Site icon ETHIO12.COM

የምስራቅ አፍሪካ ወታደራዊ የመረጃ ተቋማት ሽብርተኝነትን በጋራ ለመከላከልና ለማጥፋት ተስማሙ

የምስራቅ አፍሪካ ወታደራዊ የመረጃ ተቋማት ሽብርተኝነትን ለመከላከልና የቀጣናውን ዘላቂ ሠላም ለማስጠበቅ በትብብር እንደሚሠሩ ገለጹ።

የምስራቅ አፍሪካ የመከላከያ ወታደራዊ መረጃ መድረክ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ትናንት በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የመከላከያ ሠራዊት መረጃ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄነራል ብርሀኑ በቀለ፤ ምሥራቅ አፍሪካ የጸጥታና ደህንነት ሁኔታ አሸባሪዎች፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እንዲሁም ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ያለበት መሆኑን ጠቅሰዋል። እነዚህ ሁሉ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ የጸጥታና የደህንነት ስጋቶችን ለመከላከል አገራት በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ቀጣናውን እየፈተኑ ያሉ እንደ አልሻበብ፣ አይ ኤስ አይ ኤስና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሽብርተኞችን በተናጠል መመከት አስቻጋሪ መሆኑን ጠቁመው፤ ችግሩን ለመፍታት አገራት በጋራ መሥራት እንዳለባቸው የመምሪያው ኃላፊው ገልጸዋል። 

በተጨማሪም በአገር ውስጥ እንደ ሸኔና ሕወሓት ያሉ አሸባሪ ቡድኖች የሕዝቡን ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል ያደረሱትን በደል አስታውሰዋል። መሰል ጥቃቶችን አገራት መረጃ በመለዋወጥ መከላከል እንዳለባቸውም ነው ያስገነዘቡት። 

እንደ ሌተናል ጄኔራሉ ገለጻ፤ በግሎባላይዜሽን ዘመን አንድ አካባቢ ያለው መልካም አጋጣሚም ሆነ ስጋት በአንድ አካባቢ ብቻ የሚወሰን አይደለም። ለዚህም ከመልካም ነገር ልምድ በመውሰድ የበለጠ ማዳበር፤ መጥፎ ነገር ሲኖር ደግሞ ቀደም ብሎ መከላከል እንዲቻል የተዘጋጀው ፎረም አጋዥ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ፎረሙ ትብብር ለመፍጠር ልምድ ለመለዋወጥ በቀጣይነትም በትስስር መንፈስ ለየአገራቱ የደህንነትና የጸጥታ ስጋት የሆኑ ሁኔታዎችን ቀድሞ በማወቅና ቀድሞ ለመከላከል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንደተዘጋጀም አንስተዋል። 

ከዚህ ባለፈም ፎረሙ ለፖሊሲ አውጭዎች ተዓማኒ የሆነ መረጃን ለማቀበልና በመከላከያ ደረጃ ለመሥራት የሚያስችል ምቹ ውሳኔ ለመፍጠርም ይረዳል ነው ያሉት። 

የጅቡቲ መከላከያ ኃይል መረጃ ኃላፊ ኮሎኔል ሜጀር አደን ዱአሌ በኢትዮጵያ ጋባዥነት በፎረሙ በመሳተፋቸው አመስግነዋል። ፎረሙ ጠንከር ያሉ ሀሳቦችን ለማንሳትና በየአገራቱ መካከል ያለውን ልምድ ለመጋራት ትልቅ እድል እንደሆነም ጠቅሰዋል። 

የመረጃ ክፍል ለአገራቱ ደህንነት የጀርባ አጥንት እንደሆነ የጠቆሙት ኃላፊው፤ ያለመረጃ ልውውጥ ውጤታማ የደህንነት ሥራ ማከናወን እንደማይቻልና አሸባሪዎችን መመከት አዳጋች እንደሚሆን ገልጸዋል። የምስራቅ አፍሪካ አገራት ሽብርተኝነትን ለመከላከል ትብብርን ማዕከል ያደረገ ሥራ መሥራት ይኖርባቸዋልም ብለዋል።

ጅቡቲና ኢትዮጵያ በደህንነት ሥራዎች ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው አገራት እንደሆኑና፤ ግንኙነቱን በወታደራዊ የመረጃ ልውውጥ ደረጃ ለማሳደግ ጅቡቲ ቁርጠኛ እንደሆነች ተናግረዋል። ጅቡቲ የተለያዩ አገራት የጦር ቤዝ መቀመጫ እንደመሆኗ ለምሥራቅ አፍሪካ አገራት ወታደራዊ መረጃዎችን ለመስጠት ቁርጠኛ ናት ሲሉም ገልጸዋል። 

በምሥራቅ አፍሪካ አገራት የደህንነት መዋቅርና ትስስር መፍጠር ካልተቻለ አስቸጋሪ እንደሆነ የጠቆሙት ኃላፊው፤ ያለ መረጃ ልውውጥ ምንም ነገር ማከናወን የማይቻል በመሆኑ ጠንካራ ግንኙንትን በመፍጠር በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። 

የሶማሊያ መከላከያ ወታደራዊ ደህንነት ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ሰአድ ሙሐመድ በበኩላቸው፤ የጋራ የደህንነት ፍላጎት ላይ ያተኮረው አጀንዳ ለአገራቱ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ጠቅሰዋል። በቀጣናው ያሉ ሕዝቦች የባህል፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋና መሰል እሴቶችን እንደሚጋሩ ሁሉ፤ የጋራ ጠላታቸው የሆነውን ሽብርተኝነትን በጋራ መከላከል እንዳለባቸውም አስታውቀዋል። 

በፎረሙ ኢትዮጵያን ጨምሮ የኡጋንዳ፣ የኬንያ፣ የታንዛኒያ፣ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያና ጅቡቲ አገራት የወታደራዊ መረጃ ኃላፊዎችና አታሼዎች ተሳትፈዋል።

አዲሱ ገረመው አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9 ቀን 2014 ዓ.ም

Exit mobile version