ጠላት አርፎ እንደማይተኛ ታውቆ ለየትኛውም ተጋድሎ ራስን ማዘጋጀት እንደሚገባ የአማራ ክልል መንግሥት አስታወቀ።

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ግዛቸው ሙሉነህ በውቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም የአማራ ክልል የፀጥታ ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ተወያይቶ አቅጣጫ ማስቀመጡን ገልፀዋል። ውስጣዊ አንድነትን ለማጠናከር እና የውጭ ጠላትን ለመመከት የሕግ ማስከበር ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። የሕግ ማስከበር ሥራው ውጤት የታየበት መሆኑን የፀጥታ ምክር ቤቱ መገምገሙንና ጉድለቶችንም መመልከቱን ነው የተናገሩት።

እየተወሰደ ባለው የሕግ ማስከበር ሥራ ክልሉ ወደ ሰላም መምጣቱንም አንስተዋል። የሽብር ቡድኖች ዋነኛ ዓላማ ሕዝብ መንግሥትን እንዲጠራጠር ማድረግ እንደነበርም ገልጸዋል። ጠላት የአማራ ክልል የትርምስ ቀጣና የማድረግ ዓላማ ይዞ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል። የፀጥታ ምክር ቤቱ የጠላትን እንቅስቃሴ መገምገሙንም አስታውቀዋል። የአማራ ክልል በተፈናቃዮች እንዲሞላ ጠላት እንደሚሠራም ገልጸዋል። ጠላት ዜጎችን በግፍ ከመግደል ባለፈ በልዩ ልዩ ሰበቦች ሁከትና ብጥብጥ የመፍጠር ተግባር ለመሥራት እየጣረ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዜጎች ላይ በደረሰው ጉዳት የክልሉ መንግሥት ማዘኑን የገለፁት አቶ ግዛቸው ጠላት አሁንም ለሌላ ብጥብጥ ጉዳዮን ለመጠቀም እየሠራ ነው ብለዋል። የውጭ ጠላቶች ላይ አተኩሮ መሥራት ይገባልም ነው ያሉት። የውስጥ አንድነት እስከሌለ ድረስ ለጠላት እንጋለጣለን ያሉት ኃላፊው በብስለትና ኃይል በማሰባሰብ በጠላት ላይ በጋራ መዝመት እንደሚገባ ነው የገለጹት። ከኋላ የሚወጋ ኃይል እንዳይኖር የውስጥ ጠላትን እያፅዱ ከውጭ ጠላት ጋር መታገል ይገባል ነው ያሉት።

የክልሉ ሕዝብና መንግሥት ለሰላም የቆመ ነው ያሉት አቶ ግዛቸው ሕግና ሥርዓት የማስከበር ሥራ የአንድ ሠሞን ሳይሆን ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የፀጥታ ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል ብለዋል።

አሸባሪዎችን መልክ ለማስያዝና አንኳር ጥያቄዎች እንዲመለሱ ሕግና ሥርዓት መከበር እንዳለበትም አስታውቀዋል።

የፀጥታ ምክር ቤቱ አሁናዊ የውጭ ጠላቶችን እንቅስቃሴ በመገምገም አቅጣጫ አስቀምጧልም ብለዋል። ክረምቱን መነሻ በማድረግ የጠላት እንቅስቃሴ መኖሩንም ገልጸዋል። የጠላትን እንቅስቃሴ ለመመከትም በሁሉም ዘርፍ መዘጋጀት እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል ነው ያሉት። የፖለቲካ ሁኔታው በሚገባ መሥራት እንዳለበት መግባባት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል። ለሕዝቡ መረጃን ቶሎ ቶሎ ማድረስ እንደሚገባም አቅጣጫ ተቀምጧል ነው ያሉት።

