ህጋዊ መስፈርት ሳያሟሉ አክሲዮን ሽያጭ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ሊከሰሱ ነው

ህጋዊ ሂደቶችን ሳያሟሉ በአክሲዮን ገበያ ሽያጭ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶችና ድርጅቶች በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን አስታወቁ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን በአክሲዮን ገበያ ህጋዊ አደረጃጀትና ሽያጭ ላይ እያጋጠሙ ባሉ የህግ ጥሰቶች ላይ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በልሁ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህጋዊ ሰነዶችንና ሂደቶችን ሳያልፉ እንደ አክሲዮን ማህበር አደራጅ ሆነው የሚሰሩ የማስታወቂያ ስራዎች መበራከታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ማንኛውንም አክሲዮን ማህበር በማቋቋም አክሲዮን ለመሸጥ የሚፈልግ አካል በቅድሚያ፣ በንግድና ቀጠናዊ ትስስር በኩል ስራውን ለመስራት የሚያስችሉ ሂደቶችን ማለፍና ፍቃድ ማውጣት እንዳለበት ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከካፒታል ገበያ ባለስልጣን ስለ ኢንቨስትመንቱ መግለጫ ወይም “ፕሮስፔክትስ” ማቅረብና ይሁንታን ማግኘት እንዳለበትም እንዲሁ።

ይህ ባልሆነበት ሁኔታ አክሲዮን የሚያቋቋሙና የሚያማልል ማስታወቂያ የሚያስነግሩ የአክሲዮን ማህበራት ህጋዊ አለመሆናቸውን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ በመሰል ድርጊቶች እንዳይታለል አስጠንቅቀዋል።

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ታዬ በበኩላቸው ፣ባለስልጣኑ የተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 1248/2021 ማንኛውም ለህዝብ የሚቀርብ አክሲዮን ወይም ሰነደ መዋዕለ ነዋይ፤ ለገበያ ከመቅረቡ በፊት በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መመዝገብ እንዳለበት የሚገልጽ መሆኑን አንስተዋል። ቀጥሎም መግለጫ ወይም ፕሮስፔክት ለባለስልጣኑ ማቅረብ እንዳለበት አዋጁ እንደሚደነግግ ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም ይህን ህጋዊ ሂደት በመጣስ በአክሲዮን ገበያ ሽያጭ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ላይ የገንዘብ ብሎም የእስር ቅጣት እንደሚጣል ሚኒስትሩ ማረጋገጡን ኢዜአ ዘግቧል።

See also  ከሽብር ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ ሰዎችን አሳልፎ ለመስጠት ሁለት አገራት ፈቃደኛ መሆናቸው ተሰማ፣ ዱባይ የተወሰኑትን አስረከበች

Leave a Reply