Site icon ETHIO12.COM

አብን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እንደመረጠ ተደርጎ የሚሰራጭ መረጃ ሐሰት መኾኑን ገለጸ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ባለፉት ሁለት ቀናት የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን እንዲሁም ዛሬ ሦስተኛ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል።

የአብን የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጣሂር መሐመድ ጠቅላላ ጉባዔውን አስመልክቶ ለአሚኮ በሰጡት መግለጫ መሠረት ጠቅላላ ጉባዔው የፓርቲውን ድርጅታዊ ቁመና ገምግሟል፤ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችን በማንሳትም አቅጣጫ አስቀምጧል።

ዛሬ በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ዋንኛ ዓላማ አዲሱ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አዋጅ በሚደነግገው መሠረት ልዩ ልዩ አጀንዳዎችን መዳሰሱን አስታውቀዋል።

ፓርቲው እስካሁን የቆየባቸውን አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርቦ ውይይት ተደርጓል፣ ሰነዶችንም ተመልክቷል ነው ያሉት አቶ ጣሂር።

በጉባዔው የተዳሰሰው ሌላኛው አጀንዳ የለውጥ ጉዳይ ሲኾን የፓርቲው የለውጥ ሂደት ምን እንደሚመስል እና ቀጣይ መደረግ ባለባቸው ጉዳዮች ላይ የጠቅላላ ጉባዔ አባላቱ ሰፊ ውይይት አድርገውበታል ተብሏል። የደንብ ማሻሻያ ተደርጎ በጠቅላላ ጉባዔው በሙሉ ድምጽ መጽደቁንም የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ገልጸዋል።

አቶ ጣሂር እንዳሉት አብን ትናንት በነበረው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በተወሰነ መልኩ የአመራር ሽግሽግ ለሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች እልባት ሰጥቷል። ይሁን እንጂ የፓርቲውን መመሪያና ደንብ በውል ካለመረዳት በጠቅላላ ጉባዔው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እንደተመረጠ የሚናፈሰው ወሬ ትክክል አለመኾኑን አብራርተዋል።

በመግለጫው እንደተመላከተው ጠቅላላ ጉባዔው የሚመርጠው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ነው። የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የአገልግሎት ዘመን የሚጠናቀቅበት ጊዜ ደግሞ አልደረሰም። በመኾኑም በማዕከላዊ ኮሚቴው የተላለፈ ውሳኔ በጠቅላላ ጉባዔ እንደተሻረ ተደርጎ በተለይ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታር የሚንሸራሸረው መረጃ መሰረተ ቢስ እንደኾነ ነው አቶ ጣሂር የገለጹት።

የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው አብን እንደ ፓርቲ ከተመሰረተ አጭር ጊዜው ቢኾንም ሐሳቦቹን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሜዳ አቅርቦ በመሸጥ ተጽዕኖ የመፍጠር እንቅስቃሴው የጎላ ነው ብለዋል።

ፓርቲው የአማራ ድምጽነቱን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥልም አመላክተዋል።

የአማራ ሕዝብ ችግር እንዲፈታም ከሲቪል ድርጅቶች፣ ከመንግሥታዊ ተቋማት፣ ከምሁራን እና ከሌሎች ወንድም ሕዝብ ጋር አጋርነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው አቶ ጣሂር በመግለጫቸው ያነሱት።

ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ – (አሚኮ)

Exit mobile version