Site icon ETHIO12.COM

ስለ ወክልና መሰረታዊ ጉዳዮች በኢትዮጵያ ህግ

መግቢያ

ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳዮቻቸውን በራሳቸው መፈጸም ወይም ማከናወን የማይችሉባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ይህም ሲሆን ሌሎች ሰዎች ጉዳያቸውን እንደነሱ በመሆን እንዲፈፅሙላቸው ሲያደርጉ ይስተዋለል፡፡ ጉዳዮቹ በተለይ ለምሳሌ ማህበራዊ(ለቅሶ መድረስ፣የተመመ ሰው መጠየቅ ወዘተ) ሳይሆን ህጋዊ ጉዳዮች ማድረግ( ሽያጭ ወይም ግዢ መፈፀም) ሲሆን በህግ የሚያስከተሉት እራሱን የቻለ ህጋዊ ውጤት ስለሚኖረው ስራዎችን የማከናወኑ ሀላፊነት ህግን መሰረት ባደረገ ስምምነት ላይ የተመሰረት መሆን ይኖርበታል፡፡ስለሆነም ይህንን ስለሌላ ሰው ስራን የመስራት ሀላፊነት እና ግንኙነት የሚያስተዳድር ህግ እስፈላጊ ሆኖ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሰረት ይህንን ግንኙነት የሚገዛ ህግ በኢትዮጵያ ውክልናን የተመለከቱ ድንጋጌዎች በፍትህ ብሄር ህጉ 4ኛ መፅሀፍ አንቀፅ 14 ስር ስለ እንደራሴነት በጠቅላላ ክፍል እና ስለወኪልነት በሁለት አካቶ ይገኛል፡፡ ይሁንና የፍትሀ ብሄር ህጉ በእንደራሴነት እና በወኪልነት መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ ያብራራ ሆኖ አይታይም፡፡ በመሆንም እንደራሴነት እና ወኪልነት በህግ ባለሞያዎች ዘንድ በተለዋዋጭነት( interchangeably) በጥቅም ላይ ሲውሉ ይስተዋላል፡፡

በፍትሀ ብሄር ህጉ ቁጥር 2179 ስር እንደተደነገገው የሌላ ሰው እንደራሴ በመሆን ስራዎችን የመፈፀም ስልጣን የሚመነጨው ከህግ ወይም ከውል ነው፡፡ ለአካለ መጠን ላልደረሰ ልጅ ሞግዚት መሆን ወይም ንብረት ለማስተዳደር በሕግ የተፈቀደላቸው ጠባቂ ወይም አሳደሪ የመሆን የእንደራሴነት ስልጣን ለምሳሌ ከህግ የሚገኝ የውክልና ስልጣን ነው ፡፡ በሌላ በኩል አንድን የህግ ጉዳይ ጠበቃ ፍርድ ቤት ይዞ እንዲከራከርለት ባለጉዳይ ለጠበቃ የሚሰጠው የእንደራሴነት ስልጣን ደግሞ ከውል የሚገኝ የውክልና ስልጣን መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

የእንደራሴነት ስልጣን ወሰንን በተመለከተ የእንደራሴነት ሥልጣን የተገኘው በውል መሰረት የሆነ እንደሆነ ስልጣኑ የሚወሰነው በተዋዋዮቹ ስምምነት ነው፡፡ ይህም እንደራሴው ስራ እንዲሰራለት ሀላፊነት የሰጠው ሰው እንዲያከናውንለት ከጠየቀው ጉዳይ ወይም እንዲሰራ ከተስማሙት ስራ ውጪ መስራት አይችልም ማለት ነው፡፡ እንዲሁም እንደራሴው የተሰጠውን ሥልጣን ሦስተኛ ወገን ለሆነ ሰው አስታውቆ እንደሆነ በሦስተኛው ሰው ላይ ሥልጣኑ የሚፀናው ባስታወቀው ማስታወቂያ መሰረት ይሆናል፡፡ይህ ሲሆን የእንደራሴነት ስልጣን የሚተረጎመው ሳይስፋፋ በጠባቡ መሆን እንዳለበት የፍትሀ ብሄር ህጉ ይደነግጋል፡፡ በመቀጠል በፍትሀ ብሄር ህጉ ስለወኪልነት የተካተቱ መሰረታዊ ጉዳዮችን እንመለከታለን፡፡

