳይ ነው፡፡

በየትኛውም አከባቢ ትልቁ ሀብት የዛ አከባቢ ህዝብ አእምሮ ነው ያልተቆፈረ ድንግል መሬት አለን ይባላል አእምሮአችንስ ምን ሰርቶ ያውቃል ? ገና ምንም አልተነካም እኮ የትም ብንሄድ መሬት ውስጥ ያለው ሳይሆን ሰው ጭንቅላት ውስጥ ያለው ነገር ነው ትልቁ ሀብት ፡፡ እሱን ትተን መሬት ውስጥ ያለው ሀብት ላይ ብናተኩር መልሚያችን ሳይሆን መጥፊያችን ሁሉ ሊሆን ይችላል ፡፡

በቅንነት ሌሎችም ሼር ያድርጉልኝ!!

http://t.me//Dr_MehretDebebe

Exit mobile version