Site icon ETHIO12.COM

ብልጽግና – ጉባኤውን “ከፈተና ወደ ልዕልና” በሚል መሪ ሃሳብ ከነገ ጀምሮ ያካሂዳል

ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያን ከብተና ስጋት ታድጓል

መጋቢት 1 ቀን 2014 (ኢዜአ) የብልጽግና ፓርቲ መመስረት ኢትዮጵያን ከብተና ስጋት የታደገ መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ደራሽ በመሆን በተግባር ያረጋገጠ አሳታፊና ተራማጅ ፓርቲ መሆኑን በተግባር አረጋግጧል ሲሉም ተናግረዋል።

ብልጽግና ፓርቲ የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤውን “ከፈተና ወደ ልዕልና” በሚል መሪ ሃሳብ ከነገ ጀምሮ ለሶስት ቀናት ያካሂዳል።

በብልጽግና ፓርቲ የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ፤ ጉባኤውን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የብልጽግና ፓርቲ መመስረት ኢትዮጵያን ተደቅኖባት ከነበረው የመፍረስ ስጋት ታድጓል ብለዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ደራሽ በመሆን በተግባር ያረጋገጠ አሳታፊና ተራማጅ ፓርቲ መሆኑን በተግባር አረጋግጧል ሲሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ “አጋር” እየተባሉ አገር የመምራት ተሳትፎ እንዳይኖራቸው ተደርገው የቆዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን በማቀፍ አሳታፊነቱን በተግባር አሳይቷል ብለዋል።

የዴሞክራሲ እና የፍትህ ተቋማትን በማጠናከርና ሰብአዊ መብት እንዲከበር በማድረግም ብልጽግና የተሳካ ስራ አከናውኗል ብለዋል።

ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በመንግስት ስልጣን ውስጥ ተመድበው ተቋማትን እንዲመሩ በማድረግ በኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ ስለመፍጠሩም አንስተዋል።

ብልጽግና ከነገ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በሚያካሂደው ጉባኤ በአባላትና ደጋፊዎች ዘንድ የአስተሳሰብ አንድነትን ከማጠናከር በተጨማሪ ጠንካራ የፓርቲ መሪዎችን የመሰየም ስራ ያከናውናል ብለዋል።

ባለፉት አራት ዓመታት ፓርቲው ያለፈባቸው ፈተናዎችና ያስመዘገባቸው ስኬቶች ላይ በስፋት በመወያየት እንከኖችን ለማረምና መልካም ውጤቶችን ለማስቀጠል የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥም ጠቁመዋል።

Exit mobile version