– የውክልና ትርጉም


ውክልና ማለት ተወካይ የተባለ አንድ ሰው ወካይ ለተባለው ሰው እንደራሴ ሆኖ አንድ ወይም ብዙ ህጋዊ ሥራዎች በወካዩ ሥም ለማከናወን ግዴታ የሚገባበት ውል ማለት ነው”(የፍትሀ ብሄር ህግ ቁጥር 2199)፡፡ ከትርጉሙ ለመረዳት እንደሚቻለው ውክልና ከውል የሚመነጭ የእንደራሴነት ስልጣን ሲሆን ውክልና የሚደረገው በወካይና በተወካይ መካከል በሚደረግ ስምምነት ነው፡፡ በተጨማሪም በውክልናው የሚከናወኑት ስራዎች ህጋዊ መሆን እንዳለባቸው መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ህጋዊ ባልሆኑ ጉዳዮች ለምሳሌ ወንጀል ለመፈፀም የሚደረግ የውክልና ስምምነት ተቀባይነት የለውም ማለት ነው፡፡

– የውክልና አስፈላጊነት

አንድ ሰው አንዳንድ ተግባሮችን በራሱ ከማድረግ ይልቅ ሌላን ሰው በመወከል ተግባሮቹ እንዲከናወኑለት ሊፈልግ ይችላል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የጊዜ ጥበት፣ የቦታ ርቀት ወይም የሁኔታዎች አለመመቻቸት፣ የእውቀት ወይም የክህሎት አለመኖርና የችሎታ ማነስ ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ ሌሎችም በምክንያትነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

 የውክልና ውል አመሰራረት

ውክልና በግልፅ (ማለትም ወካይ የውክልና ስልጣኑን ለተወካይ እንደሰጠው በግልፅ በማሳወቅ) ወይም በዝምታ ሊሰጥ ይችላል (expressly or impliedly) ፡፡ ተወካዩም ሊፈፅመው የሚገባው የሥራ ተግባር ስለአፈፃፀሙ በአንዳንድ ህጋዊ ፎርም ውስጥ እንዲገባ የሚያስፈልገው ሲሆን ውክልናው ለተወካዩ ሊሰጠው የሚገባው ይኸው ሕግ በሚያዘው ፎርም መሠረት ነው፡፡ ለምሳሌ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል በፅሁፍ መሆን ካለበት ወኪሉ ሽያጩን እንዲያከናውንለት ወካይ የሚሰጠው የውክልና ሥልጣን ውል ከወዲሁ በፅሁፍ መሆን ይኖርበታል፡፡

በሌላ በኩል ውክልናውን የሚቀበለው ተወካይ መቀበሉን በግልፅ ወይም በዝምታ ሊፈጽም ይችላል፡፡ ውክልናውን መቀበል የማይፈልግ ከሆነ ደግሞ በግልፅ እንደማይቀበል በመግለፅ ከኃላፊነት እራሱን ማግለል ይችላል፡፡ ስለሆነም ተወካይ ውክልናውን የማይቀበል መሆኑን ከወዲሁ በግልፅ ካላስታወቀ በስተቀር የተወከለበት ነገር ከሚያካሂደው ሥራ ጋር ግንኙነት ያለው ጉዳይ መሆኑ በግለፅ የታወቀ ከሆነ፣ ወይም ከሙያ ሥራው አመራር ጋር የሚመሣሠል ጉዳይ ከሆነ፣ ወይም ይህንን የመሠለውን ጉዳይ ለመሥራት ፍቃደኛ ለመሆኑ በአደባባይ ገልጾ ሀሳብ በማቅረብ አስታውቆ እንደሆነ ውክልናውን እንደተቀበለ ይቆጠራል።

