ETHIO12.COM

የወልቃይት ጠገዴ የሕጋዊነት ጥያቄ በአዲስ አበባ እየተመከረበት ነው

“የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝብ የመሰረተ ልማቶች ተጠቃሚ እንዲኾን የፌዴራል መንግሥት ኀላፊነቱን ይወጣ” የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የሰላምና ደኅንነት መምሪያ ኅላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ

የወልቃይት ጠገዴ የሰላም እና ልማት ማኅበር የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም እና ፍትሐዊ የመሰረተ ልማት ተጠቃሚ እንዲኾን ከአካባቢው ተወላጆች ጋር በአዲስ አበባ እየመከረ ነው።

የወልቃይት ጠገዴ አማራ የሰላም እና የልማት ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አሰፋ አዳነ እንዳሉት ማኅበሩ ያዘጋጀው ይህ መድረክ አካባቢው ያጣውን መሰረተ ልማት መፍትሔ ማግኘት በሚችልበትና ሕዝቡ ኹሉን አቀፍ ተጠቃሚ እንዲኾን ዓላማውን ያደረገ ነው።

የአማራ ሕዝብ በሰላማዊ መንገድ ሲጠየቅ የቆየውን የማንነት ጥያቄ በመስዋእትነቱ ቢያስመልስም በሕጋዊ መንገድ ጥያቄው ያልተመለሰ በመኾኑ የማንነት ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ ማኅበሩ ይሠራል ብለዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የሰላም እና ደኅንነት መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ እንዳሉት “ትላንት አይደለም በመንግሥት እውቅና ስብሰባ ማድረግ ይቅርና ለመኖር እንኳን የምንሳደድበት ነበር። በዘመነ ኢህአዴግ የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላት በርካታ ግፍ ሲደርስባቸው ነበር። ትህነግ እስከአሁን የወልቃይትን ሰቲት ሁመራ ዞን አልረገጠም፤ አሁንም ወደፊት ሕዝቡ ራሱን የሚጠብቅ በመኾኑ አይደረግም” ብለዋል።

ዞኑ በጀት የሌለው በመኾኑ ሕዝቡ ለበርካታ ችግር ተዳርጓል ያሉት ኮሎኔል ደመቀ የአማራ ክልል ለዞኑ የበጀት ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው የፌዴራል መንግሥት ምንም አይነት በጀት መድቦልን አያውቅም፤ በዚህ ምክንያት መሰረተ ልማት ለማሟላትና ለመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ለመክፍል መቸገረቸውን ነው የተናገሩት፡፡ የፌዴራል መንግሥት በጀት ሊመድብ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የፌደራል መንግሥት የአካባቢውን የመሰረተ ልማት ሌሎች ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሕዝቡ እንደሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለው መብት ሊከበርለት ይገባል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ:–አንዷለም መናን – (አሚኮ)

Exit mobile version