Site icon ETHIO12.COM

“በኦሮሚያ በርካታ ታጣቂዎች እጃቸውን እየሰጡ ነው”

መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን በመጋዘን በመከዘን፣ በማሸሽ፣ በኮንትሮባንድ ወደውጪ ሀገር ለማውጣት የአቅርቦት እጥረት ለመፍጠር በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃዎችን መውሰድ እንደተጀመረና ከነዚህ አካላት ጋር ትስስር ያላቸውና በመንግሥት ተቋማት በሚሠሩትም ላይ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑ ተነግሯል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተደራጀ የሕግ ማስከበር ሥራ እየሠራ መሆኑን የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ የአገሪቱ መንግሥት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተደራጀ የሕግ ማስከበር ሥራ እየሠራ በመሆኑ አብዛኛው የሀገራችን ክፍል አንጻራዊ ሰላም እየሰፈነ ይገኛል ብለዋል።

እየተሠሩ ባሉ የሕግ ማስከበር ሥራዎች በመላው ኦሮሚያ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እና ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ለመፍጠር የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት እያሳየ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው፡፡ ይህንን በማጎልበት ሁሉንም አካባቢዎች ከሸኔ የሽፍታ ኃይል የማፅዳት ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በአንዳንድ ዞኖች ወረዳዎችና አጎራባች ክልሎች ወሰን አካባቢ የሚንቀሳቀሰው የሸኔ ኃይል እያደረሰ ያለውን የንብረት ዝርፊያ፣ ውድመት፣ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር እና መፈናቀልን የክልልና የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች በተቀናጀ እና ሕብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ከፍተኛ የተባለ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

እስካሁን በተደረገ ኦፕሬሽንም በርካታ የሸኔ አባላት መደምሰሳቸውን እና የስንቅና የመሣሪያ አቅርቦት ሆነው ይሠሩ የነበሩ አካባቢዎችም ከሸኔ እየጸዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተወሰደው እርምጃ ህብረተሰቡ ያሳየው አጋርነት በጣም የሚያስመሰግን እንደሆነ የገለጹት ኃላፊ ሚኒስትሩ፤ ተታለው ወደዚህ አስጸያፊ ተግባር የገቡ የሽፍታው ቡድን አባላት በአባ ገዳዎችና በሀገር ሽማግሌዎች ምክር በርካታ ታጣቂዎች እጃቸውን እየሰጡ ነው ብለዋል፡፡

መንግሥት በመላ ሀገሪቱ ሕግና ሥርዓት ለማስከበር እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል አንጻራዊ ሰላም እየሰፈነ ቢገኝም፤ የተለያዩ መዋጮዎችን በግዴታ የሚያስከፍሉ፣ ሕፃናትን በማፈን መደራደሪያ የሚያደርጉ፣ ሴቶችን አስገድደው የሚደፍሩ፣ የመንግሥትን ሥራ የሚያደናቅፉ፣ በንጹሃን ዜጎችና በጸጥታ ኃይሎች ላይ ድንገተኛ ጥቃት የሚፈጽሙ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች እየተለመዱ መጥተዋል፡፡ በዚህም ሕብረተሰቡ እየተንገላታ በመሆኑ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በመንግሥት የተደራጀ ሕግ የማስከበር የሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ እንደገባ ገልጸዋል፡፡

በተያያዘ የሕወሓት ታጣቂዎች በጉልበት ከያዟቸው የአፋርና የአማራ አካባቢዎች በመውጣት ህብረተሰቡ ከቀየው ሳይፈናቀል ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኝ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የጠቀሱት ዶክተር ለገሰ፤ መንግሥት በገባው ቃል መሠረት ውሳኔው ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ የሰብዓዊ ዕርዳታው በየብስና በአየር ትራንስፖርት እንዲጓጓዝ አፋጣኝ ምላሽ ሰጥቷል ብለዋል፡፡