በመርህ ደረጃ አንድ ሰው ለቀረበለት ውል ምላሸ ሳይሰጥ ዝም ቢል የቀረበለትን የውል ሀሳብ እንደተቀበለ እንደማያስቆጥርበት (silence doesn’t amount to acceptance) የፍትሀ ብሄር ሕግ ይደነግጋል(ፍ/ብ/ህ/ቁ.1682)፡፡ ነገር ግን የውክልና ጉዳይ በልዩ ሁኔታ የሚወሠድ በመሆኑ አንድ ሰው በቀረበለት የውክልና ውል ላይ ግልፅ የሆነ ያለመቀበል ሃሣብ እስካላቀረበ ድረስ ዝምታው የውክልናውን ውል እንደተቀበለ የሚያስቆጥርበት መሆኑን የፍ/ብ/ህ//ቁ 2201(2) ደንግጓል፡፡ በዚህ ሁኔታ የውክልናው ውል ውክልናውን ባቀረበውና በተቀበለው ሰው መካከል ይመሠረታል ማለት ነው፡፡ ውክልናው የሚሰጠው ለብዙ ሰዎች ከሆነ ግን የውክልና ስልጣኑን ሁሉም ባንድነት መቀበላቸው ካልተረጋገጠ በቀር ውክልናው እንደጸና አይቆጠርም። በመሆኑም ውክልና ከላይ በተጠቀሱት ሁኔታዎች ይቋቋማል ማለት ነው፡፡

– የውክልና ወሰን

ውክልናው ሲቋቋም የውክልናው ወሰን እስከምን ድረስ ነው የሚለው ደግሞ በፍትሃ ብሄር ህጉ ቁጥር 2202 ላይ ተቀምጧል። በዚህም መሠረት የውክልናው ወሰን በውሉ ላይ በግልፅ ተጠቅሶ ካልተቀመጠ በስተቀር ለውክልናው የሚሰጠው ወሰን እንደ ጉዳዩ አይነት ይሆናል። ወካዩ የውክልናውን ወሰን በውክልናው ውል ላይ በግልፅ ካስቀመጠ ደግሞ ወሰኑ በግልጽ በተቀመጠው መሠረት ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ውክልናው ለአንድ ልዩ ጉዳይ ወይም ለእያንዳንዱ ጉዳዮች ወይም ለወካዩ ጉዳዮች ሁሉ ጠቅላላ ውክልና ሊሆን ይችላል (ፍ/ብ/ህ/ቁ 2202 (2))። ይህ ማለት አንድ ሰው ለአንድ ለተወሠነ ጉዳይ ብቻ ወይንም ለተለያዩ ከአንድ በላይ ለሆኑ ጉዳዮች ወይንም ለሁሉም ጉዳዮቹ ውክልና ሊሰጥ ይችላል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ከላይ በተጠቀሰው የውክልና ወሰን መሠረት ውክልናን ጠቅላላ ውክልናና ልዩ ውክልና ተብሎ ይከፈላል ሊከፈል ይችላል፡፡

– ጠቅላላ ውክልና

ጠቅላላ ውክልና ማለት በጠቅላላ አነጋገር የተደረገ ውክልና ሲሆን የአስተዳደር ሥራዎች ለመፈፀም ብቻ ለተወካዩ የሚሰጥ ውክልና ነው፡፡ ይህ ማለት ወካይ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በዝርዝር ሳይገለፅ እንዲሁ በጠቅላላ አነጋገር ወክየዋለሁ የሚል ከሆነ ተወካዩ ከአስተዳደር ሥራዎች ውጭ የመሥራት ሥልጣን አይኖረውም ማለት ነው። ይህም የሚሆነው ተወካዩ የተወከለበት ነገር ከሚያካሂደው ሥራ ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው መረዳት ባልተቻለበት ጊዜ ነው፡፡ ተወካዩ የተወከለበት ነገር ከሚያካሂደው ነገር ግንኙነት ካለው ግን ተወካዩ ከአስተዳደር ሥራዎች ይልቅ ከራሱ የዕለት ስራዎች ጋር የሚገናኘውን ሥራ ነው መስራት ያለበት። ስለዚህ ተወካዩ የሚተገብረው ሥራ ወካዩ ከወከለው ጉዳይ ጋር ያለውን ግንኙነት መረዳት ካልተቻለ ተወካዩ በተሠጠው ሥልጣን መሥራት የሚችለው የአስተዳደር ስራዎችን ብቻ ይሆናል፡፡
የአስተዳደር ሥራ ተብለው በፍትሀ ብሄር ህጉ የተቀመጡት ሥራዎች የሚከተሉት ናቸው( ፍ/ብ/ህ/ቁ. 2204)፡፡

