Site icon ETHIO12.COM

የነዳጅ ድጎማ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ነው

የነዳጅ ድጎማን የተመለከተ ዝርዝር መረጃ !

የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ፤ ከመጪው #ሃምሌ 2014 ዓ/ም ጀምሮ የነዳጅ ድጎማ እየተደረጉ የሚቀጥሉ ተሽከርካሪዎችን ዝርዝር መረጀ ክልሎች ለይተው እንዲልኩ አዟል።

መረጃው ተሰብስቦ ወደ ማዕከላዊ ቋት የሚገባ ሲሆን ለሁሉም ነዳጅ ማደያዎች የተደጓሚ ተሽከርካሪዎች ዝርዝር ይሰጣቸዋል ተብሏል።

የማይታይም እና ሎጅስቲክስ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ ሰይፉ እልፉ ለሸገር ኤፍ ኤም 102.1 በሰጡት ቃል ፤

” ምን ያህል ተሽከርካሪዎች በኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ? የሚለውን ነገር አዋጁን መሰረት በማድረግ ዝርዝር መረጃዎችን አደራጅተን ለክልሎች በሙሉ ስልጠና ሰጥተን መረጃዎች ከክልል እየተሰበሰቡ ነው።

ትክክለኛ የሆነ መረጃ ፣ መደጎም ያለባቸው መኪኖች እነዚህ ናቸው ብለው ክልሎች ለይተው ያሳውቃሉ፤ እኛ ወደ ዳታ እናስገበ እና መደጎም ያለባቸው መኪኖች ተለይተው ይታወቃሉ።

ዝርዝር መረጃ ውስጥ በምንገባበት ወቅት የጠራ የመረጃ የለም የጠራ መረጃ እንዲኖር ነው እየተሰራ ያለው።

ይህን በአጭር ጊዜ ልንጨርስ ክልሎች ኃላፊነት ወስደው እየሰሩ ያሉ አሉ አንዳንዶቹ ክልሎች በከፊል መረጀዎችን ጨርሰዋል ” ብለዋል።

ለተመረጡ የትራንስፖርት ሰጪዎች ብቻ የሚደረገው የነዳጅ ድጎማ በምን አይነት መልኩ ነው አሰራሩ ላይ ቁጥጥር የሚደረገው ለሚለውም አቶ ሰይፉ ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥተዋል ፦

” ድጎማው ከማንዋል ወጥተን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ነው የሚሆነው።

GPS ይገጠማል Speed Limit ጋር የተጣመረ ነው የሚገጠመው ፤ በሌላ በኩል የሚገጠመው GPS ፤ የነዳጅ ሴንሰር አለው ፤ በኪሎ ሜትር ምን ያህል ሄደ ? ስንት ኪሎ ሜትር ላይ ምን ያህል ተጠቀመ የሚለው በሙሉ ይታወቃል።

ይሄን በምናደርግበት ሰዓት የሚደጎሙ መኪኖች በሙሉ ልዩ መታወቂያ ይሰጣቸዋል፤ ታግ ይለጠፋል።

ማደያዎች ያውቃሉ ዝርዝራቸው እነሱ ጋር ስለሚሰጠ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ማደያ በሙሉ ይሰጣቸዋል፤ እነሱ ያን ታግ አሳይተው ነው የሚቀዱት።

አሮጌና አዲስ መኪኖች አሉ ። እነዚህ በሙሉ ይለያሉ ደረጃ 1፣ 2፣ 3 የሚባለው የነዳጅ አጠቃቀምና የኪ/ሜትር ሽፋናቸው ይታወቃል። ስለዚህ በዛ መሰረት እያንዳንዱ ተለይቶ ነው የሚሰጠው።

ለምሳሌ ፦ አዲስ አበባ ላይ ከፒያሳ – መገናኛ የሚሄድ ታክሲ ኪ/ሜትሩ ይታወቃል ፤ ስንት ጊዜ ተመላለሰ የሚለው ይታወቃል ይህን ሂሳብ ተሰርቶ በቀን ስንት ኪ/ሜትር ሸፈነ ፤ በአንድ ሊትር ስንት ኪ/ሜ ይሄዳል የሚለው ስለሚታወቅ በሱ መጠን ነው ነዳጅ የሚቀዳው።

ከዚህ ውጭ ነዳጅን ባልተሰጠው ነገር ሄጄ እቀዳለሁ ካለ ገበያው ባስቀመጠው ዋጋ ነው የሚቀዳው እንጂ በታሪፉ አይካተትም።

አሁን GPS ገጣሚዎችን በሙሉ ስልጠና ሰጥተናል። እራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አድርገናል መንግስት በራሱ በኩል አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅት አድርጓል ” ብለዋል።

👉 ታክሲዎች

👉 ሃይገሮች

👉 ባጃጆች

👉 የሃገር አቋራጭ አውቶብሶች የነዳጅ ድጎማው የማይነሳባቸው ሲሆን ነገር ግን ለመደጎም በማህበር መደራጀት ግዴታቸው ነው ተብሏል።

ባለንብረቶች በማህበር ካልተደራጁ በግለሰብ ደረጃ ማንም ሊደጎም እንደማይችል አቅጣጫ ተቀምጧል።

በሌላ በኩል ፤ ከፌዴራል እስከ ክልል ባለው መዋቅር ለመንግስት ስራ የሚያስፈልጉ መኪኖች ድገማው የማይመለከታቸው ሲሆን በወቅታዊ የገበያ ዋጋ እየገዙ ይጠቀማሉ ተብሏል።

አቶ ሰይፉ ፤ ” መንግስት አይደጎምም ፤ መንግስት ከድጎማው ይወጣል ፤ አይደጎምም በነፃው ገበያ ነው መቅዳት ያለበት። ምክንያቱም መደጎም ያለበት ድሃው የህብረተሰብ ክፍል ነው። ” ሲሉ ለሬድዮ ጣቢያው ተናግረዋል።

Credit : ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 @tikvahethiopia

Exit mobile version