በዚህም መሠረት የዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማት መድኃኒቶችን፣ የህክምና ቁሳቁሶችን አልሚ ምግቦችንና ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎችን በተመቻቸላቸው የየዕለት የአየር ትራንስፖርት በቻሉት መጠን ማጓጓዝ ጀምረዋል ብለዋል።

በየብስ ትራንስፖርትም በአብአላ መንገድ በዓለም ምግብ ድርጅት አቅራቢነት ዕርዳታዎችን ማጓጓዝ እንደተጀመረና በመጀመሪያው ዙር በዓለም ምግብ ድርጅት ዕርዳታ አቅራቢነት ከተላኩት 20 ከባድ ተሽከርካሪዎች 13 ያህሉ መቀሌ እንደገቡ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

የአፋር ሕዝብና መንግሥት የሕወሓት ታጣቂዎች የሚያደርሱትን ግፍና ግድያ ተቋቁመው በትግራይ ክልል ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ያሉ እህትና ወንድሞቹን ለመታደግ ያሳየው ትብብርና በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ያሳዩት ዝግጁነት በእጅጉ የሚያስመሰግናቸው ነው ብለዋል፡፡

የሕወሓት ታጣቂዎች በጉልበት ከያዟቸው አካባቢዎች አለመውጣታቸውን ተከትሎ ለሰብዓዊነት የቆመ ሁሉ ግፊት እንዲያደረግባቸው መንግሥት ጥሪውን አቅርቧል፡፡

አገልግሎቱ የኢኮኖሚ መረጋጋትና የዋጋ ንረትን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫም መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ዕቅድ አውጥቶ ወደሥራ መግባቱ ተጠቅሷል፡፡ 

ለዋጋ ንረትና ግሽበት ዓለም አቀፍ የሆኑና ሀገራዊ የሆኑ ምክንያቶች እንዳሉት ተጠቅሷል፡፡ የዓለም አቀፍ ሸቀጦች ዋጋ መናር፤ በሸማቾችና በአምራቾቾ መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት አለመኖር እና ከመሠረታዊ ፍላጎታችን ጋር የሚመጣጠን ምርትና ምርታማነት አለመኖር ለዋጋ ንረትና ለኑሮ ውድነቱ ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው ተብለዋል፡፡ 

እነዚህን ችግሮች የወለዱትን የዋጋ መናርና የኑሮ ውድነት ህብረተሰቡን ጭምር በማሳተፍ መንግሥት በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ለመፍታት ዕቅድ አውጥቶ ወደ ሥራ እንደገባ መግለጫው አትቷል፡፡

በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን አሻጥር ለመቅረፍ ከተለያዩ ሕግ አስከባሪ አካላት እና ተቋማት የተውጣጣ ግብረ ኃይል ተደራጅቶ በየደረጃው ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ሕግና ሥርዓት የማስከበር ሥራ እንደተጀመረ ዶክትር ለገሰ ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ለዋጋ መናር አስተዋፅዖ አድርገዋል በተባሉ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰድ ተጀምሯል፡፡ 

መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን በመጋዘን በመከዘን፣ በማሸሽ፣ በኮንትሮባንድ ወደውጪ ሀገር ለማውጣት የአቅርቦት እጥረት ለመፍጠር በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃዎችን መውሰድ እንደተጀመረና ከነዚህ አካላት ጋር ትስስር ያላቸውና በመንግሥት ተቋማት በሚሠሩትም ላይ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ይህ ቁጥጥርና ሕግና ሥርዓት የማስከበር ጉዳይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ቀደም ሲል የተፈጸሙ ግዢዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሀገር ውስጥ በፍጥነት እንዲጓጓዙ እና ከፍላጎቱ ጋር ሊመጣጠን የሚችል ተጨማሪ ፈጣን ግዢዎች እንዲፈጸሙ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ውብሸት ሰንደቁ 

አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 2014 ዓ.ም

Exit mobile version