Site icon ETHIO12.COM

እራሱን አስመጭ ነኝ በማለት ሲያጭበረብር የነበረው 16 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት ተወሰነበት

እራሱን አስመጭ ነኝ በማለትና በሀሰት በተዘጋጁ መንግስታዊ ሰነዶቸ በመገልገል ለተሸከርካሪው ሊብሬና ታርጋ ሊያወጣ ሲሞክር በቁጥጥር ስር የዋለው ተከሳሽ በ16 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራትና በ10 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ተወሰነበት ።

የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ታደለ ንጉሴ የተባለው ተከሳሽ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 23(2)(3)(ሀ)ን ፣ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥ 859/2006 አንቀፅ 167(1) እና የፌደራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀፅ 119(5) ላይ የተመለከቱትን በመተላለፍ በሌላ ግለሰብ ስም በጊዜያዊነት ለቱሪስት አገልግሎት ወደ ሃገር ውስጥ የገባ “ኪያ ስፖርቴጅ” ተሸከርካሪ ቀረጥና ታክስ ተከፍሎበት ወደ ሀገር ውስጥ እንደገባ በማስመሰል ታርጋና ሊብሬ ለማውጣት በራሱ ስም ”አስመጭ“ በሚል የተዘጋጀ ሀሰተኛ ዲክላሪሲዮን፤ የተከሳሽ ድርጅት ማህተም ያረፈበት በተከሳሹ ስም የተዘጋጀ ሀሰተኛ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ እንዲሁም ተሽከርካሪው በህጋዊ መልኩ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ አስፈላጊውን የጉምሩክ ፎርማሊቲ አሟልቶ ሰነድ የተበተነ መሆኑን የሚገልፅ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የአቃቄ ቃሊቲ ጉምሩክ ቅ/ፅ/ቤት የሚል የራስጌና የግርጌ ማህተም ያረፈበት ሀሰተኛ ደብዳቤ በማቅረብ ተከሳሹ ለተሸከርካሪው ሊብሬና ታርጋ ሊያወጣ ሲሞክር በቁጥጥር ስር የዋለ በመሆኑን ይገልጻል፡፡

ተከሳሹ በፈፀመው በሀሰት በተዘጋጀ መንግስታዊ ሰነዶች መገልገል ፣ ባለስልጣናቱ የሚጠቀሙበትን ሰነድ ወደ ሀሰት መለወጥና መጠቀም እንዲሁም ሀሰተኛና የተጭበረበሩ ደረሰኞችን መያዝና መጠቀም ወንጀል በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የኢኮኖሚ እና ታክስ ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶበታል ።

በከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት የቀረበው ተከሳሽ ታደለ ንጉሴ የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ በዐቃቤ ህግ ክስ ላይ የተጠቀሱትን ወንጀሎች አለመፈፀሙን በመግለጽ ክዶ ለችሎቱ አስረድቷል፡፡

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ተከሳሹ ወንጀሉን ስለመፈፀሙ የሚያስረዱ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ የድርጊቱን መፈፀም በበቂ ሁኔታ ያስረዳ በመሆኑ ተከሳሹ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሹም ክሱን በማስረጃ ደግፎ ማስተባበል አልቻለም ።

በዚህም መሰረት ችሎቱ የጥፋተኝነት ፍርድ በመስጠት ተከሳሽን ያርማል መሰል አጥፊዎችን ያስተምራል ሲል ተከሳሽ በ16 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራትና በ10 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ወስኖበታል ።

– federal general attorney

Exit mobile version