ዜጎችን በሚጨፈጭፉ የሽብር ቡድኖች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም አንስተዋል። የዜጎችን መጨፍጨፍ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በአማራ ክልል የበለጠ ብጥብጥ ለመፍጠር የሚጥሩ ጠላቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል። ጠላት አርፎ እንደማይተኛ ታውቆ ለየትኛውም ተጋድሎ ራስን ማዘጋጀት እንደሚገባ የፀጥታ ምክር ቤቱ አቅጣጫ ማስቀመጡን አንስተዋል። ጠላት የሚፈራውና የሚያከብረው የፀጥታ ኃይል መገንባት ይገባልም ነው ያሉት። ሕዝቡ ለፀጥታ ኃይሉ አስተማማኝ ደጀን ሆኖ ለሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች አጋዥ እንዲሆንም አሳስበዋል።

ከፀጥታው ጎን ለጎን የልማት ሥራዎች መሠራት እንደሚገባም ተናግረዋል። ጠላቶች በወሳኝ ወቅት በአማራ ክልል የልማት ሥራዎች እንዳይሰሩና ክልሉ ከድህነት እንዳይወጣ የማድረግ ሥራ እንደሚሠሩም አንስተዋል። የኑሮ ውድነትን ለመፍታት የልማት ሥራዎችን በትኩረት መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

ሕግ የማስከበር ሥራው ጠላቶች እንደሚሉት አማራን የማዳከም ሳይሆን አማራን የማጠናከር መሆኑንም አስገንዝበዋል። ሕዝቡም የሕግ ማስከበር ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየጠየቀ መሆኑንም ገልጸዋል። ለአማራ ሕዝብ ጥቅምና አንድነት የቆመን አካል የመያዝ ዓላማ እንደሌለ አስታውቀዋል። ሕግን ባከበረ መልኩ ሕግ የማስከበር ሥራው መቀጠል እንደሚገባውም የፀጥታ ምክር ቤቱ በአፅንኦት እንደገመገመው ነው የተናገሩት።

የአማራና የኦሮሚያ ክልል መንግሥታት የጥፋት ተልዕኮዎችን በጋራ ለማጥፋት እየሠሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ኦነግ ሸኔን ለማጥፋት የፀጥታ ኃይሎች በቅንጅት እየሠሩ መሆናቸውንም አንስተዋል። ጠላቶች ዜጎችን እየጨፈጨፉ የአማራን ሕዝብ ማስቆጣትና ሌላ ብጥብጥ እንዲያነሳ እንደሚፈልጉ የተናገሩት አቶ ግዛቸው ሕዝቡ የጠላትን አሰላለፍ መረዳት እንደሚገባው ነው የተናገሩት። የዜጎች ጭፍጨፋ ያስቆጣል፣ ያሳስባልም፣ መፍትሔው ግን በትግል ሥልቱ መግባባት እና መደራጀት ይገባል ነው ያሉት።

አሸባሪውና ወራሪው ትህነግ ለጦርነት ሲዝት እንደኖረና አሁንም እየዛተ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ግዛቸው የአማራ ሕዝብ የሰው አይነካም የራሱንም አሳልፎ አይሰጥም፣ ይሄን አቋማችን አጠናክረን እንቀጥላለን፣ ለሰላም ቅድሚያ እንሰጣለን ከዚያ በላይ ለሚመጣ ጉዳይ ዝግጅት ያስፈልጋል፣ ክልሉ የሚጠበቅበትን ያደርጋል ነው ያሉት። ክልሉ ከሌሎች ክልሎች ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑንም አስታወቀዋል። በመከፋፈል እና ጠላት በሚፈጥረው አጀንዳ በመራመድ ጥያቄዎችን ማስመለስ፣ ሰላምም ማምጣት አይቻልም ነው ያሉት። የጠላት ኃይል እስካልከሰመ ድረስ የዜጎች ሞት ሊቀርና ሰላም ሊመጣ እንደማይችል በመገንዘብ በአንድነት መሥራት ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ – (አሚኮ)

Leave a Reply