Site icon ETHIO12.COM

የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ሰራዊቱን ከአፋር ኤሬብቲ ማስወጣቱን አስታወቀ፤ አፋር ክልል አላረጋገጠም

ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ጦርነት ውስጥ የገባው ህወሓት በአፋር ክልል ኤሬብቲ ተብሎ የሚጠራ ስፍራን ተቆጣጥረው የነበሩ ተዋጊዎቼ አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ አድርጊያለሁ ማለቱን ቢቢሲ አስታወቀ። የአፋር ክልል ግን እስካሁን ያለው ነገር የለም።

ትህነግ ወሮ ከያዘው ኤሬብቲ ተብሎ ከሚጠራው ስፍራ ለማስወጣት ከውሳኔ የደረሰው ለሰብአዊነት ሲባል የተደረሰው ስምምነት ተከብሮ ያልተገደብ ሰብአዊ እርዳት ትግራይ እንዲደርስ ሲባል መሆኑንን አመልክቷል። ይሁን እንጂ ሌሎች የአፋር ክልል አካል ከሆኑ ስፋራዎች መንግስት እንዲለቅ ቢጠይቅም ለምን ሙሉ በሙሉ ለቆ እንዳልወጣ ያለው ነገር የለም።

ትህነግ ለሰላም ውይይቱን ለማሳለጥ በተለይም ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ሚያዚያ 4/2014 ዓ. ም. የትህነግ ሠራዊት ተቆጣጥሮት ከነበረው ኤሬብቲ ተብሎ ከሚጠራው የአፋር አካባቢ ሠራዊቱ እንዲነሳ መደረጉን ያስታወቀው ሚያዚያ 5/2014 ዓ.ም. በክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ በተላለፈው መግለጫ እንደሆነ ቃል በቃል ትርጉሙን ቢቢሲ አስቀምጦ መረጃውን አሰራጭቷል። ይሁን እንጂ የአፋር ክልል በወረራ የያዘው የትህነግ ሃይል አካባቢዎቹን ለቅቆ ስለመውጣቱ ያለው ነገር የለም።

የትህነግ ኃይሎች ተመተው ከለቀኡ በሁዋል ዳግም በአፋር ክልል ዞን ሁለት የሚገኙ ወረዳዎችን የወረሩት በጥር ወር አጋማሽ ላይ እንደነበር ይታወሳል። በዚህም የተነሳ በመቶ ሺህ ሲፈናቀሉ፣ በርካታ ንጹሃንና ህጻናት በአሰቃቂ ሁኔታ እንደተገደሉና አካላቸው እንደጎደለ ሪፖርቶች ሲወጡ ነበር። በቪዲዮ የተደገፉ መረጃዎችም ተሰራጭተዋል። ክልሉ እንዳለው አምስት ወረዳዎችን በወረራ መያዛቸውን ማስታወቁም አይዘነጋም።

በኪልበቲ ረሱ ዞን በህወሓት ቁጥጥር ሥር ገብተዋል ተብለው ከነበሩት 5 ወረዳዎች መካከል አብአላ፣ መጋሌ፣ ኤሬብቲ እና በራህሌ ይገኙባቸዋል። ትህነግ በትናንቱ መግለጫ ሠራዊቴን አስወጥቻለሁ ያለው ኤሬብቲ ተብሎ ከሚጠራው ስፍራ ነው። ትህነግ ከአፋር ክልል ሙሉ በሙሉ ስለመውጣቱ እስካሁን ግልጽ አይደለም።

የአፋር ክልል በአምስት ዞኖች የተዋቀረ ሲሆን ከትግራይ ክልል ጋር የሚዋሰኑ ዞን ሁለት ውስጥ አምስት ወረዳዎች ይገኙበታል። ትህነግ ሠራዊቴን አስወጥቻለሁ ያለበት ኤሬብቲ በዞን ሁለት ውስጥ ካሉ ወረዳዎች አንዱ እንደሆነ

ከሰመራ መቀለ በሚደረገው የየብስ የሰብአዊ አቅርቦት ዋነኛ መንገድ ላይ የሚገኘው አብአላ ወረዳ በዞን ሁለት ውስጥ ይገኛል።

ህወሓት የአፋር ክልል አካባቢዎችን መያዙን ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ከቀያቸው ተፈናቅለው እንደነበረ የአፋር ክልላዊ መንግሥት አስታውቋል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማድረስ ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን ተከትሎ የትግራይ ኃይሎችም ውሳኔውን ተቀብለው ግጭት ለማቆም ተስማምተዋል።

መንግሥት ግጭት የማቆም ውሳኔውን ባስታወቀበት መግለጫ “በትግራይ ክልል የሚገኙ አማጺያን ከማንኛውም ጥቃት እንዲታቀቡና በኃይል ከያዟቸው የአጎራባች ክልል አካባቢዎች እንዲወጡ” ጠይቆ ነበር።

ሁለቱ ኃይሎች ለሰብአዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም ከተስማሙ በኋላ፤ ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተሸከርካሪዎች ከወራት በኋላ ትግራይ መድረስ ችለዋል።

ይህ የህወሓት ከአፋር አካባቢ ሠራዊት የማስወጣት ውሳኔ የተሰማው የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ እና ምክትላቸው ፓይተን ኖፍ አዲስ አበባ እንደሚገቡ በተገለጸበት ወቅት ነው።

አምባሳደሩ ለመጨረሻ ጊዜ ማለትም መጋቢት 12 እና 13/2014 ዓ. ም. በአዲስ አበባ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ነበር የፌደራሉ መንግሥት ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ ሲል ግጭት ለማቆም መወሰኑን ያስታውቀው።

አምባደር ሳተርፊልድ በዚህኛው ጉብኝታቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከሰብአዊ ድርጅት አስተባባሪዎች እና ዲፕሎማቲክ አጋሮች ጋር ይገናኛሉ ሲል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቋል።

ከ18 ወራት በፊት በፌደራሉ መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስን አስከትሏል። በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አጎራባች ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ህልፈት ምክንያት ሆኗል።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ለረሃብ ተጋልጠዋል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ቁጥራቸው በውል በማይታወቁ ሰዎች ላይ የተለያየ መጠን እና ዓይነት ያላቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል።

Exit mobile version