Site icon ETHIO12.COM

በኦሮሚያ ቦረና ዞን – ገበሬዎች ራሳቸው ሞፈር እየጎተቱ እያረሱ ነው

በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በምትገኘው ተልተሌ ወረዳ በቅርቡ ባጋጠመው ድርቅ ከብቶቻቸውን ያጡ ገበሬዎች በበሬ ፈንታ ራሳቸው ሞፈር እየጎተቱ ሲያርሱ መታየታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

በኦሮሚያ ቦረና ዞን የተልተሌ ወረዳ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አማረ ምንም እንኳ ሁኔታው በስፋት ባይስተዋልም በድርቁ ምክንያት በሬዎቻቸው የሞቱባቸው ገበሬዎች ራሳቸው ሞፈር እየጎተቱ እያረሱ መሆኑን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ከሰሞኑ ይህንኑ የሚያሳይ አንድ ተንቀሳቃሽ ምሥል በማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት መጋራቱን ተከትሎ ነበር ጉዳዩ አነጋጋሪ ሆኖ የቆየው።

እነዚህን ተንቀሳቃሽ ምሥሎች እና ፎቶግራፎች በስልካቸው ካሜራ ያስቀሩት በአካባቢው ባለ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት አቶ ዱብ ቡራ ናቸው።

ለቢቢሲ የተጋራው ይህ ተንቀሳቃሽ ምሥል ሰዎች በቡድን ሆነው በሬን ተክተው ሞፈር እየጎተቱ ሲያርሱ ያሳያል። 

መምህር ዱብ ቡራ ምሥሎቹን ያስቀሩበትን አጋጣሚ ሲያወሱ ወደ ትምህር ቤት እየሄዱ ሳለ ከዚህ ቀደም አይተው የማያውቁት ክስተት እንዳጋጠማቸው ያስረዳሉ። 

“ከዚህ ቀደም አይቼ የማላውቀው ነገር ስለሆነ በቪዲዮ ቀረጽኩና አወጣሁት። ለምን እንደዚህ እንደሚያርሱ ስጠይቃቸው፤ ‘እንደምታውቀው በሬዎች የሉንም። ጊዜው የእርሻ ስለሆነ ደግሞ ማረስ አለብን’ አሉኝ” በማለት ለቢቢሲ ሁኔታውን ተናግረዋል። 

በተልተሌ ወረዳ ቢሌ ዳንዲ ቀበሌ በዚህ መልኩ እያረሱ ከሚገኙት መካከል አንዱ የሆነው ወጣት ቱራ ቦባ ይባላል። 

ቱራ “በድርቁ ምክንያት ከብቶቻችን ስላለቁብን፤ ከብቶችን ተክተን ለማረስ እየሞክርን ነው” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል። 

ቱራ አቅም ያላቸው ወጣቶች በአምስት አምስት ተቧድነው የጎረቤት ሰዎች እርሻዎችን እያረሱ እንደሆነ ይናገራል።

ይህን ምሥል ከቀረጹ አንድ ሳምንት እንደሆናቸው የሚናገሩት መምህሩ ደግሞ፤ በቅርቡ ዝናብ መጣል መጀመሩን ተከትሎ አርሶ አደር በሚበዛበት አካባቢ የእርሻ ሥራ መጀመሩን ይናገራሉ። 

“በድርቁ ምክንያት ከብቱን የሸጠ አለ፣ ከብቶቹ የሞተበትም አለ። በዚህ መንገድ [በሬን ተክቶ] ከማረስ ውጭ ሌላ አማራጭ የላቸውም” የሚሉት መምህሩ፤ የተደራጁ ወጣቶች በሬ ለሌላቸው አርሶ አደሮች በክፍያ በሬን ተክተው በጉልበት እያረሱ እንደሆነ ያስረዳሉ። 

የተልተሌ ወረዳ ግብርና ቢሮ ኃላፊው አቶ ብርሃኑ አማረ፤ በቅርቡ ዝናብ መጣል መጀመሩን ተከትሎ የእርሻ ሥራ መጀመር ያለበት ነው ይላሉ። በአካባቢው በሬ የሌላቸው ሰዎች በሬ ካላቸው ሰዎች ተውሰው እያረሱ እንደሆነም የግብርና ቢሮ ኃላፊው ይናገራሉ። 

በወረዳው ለእርሻ ሥራቸው በሬ የሌላቸው ሰዎች ቁጥር ምን ያክል እንደሆነ መረጃው እንደሌላቸው የሚናገሩት የግብርና ቢሮ ኃላፊው፤ የክልሉ መንግሥት ግን ዘር እና ማዳበሪያ ለገበሬው እያቀረበ እንደሆነ ተናግረዋል። 

አቶ ብርሃኑ ገበሬው የእርሻ መሬቱን ለማረስ በሚያደርገው ጥረት መንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ከቀናት በፊት የተመድ የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው ድርቅ ከ14-20 ሚሊዮን ሰዎችን ለረሃብ ሊዳርግ ይችላል ሲል አስጠንቅቆ ነበር።

ድርጅቱ በኢትዮጵያ በድርቁ ምክንያት 7.2 ሚሊዮን ገደማ የቤት እንስሳት ሳይሞቱ አይቀርም ያለ ሲሆን፤ በደቡብ እና ደቡብ ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል ያሉ ሰዎች በ40 ዓመታት ውስጥ አይተው የማያውቁት ድርቅ አጋጥሟቸዋል ብሏል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል በድርቁ ምክንያት የተጎዱ ