Site icon ETHIO12.COM

በድሬዳዋ ከተማ በነበረው ሁከት ተሳታፊ የነበሩ 89 ተጠርጣሪዎች ተያዙ

በእለቱ የነበረውን ሁከት አስመልክቶ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ብሩክ ፈለቀ እና የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምርያ የህዝብ ግንኙነትና የለውጥ ስራዎች ዳይሬክተር ኮማንደር ገመቹ ካቻ በጋራ በመሆን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በሰጡት መግለጫ÷ በክርስትና እና በእስልምና እምነት ተከታዮች ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው የረመዳንና የዐብይ ፆም ፍፁም ወንድማማችነትና እህትማማችነት እንዲሁም አብሮነት የታየበት መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በተጨማሪም ሙስሊሙ ለክርስቲያኑ ከቤተክርስትያን ሲወጡ የተለያዩ መስተንግዶ ያደረጉበት ክርስትያኑ ለሙስሊሙ የአፍጥር ስነ ስርዓት በማዘጋጀት አብረው የፆሙበት የድሬዳዋ እሴቷ የጎለበተበት ታላቅ ወቅት ነበር ሲሉም በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡

ይህን ለማጠልሸት የተለያዩ አጀንዳዎችን በመያዝ በትላንትናው እለት የጁመአ ሶላት አድርገው ምእመኑ ወደ ቤታቸው በሚመለሱበት ወቅት ፅንፈኛ የሆኑ አካላት ሁከትና ረብሻ በማስነሳት ንብረቶችን ለማውደም ባደረጉት እንቅስቃሴ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት እንደደረሰ ተገልጿል።

ይህ እኩይ ተግባር የሙስሊሙን ማህበረሠብ የማይወክል ሲሆን÷ በተከሰተው ረብሻና ሁከት አንድ የ4 አመት ህፃን ልጅ በተባራሪ ጥይት ተመቶ ህይወቱ ማለፉን እና 22 ፖሊሶች መጎዳታቸው ተገልጿል።

በችግሩ ወቅት የተያዙ 89 ተጠርጣሪዎች ለሁከቱ ሊጠቀሙባቸው የነበሩ ሀሺሽና ቤንዚል እጅ ከፍንጅ መያዛቸውም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

ለሁከትና ረብሻ ሲጠቀሙባቸው የነበረው ህፃናትን በመሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን የመምከርና የመገሰፅ ሀላፊነት እንዳለባቸው እና ነዋሪዎች የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል።

በድሬደዋ ከተማ ሁከት እንዳለ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚተላለፉ መልዕክቶች ሀሰት መሆናቸውን በመግለፅ÷ ከተማዋ ሰላም መሆኗን እና ሙሉ ለሙሉ እንቅስቃሴ መኖሩም ተመላክቷል፡፡

ማህበረሰቡ ማንኛውንም ፀጉረ ልውጥ ሰው ሲያይ በአቅራቢያ ወዳለ ፖሊስ ጥቆማ በመስጠት ማሳወቅ እንዳለበት መልዕክት መተላለፉን ከድሬዳዋ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡\

ፋና

Exit mobile version