Site icon ETHIO12.COM

ከ42ቱ የእጩዎች ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌላቸውንና ፍላጎት ያላሳዩትን መሰረዛቸውን ፓርላማው አስታወቀ

“አንዳንዶቹ በዜግነት ኢትዮጵያዊ ያለመሆናቸው በመረጋገጡ እና አንዳንድ እጩዎች ደግሞ ፍላጎት እንደሌላቸው በመግለጻቸው ከ42ቱ የእጩዎች ዝርዝር ውስጥ እንዲሰረዙ ተደርጓል”— የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ከሰሞኑ ማህበራዊ ሚድያ ላይ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከቀረቡ 42 እጩ ኮሚሽነሮች ዝርዝር ውስጥ ያልተካተቱ ግለሰቦች ኮሚሽነር ሆነው የተሰየሙበት ምክንያት ምን ይሆን በሚል በርካታ መላ ምቶች ሲቀመጡ ነበር፣ አንዳንዶችም ይህን አስታከው ሂደቱ ከመጀመርያው ግልፅነት የጎደለው እንደሆነ አስተያየት ሰጥተዋል።

በዚህ ዙርያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራርያ ሰጥቷል።

ምክር ቤቱ በአጠቃላይ 632 ጥቆማዎች እንደተቀበለ የገለፀ ሲሆን ከነዚህ መካከልም 42 በአንደኛ ደረጃ እና 75 ያክሉን ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ምድብ ለማደራጀት ተችሏል ብሏል።

“በተለያዩ መንገዶች የተሰበሰቡ 2,890 አስተያየቶችን በማደራጀት የእጩዎችን ሁኔታ እንደገና ለማየት እንደ ግብአት ተጠቅመናል፡፡ በዚሁ መሰረት ብዝሃነትን፣ ጾታን እና እድሜን መሰረት ያደረገ ማስተካከያ ተደርጓል” ይላል የምክር ቤቱ መረጃ።

አክሎም “አንዳንዶቹ በዜግነት ኢትዮጵያዊ ያለመሆናቸው በመረጋገጡ እና አንዳንድ እጩዎች ደግሞ ፍላጎት እንደሌላቸው በመግለጻቸው ከ42ቱ የእጩዎች ዝርዝር እንዲሰረዙና በምትካቸውም በሁለተኛ ደረጃ ከተለዩት መካከል ወደ 42ቱ ተካተው በድጋሜ ለህዝብ አስተያየት በድረ ገጻችን ላይ ለህዝብ አስተያየት ይፋ ተደርገዋል፡፡ ከአስተያየቶቹ በኋላም 11ዱ ኮሚሽነሮች ተለይተው በኢፌዴሪ የህ/ተ/ም/ቤት ተሰይመዋል” ብሏል።

Exit mobile version