Site icon ETHIO12.COM

“በክልሉ አራት ወሳኝ አካባቢዎች ላይ ጠንካራና የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል”

በርዕሰ መስተዳድሩ የሰላሳ ቀን ዕቅድ መሰረት በሸኔ ታጣቂዎች ላይ የተቀናጀና ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደ ነው


የክልሉን ሰላም በማስፈን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ለመመለስ በኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሰላሳ ቀን ዕቅድ መሰረት በሸኔ ታጣቂዎች ላይ የተቀናጀና ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል የፀጥታና አስተዳደር ምክትል ቢሮ ኃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ አስታወቁ፡፡

ኮሎኔል አበበ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሰሞኑን በጨፌ ጉባዔ ላይ ሽብር ቡድኑን በአንድ ወር ውስጥ አደብ ለማስገዛት ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት በክልሉ አራት ወሳኝ አካባቢዎች ላይ ጠንካራና የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል፡፡

እንደ ምክትል ቢሮው ኃላፊ ገለጻ፤ ሽብር ቡድኑ በስፋት በመንቀሳቀስ በንጹሃን ዜጎች ላይ ሞትና በደል ያደረሰባቸው በወለጋ፣ በጉጂ፣ በምዕራብና ሰሜን ሸዋ አካባቢዎች በአሁኑ ጊዜ የክልሉና የፌዴራል የፀጥታ አካላት በሽብር ቡድኑ ላይ የተቀናጀ እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡

በተጀመረው ኦፕሬሽን በርካታ የሽብር ቡድኑ አባላት ተደምስሰዋል፡፡ የተመዘገቡ ድሎች በዝርዝር ለህዝብ ይፋ ይደረጋሉ፡፡

ሸኔ ከአሸባሪው ህወሓት ጋር በመሆን ኦሮሚያን የብጥብጥ ቀጠና በማድረግ አገር ለማፍረስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ የተናገሩት ኮሎኔል አበበ፤ ኦሮሚያ ብሎም ኢትዮጵያን ማፍረስ ከምናባዊ እሳቤና ከቀን ቅዥት ስሌት በዘለለ መቼም ቢሆን ሊሳካ የማይችል የሴረኞች ህልም ነው ብለዋል።

በቡድኑ ላይ እርምጃ እየተወሰዱ ባሉባቸው የሚገኙ የክልሉ ነዋሪዎች ከጸጥታ አካላት ጎን መሰለፋቸውን የጠቀሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ስንቅ በማቀበል፣ ጥቆማ በመስጠትና ቀጥታ እርምጃ በመውሰድ ህዝቡ እያደረገ ያለው ተሳትፎ የሚደነቅና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት በጎ ተግባር መሆኑን አስገንዝበዋል።

እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ የክልሉ መንግሥት ሽብተኝነትና ጽንፈኝነት ለክልሉም ሆነ ለአገር ህልውና አደገኛ መሆኑን በጽኑ ያምናል። በአሸባሪው ሸኔ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ሲጠናቀቅ በሌሎች አካባቢዎች ያለውን የሰላም ችግር ለመፍታት በሚደረገው እንቅስቃሴ ክልሉ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣም አስታውቀዋል።

በአንዳንድ ክልሎች የአገር ሰላምና የህዝቦች አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ የሽብር ተግባርና አስተሳሰብ በስፋት እየተስዋለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሌሎች ክልሎችም ሰላም ለማስፈን ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስዱ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። 

የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር በመሆን አገር የመገንባት ታሪክ እንጂ ጽንፈኛና ሽብርተኛን የማስታመም ህልውና የለውም ያሉት ኮሎኔል አበበ፤ በሽብርተኛው ሸኔ ላይ የጀመረውን የማያዳግም እርምጃ በመሰሎቹ ላይም እንደሚወስድ አስታውቀዋል።

የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች በድርጊታቸው ተጸጽተው ወደ ሰላማዊ ኑሮ የመመለስ ፍላጎት ካላቸው የክልሉ መንግሥት የሰላም በሩአሁንም ክፍት መሆኑንም አመልክተዋል።

ዋቅሹም ፍቃዱ EPA

Exit mobile version