Site icon ETHIO12.COM

ካናዳ ኢትዮጵያን እደግፋለሁ አለች

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት፣ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት እንዲሁም የጤና ሥርዐት ለመዘርጋት ካናዳ እገዛ እንደምታደርግ ገለጸች።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት፣ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት እንዲሁም የጤና ሥርዐት ለመዘርጋት ካናዳ እገዛ እንደምታደርግ በኢትዮጵያ የሀገሪቱ አምባሳደር ስቴፋኒ ጆቢን ገለጹ።

በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ስቴፋኒ ጆቢን፤ የካናዳና ኢትዮጵያ የቆየ ጠንካራ ወዳጅነት ተጠናክሮ የሚቀጥል መኾኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የገጠማትን ወቅታዊ ችግር እንድታልፍ ካናዳ እገዛ እንደምታደርግ አረጋግጠው የኢትዮጵያን የተለያዩ የልማት ጥረቶችም ትደግፋለች ብለዋል።

በተለይም “ሴቶችን ማዕከል ያደረገው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችንን መሠረት በማድረግ በኢትዮጵያ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን እየደገፍን እንገኛለን” ሲሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ሀገራዊ ምክክር ካናዳ በአዎንታዊ ጎኑ የምትቀበለውና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እገዛ የሚያደርግ መኾኑን ታምናለች ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ የታለመለትን ግብ እንዲመታና በኹሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ኹሉን አቀፍና ግልጽ የፖለቲካ ሂደቶች ሊኖሩት ይገባል ነው ያሉት።

በጦርነቱ ወቅት የተፈጸሙትን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች በተጠያቂነትና በፍትሕ ሥርዐት ገቢራዊ ማድረግም ወሳኝ መኾኑን አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጋር ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተደጋጋሚ የስልክ ልውውጥ ማድረጋቸውን አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ለኢትዮጵያ አቻቸው ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ ድጋፍ የወሰነችው የተኩስ አቁም ውሳኔ ተገቢ መኾኑን ገልጸውላቸዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የካናዳ ዓለም አቀፍ የድጋፍ ትብብር መርኃ-ግብር አንዷ ሀገር መኾኗን ገልጸው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2021 እስከ 2022 ኢትዮጵያ 43 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር ድጋፍ እንደተቀበለች ተናግረዋል።

የገንዘብ ድጋፉም በኢትዮጵያ ጦርነቱን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ችግር ላይ የወደቁ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ የሚውል መኾኑን አስረድተዋል።

ለኢትዮጵያ የልማት ግቦች መሳካት የሚያግዝ 74 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር ድጋፍ ማድረጓን እንደገለጹ ኢዜአ ዘግቧል።

በጦርነቱ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ድጋፍ ለማድረግና በኢትዮጵያ የሥርዐተ-ጾታና የሥነ-ተዋልዶ ጤና ለማጎልበት የሚደረገውን ጥረት እያገዘች መኾኑንም አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል በቅርቡ የካናዳ መንግሥት ይፋ ባደረገው ስደተኞችን የማቋቋም መርኃ-ግብር በመታገዝ በኢትዮጵያ ስደተኞችና ተቀባይ ማኅበረሰቦችን የትምህርት ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያና የካናዳ የኹለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1965 ነበር።

(አሚኮ)

Exit mobile version