Site icon ETHIO12.COM

ኦሮሚያ – ከ7 ሺህ በላይ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን መዉሰዱን አስታወቀ

የኦሮሚያ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰዉ ሃበት ልማት ቢሮ የመልካም አስተዳደር ችግር በፈጠሩና የሥነ ምግባር ጉድለት በታየባቸዉ ከ7 ሺህ በላይ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን መዉሰዱን አስታወቀ።

ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ሕብረተሰቡ የሚያነሳቸዉን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍ በትኩረት እየሠራ መሆኑንም አስታዉቋል።

ቢሮዉ በአገልግሎት አሠጣጥ ላይ ያተኮረ ስልጠና ለቡራዩ ከተማ አስተዳደር አመራሮችና የመንግስት ሠራተኞች ሰጥቷል።

የኦሮሚያ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰዉ ሃብት ልማት ቢሮ በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቶች ላይ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ በቴክኖሎጂ የታገዘ የሕዝብ አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ተግባራዊ በማድረግ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማቃለል ላይ ከሚገኙ የክልሉ ከተሞች መካከል የቡራዩ ከተማ አስተዳደር አንዱ ነዉ።

የከተማዉ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰዉ ሃብት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፈካታ ገመዳ ከአገልግሎት አሰጣጥ መጓተት ጋር ተያይዞ የከተማዋ ነዋሪዎች የሚያነሷቸዉን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍ በከተማዉ ከንቲባ ጽ/ቤት: ማዘጋጃ ቤት: የመሬት አስተዳደርና ሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች ዉስጥ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ አገልግሎት እየተሰጠ ነዉ ብለዋል።

ቴክኖሎጂዉን በመጠቀም ብልሹ አሰራሮችን: ሙስናን: የባለ ጉዳዮች መመላለስንና የሠራተኞች የስራ መግቢያና መዉጫ ሰአት መቆጣጠር ችለናል ያሉት ኃላፊዉ ለ2 ቀናት ለከተማዉ አመራሮችና የመንግስት ሠራተኞች የሚሰጠዉ ስልጠና የአገልጋዮችን ግንዛቤ ከማሻሻል ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።

ለአመራሮቹ የአመራርነት ስልጠና የሠጡት የፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ምሁሩ ዶ/ር ከበደ ገነቲ ስልጠናዉ የአገልግሎት አሠጣጥ ሂደትን በማዘመን የተገልጋዮችን እርካታ የሚጨምር መሆኑን ገልጸዋል።

ታታሪ አገልጋዮችን ማበረታታትና የሥነ ምግባር ጉድለት የታየባቸዉን ማረም ሕዝቡ የሚያነሳቸዉን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ከመቅረፍ አንጻር ጉልህ ሚና እንዳለዉ የተናገሩት ምሁሩ አመራሩና ሲቪል ሰርቫንቱ ከምንም በላይ ሕዝቡን በቅንነት በማገልገል ተገልጋዮችን ሊያረካ ይገባል ብለዋል።

በስልጠናዉ ላይ የተሳተፉ አንዳንድ የቡራዩ ከተማ አስተዳደር አመራሮችና የመንግስት ሠራተኞችም ስልጠናዉ ወቅታዊ መሆኑን በመግለጽ ሕዝቡ የሚያነሳቸዉን ቅሬታዎች ለመቅረፍ ዝግጁ መሆናቸዉን ገልጸዋል።

የቡራዩ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጀግናዉ ግዛዉ ስልጠናዉ በከተማዉ የተጀመሩ ሪፎርሞችንና መልካም ተሞክሮዎችን ይበልጥ ከማጠናከር ረገድ ትልቅ ድርሻ አለዉ ብለዋል።

የኦሮሚያ ፐብሊክ ሰርቪስና ሰዉ ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዳምጦ ገመቹ በበኩላቸዉ ቢሮዉ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑን በመግለጽ በቡራዩ ከተማ የተጀመረዉ ስልጠና የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።

የቡራዩ ከተማ አስተዳደር ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግ የጀመረዉ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ያሉት ኃላፊዉ ተሞክሮዉ በሌሎች ከተሞችና ዞኖች ሊስፋፋ ይገባል ብለዋል።

አንዳንድ አመራሮችና የመንግስት ሠራተኞች በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተግዳሮት እንደሚፈጥሩ: ጥቅማጥቅም እንደሚቀበሉና ተገልጋዮችን እንደሚያንገላቱ የተናገሩት የቢሮዉ ኃላፊ የመንግስትን አገልግሎት በገንዘብ ለመሸጥ በሞከሩ: በሙስና በተጠረጠሩና የሥነ ምግባር ጉድለት በፈጸሙ ከ7 ሺህ በላይ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ ከስራ ማሰናበትን ጨምሮ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዳቸዉን ጠቅሰዋል።

የሠራተኛዉን ክህሎትና አቅም ለማሻሻል ከሚሰራዉ ስራ ጎን ለጎን ሕዝብን በሚያንገላቱና የመልካም አስተዳደር ችግር በሚፈጥሩ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ እየተወሰደ ያለዉ እርምጃም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ወንድማገኝ አሰፋ OBN

Exit mobile version