 የወካዩን ሀብት የማሰቀመጥ፣ የመጠበቅ ሥራ
 ከሶስት አመት ለማያልፍ ዘመን የማከራየት
 በብድር የተሰጠውን ሀብት የመሰብሰብ
 ከሀብቱ የሚመጣውን ገቢ ተቀብሎ የማስቀመጥና
 ለተከፈሉ ዕዳዎች ደረሰኝ የመሥጠት ሥራዎች ናቸው።

በመሆኑም በጠቅላላ ውክልና የውክልና ሥልጣን የተሰጠው ተወካይ ከላይ ከተዘረዘሩት ሥራዎች ውጭ የመሥራት ወይንም የመከወን ሥልጣን የለውም። በዚህ ጉዳይ ብዙ ጊዜ በህብረተሰቡ ዘንድ የተሳሳተ ግንዛቤ ይታያል ፡፡ይህም ስሙ ጠቅላላ ውክልና ስለሚል ብቻ ለተወካይ አጠቃላይ የወካዩን ተግባሮች የመከወን ሥልጣን የሰጠው አድርጐ የመረዳት ሁኔታ አለ፡፡ በዚህም ምክንያት ወካዮች ሁሉንም ሥራዎችን መወከል ሲፈልጉ ጠቅላላ ውክልና ወይም ሙሉ ውክልና ብለው የውክልና ስልጣን የመስጠት ሁኔታዎች ያጋጥማሉ። ይሁንና ጠቅላላ ውክልና ግን ሰዎች በሚያስቡት ወይም በሚገነዘቡት መልኩ ሳይሆን ህጉ ባስቀመጠው መሠረት የአስተዳደር ስራዎችን ብቻ የሚያካትት ነው።

 ልዩ ውክልና

ልዩ ውክልና ማለት አንድ ሰው ከአስተዳደር ሥራ ውጭ ያሉ ሥራዎችን በወኪሉ ለማሠራት የሚያስችለው የውክልና አይነት ነው፡፡ ስለሆነም በልዩ ውክልና የውክልና ስልጣን የተሰጠው ተወካይ ተለይተው በዝርዝር የተመለከቱ ጉዳዮችንና እንደ ጉዳዩ አይነትና እንደ ልማድ አሰራር ከጉዳዩ ጋር ተከታታይነትና ተመሣሣይነት ያላቸው ነገሮችን ማከናወን ይችላል ማለት ነው( ፍ/ብ/ህ/ቁ 2206/1/)፡፡ ከዚህ ባሻገር አንድ ተወካይ ልዩ የውክልና ሥልጣን ከሌለው በስተቀር ሊፈጽማቸው የማይችላቸው ተግባራቶች አሉ፡፡ እነሱም፡-
• የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን መሸጥ ወይም አሲዞ መበደር
• ካፒታሎችን በአንድ ማህበር ውስጥ ማስገባት
• የሀዋላ ሰነዶችን መፈረም (sign bill of exchange)
• መታረቅ
• ለመታረቅ ውል መግባት
• ስጦታ ማድረግ ወይም
• በአንድ ጉዳይ በፍርድ ቤት ቀርቦ መከራከር ናቸው።

