Site icon ETHIO12.COM

«ሚኒስቴሩ የዋጋ ንረትን እያባባሱ የሚገኙ ሌቦችን ለይቶ እርምጃ መውሰድ አልቻለም»

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የዋጋ ንረትን እያባባሱ የሚገኙ ሌቦችን ለይቶ እርምጃ መውሰድ አልቻለም ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከፍተኛ ወቀሳ አቀረቡበት።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በበኩሉ የዋጋ ንረቱንና የኑሮ ውድነቱን የሚያባብሱ 103 ሺህ 901 ህገወጦች ላይ በየደረጃቸው እርምጃ ወስጃለሁ ሲል አስታውቋል። 

ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ የሥራ ዘመን አምስተኛ መደበኛ ስብሰባውን ትናንትና ሲያደርግ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርን የስምንት ወራቅ ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል። 

በወቅቱ በርካታ የምክር ቤት አባላት የኑሮ ውድነቱን የሚያባብሱ ህገወጦች ላይ ተገቢው ዕርምጃ አልተወሰደም፤ በዚህም የተነሳ የሸቀጦች ዋጋ መቆጣጠር አልተቻለም በሚል በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ላይ የሰላ ትችት ሰንዝረዋል።

ሁል ጊዜ ሌባ አለ ፤ ሌቦችና ህገወጦች ናቸው ንግዱን የሚያበላሹት ይባላል። ይህንን ንግግር ከከፍተኛ ባለስልጣናት አንስቶ የንግድና ቀጠናዊ ሚኒስትሩም ሲደግሙት አድምጠናል። ይሁንና ሌቦቹ እነዚህ ናቸው ተብሎ አልተለዩም። ተለይተውም አስተማሪ እርምጃ ሲወሰድባቸው አናይም ሲሉ በምሬት ተናግረዋል። 

ሁልጊዜ አንድ ችግር ሲነሳ ህብረተሰቡ ነው የሚጎዳው፤ አሁንም በኑሮ ውድነቱ በተለይም በዘይትና በሌሎች መሰረታዊ ፍጆታዎች እጥረትና ውድነት የሚሰቃየው ሕዝብ ነው ብለዋል። 

በየቦታው በተዋቀሩ ሸማች ማኀበራት የለም የሚባለው ስኳርና ዘይት መርካቶ በችርቻሮ ጭምር ሲሸጥ ይታያል፤ ይህን ማስተካከል ደግሞ የሚኒስቴሩ ሥራ ነው ሲሉ የምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።

ሥልጣኑ በእጃችሁ እስካለ ድረስ ህገወጦች ላይ አስተማሪ እርምጃ ለምን መውሰድ ተሳናችሁ? ሲሉ የጠየቁት የምክር ቤት አባላቱ፤ በቀጣይ መሰረታዊ ፍጆታ ዕቃዎችን እንደፈለገ ሲያሻሽጥ የሚውለውን ህገወጥ ደላላ ማስታገስ ያስፈልጋል ብለዋል። 

በተለይም በንግዱ ስርዓት ላይ ህገወጥነትን እያስፋፉና የዋጋ ግሽበትን እያባባሱ የሚገኙ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ ከወሬ በዘለለ በተግባር ልትሰሩ ይገባል ሲሉ የምክር ቤት አባላቱ ለንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አመራሮች መልዕክት አስተላልፈዋል። 

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ በበኩላቸው፤ ተቋማቸው የኑሮ ውድነቱን የሚያባብሱ 103 ሺህ 901 ህገወጦች ላይ በየደረጃቸው እርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል። 

የኑሮ ውድነቱንና የዋጋ ንረቱን የሚያባብሱ ህገወጦች ላይ በየደረጃው በተዋቀረው የዋጋ ማረጋጋት ፤ ህገወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ ቁጥጥር ግብረ-ኃይል በኩል በተደረገ ክትትል የተለያየ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል። 

ገበያውን ለማረጋጋት ሲባል በተከናወነው የቁጥጥር ሥራ ሰባት ነጥብ 77 ሚሊዮን ብር በቅጣት መልክ ሰብስቦ ለመንግሥት ገቢ ማድረጉን ተናግረዋል። 

በቀጣይነትም የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት የሚረዱ የቁጥጥርና ህገወጥ ደላሎችን የመለየት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። 

ሚኒስቴሩ ህገወጦችን በየጊዜው እየለየ ቢሆንም እስከ ወረዳ ድረስ ግን የቁጥጥር ማነስና ህግን ተከትሎ ያለመስራት ክፍተት አለ ያሉት ሚኒስትሩ፤ አሁን ላይ ገና ወደስልጣን ከመጣሁ ስድስት ወር ቢሆንም በቀጣይ ጊዜያት ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ይበልጥ ትኩረት አድርጌ እሰራለሁ ሲሉ ተናግረዋል። 

በሌላ በኩል በፍራንኮ ቫሎታ አሰራር በእራሳቸው የውጭ ምንዛሪ መሰረታዊ ፍጆታ ወደ አገር ውስጥ ያስገቡ ዜጎች ያስመጡትን ምርት ወደ ገበያው የሚያስገቡበት መንገድ ላይ ጥብቅ የቁጥጥር ስርዓት ለመዘርጋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። 

ወደ አገር የገባውም ምን ያህል በተገቢው መንገድ እየተከፋፈለ ይገኛል የሚለውን በመለየት የዘይት ምርት እጥረትን እንዳይባባስ ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ህገወጥ ደላሎችንና ሌቦችን ከመስመር ለማስወጣት እንዲሁም ህገወጥ የነዳጅ ሽያጭን ለመከላከል መንግሥት ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል።

ጌትነት ተስፋማርያም

አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2014

Exit mobile version