Site icon ETHIO12.COM

በሃይማኖት ሽፋን – የፌዴራል የደኅንነትና የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አስታወቀ

በጎንደር በተከሰተው ግጭት የተሳተፉና ሁከቱን ለማባባስ የተንቀሳቀሱ 280 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን አመልክቷል።

በሃይማኖት ሽፋን ግጭት ለመቀስቀስ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የፌዴራል የደኅንነትና የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።

በሃይማኖት ሽፋን ግጭት በመቀስቀስ ጸረ-ኢትዮጵያ የሆኑ ኀይሎችን ፍላጎት ለማሳካት በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የፌዴራል የደኅንነትና የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።

በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጎንደር ከተማ ከቀብር ስፍራ ጋር በተያያዘ በክርስትናና በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የተቀሰቀሰውን ግጭት መነሻ በማድረግ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም በሃይማኖት ሽፋን ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር ጸረ-ኢትዮጵያ የሆኑ ኀይሎችን ፍላጎት ለማሳካት በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የፌደራል የደኅንነትና የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቋል።

የጋራ ግብረ ኃይሉ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ጸረ ኢትዮጵያ አቋም የሚያራምዱ የተለያዩ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ብሔርን መሰረት ያደረገ የጥላቻ አጀንዳ በማሰራጨት ሀገሪቱን ወደ ቀውስ ለማስገባት ጥረት ሲያደርጉ ነበር።

ሕብረተሰቡ ለዓመታት በገነባው ጠንካራ የሆነ የጋራ እሴት ይህ ሙከራ የከሸፈባቸው ኃይሎች፣ ቀሪውን የሃይማኖት ካርድ በመምዘዝ በተለያዩ እምነት ተከታዮች ዘንድ መጠራጠርና ጥላቻ እንዲፈጠር ብሎም ወደ ግጭት እንዲያመራ በተለያዩ መንገዶች ሲቀሰቅሱ ቆይተዋል።

በጎንደር የተከሰተው ግጭት በተለያዩ እምነቶች መካከል ግጭት በመቀስቀስ ወደ ሀገራዊ ቀውስ እንዲያመራ የሚደረገው ሴራ አካል መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፤ በዚህ ድርጊት በተሳተፉ አካላት ላይ ተገቢ እርምጃ መወሰደ መጀመሩን ጠቁሟል።

በዚህ መሰረት በጎንደር በተከሰተው ግጭት የተሳተፉና ሁከቱን ለማባባስ የተንቀሳቀሱ 280 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን አመልክቷል።

እንደ መግለጫው፤ በጎንደር የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በሌሎች አካባቢዎችም በተለያዩ እምነት ተከታዮች መካከል ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር የሚጋብዙ ቅስቀሳዎች እንዲሁም ሃሰተኛ መረጃዎችም በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በስፋት እየተሰራጩ ይገኛሉ።

በአንዳንድ አካባቢዎችም የእምነት ተቋማትና ግለሰቦች ላይ ጥቃት በመፈጸም ግጭቱ ሀገራዊ ቅርጽ እንዲኖረው ሙከራ እየተደረገ ነው።

የፌዴራል የደኅንትና የጸጥታ መዋቅር በድርጊቱ በሚሳተፉት ላይ ብቻ ሳይሆን ከኋላ በመሆን በሚዘውሩት ላይ በቂ መረጃና ማስረጃ ያለው በመሆኑ ተከታታይ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ያስታወቀው መግለጫው፤ ችግሩ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም እንዲስፋፋ በየትኛውም የመገናኛ ዘዴ የሚቀሰቅሱ፤ በተለይም ደግሞ የማኅበራዊ ትስስር ገፆችን በመጠቀም ሐሰተኛና የጥላቻ መረጃ የሚያሰራጩ አካላት በሕግ የሚጠየቁበት አግባብ መኖሩን ጠቁሟል። በዚህ ህግወጥ ድርጊት የሚሳተፉ ባስቸኳይ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም በጥብቅ አሳስቧል።

ኢትዮጵያውያን ለዓመታት የገነቡት በአብሮነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እኩይ ዓላማ ባነገቡ የውስጥና የውጭ ፀረ ሰላም ኀይሎች እኩይ ሴራ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ አካላት በሚፈጥሩት የግጭት አጀንዳ አይሸረሸርም ያለው መግለጫው፤ ሕብረተሰቡ ለዘመናት ባዳበራቸው መልካም እሴቶች እንደዚህ አይነት የፈተና ወቅቶችን በውይይትና በሰከነ መንፈስ በመፍታት እንደሚያስመሰክር የጋራ ግብረ ኃይሉ እምነት መሆኑንም ጠቁሟል።

ዛሬም ኢትዮጵያን ሌላ የግጭት አጀንዳ በመስጠት ለማተራመስ ሙከራ ቢደረግም በደኀንነትና በጸጥታ መዋቅሩ ከፍተኛ ጥረት በቁጥጥር ስር ውሏል ያለው የፌዴራል የደኅንነትና የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል፤ ሕብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን በመሆን ችግሩ እንዳይስፋፋ ያደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመልክቷል።

Exit mobile version