በሌላ በኩል በፍትሀ ብሄር ህጉ ከተካተቱ መሰረታዊ ጉዳዮች ውስጥ የተወካይ እና የወካይ ግዴታዎች ይገኙበታል፡፡እነሱም፡-

 የተወካይ ግዴታዎች
 ጥብቅ የሆነ ቅንልቦና መኖር /ቅን የመሆን ግዴታ/
 ታማኝነት
 ሚስጥር ጠባቂነት /በውክልና ምክንያት ያገኘውን ሚስጥር የመጠበቅ ግዴታ/
 የሂሳብ አያያዝና ሂሣብ የማቅረብ ግዴታ
 ታታሪነት /ትጉህ የመሆን ግዴታ/
 ስራን በራስ የመፈፀም ግዴታ/obligation to act personally/

 የወካይ ግዴታዎች
 ለተወካዩ ደሞዝ /የድካም ዋጋ/የመክፈል ግዴታ/ስምምነት ወይም ልማዳዊ አሠራር ካለ
 ወጭ የመሥጠትና የማወራረድ ግዴታ
 ተወካይን ከግዴታ ነፃ ማውጣት(ተወካይ ስለወካይ የውል ግዴታ ገብቶ ከሆነ ውሉን በመፈፀም ተወካይን በግዴታ ማውጣት)
 ለተወካይ ኪሣራ መክፈል (የወካይን ስራ ሲሰራ ከተወካይ ጥፋት ውጪ ጉዳት ከደረሰበት ወካይ የካሣ ክፍያ የመክፈል ግዴታ አለበት)

 የውክልና ስልጣንን አላግባብ መጠቀም

አንድ ተወካይ በተሰጠው የውክልና ስልጣን ሊሰራው ከሚገባው ተግባር ባሻጋር ሌላ ወካዩ እንዲሰራ የማይፈልገውን ተግባር ቢያከናውን ተወካዩ የተሰጠውን የውክልና ሥልጣን ያለአግባብ ተጠቅሟል ሊባል ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ተወካዩ የተጣለበትን አደራ በአግባቡ አለመወጣቱን ያሣያል፡፡ የተሰራውን ስራ በተመለከተ ደግሞ ወካዩ ተወካዩ የፈፀመውን ተግባር ማፅደቅ ወይም ውድቅ ማድረግ ይችላል ፡፡ እንዲሁም ተወካይ ጊዜው ባለፈበት የውክልና ሥልጣን የተገለገለ ወይም በተሻረ ውክልናው የሰራ እንደሆነ የተሰራውን ስራ ወካይ ሊያፀድቀው ወይንም ሊሽረው ይችላል( ፍትሃብሄር ሕግ ቀ. 2190/2/ ) ፡፡

 ስለውክልና ሥልጣን መቅረት ወይም መቋረጥ

የውክልና ሥልጣን ከዚህ በታች በተቀመጡት ሶስት ምክንያቶች መሠረት ሊቀር ወይንም ሊቋረጥ ይችላል፡፡ እነሱም ፡-

  1. የውክልናው ሥልጣን በወካዩ መሻር
  2. የተወካዩ የውክልና ስልጣኑን መተው
  3. የወካዩ ወይም የተወካዩ መሞት ፣ከአካባቢ መጥፋት ፣ለሥራት ችሎታ ማጣት ወይም በንግድ ኪሣራ ላይ መውደቅ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ውክልና በሰዎች የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ውስጥ የሚስተዋል ክንውን በመሆኑና የውክልና ህግ በኢትዮጵያ በብዛት የሚሰራበት ህግ በመሆኑ ሰዎች ስለውክልና ጠቅላላ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እና ጉዳዮች በተወካይ እንዲፈጸሙላቸው ሲያደርጉ ወክልና ከመስጠታቸው በፊት የውክልናን ውጤት ማወቅ ጠቃሚ ነው፡፡

በንቃተ ህግ፣ ትምህርተና ስልጠና ዳይሬክቶሬት

Ministry of justice

Exit mobile version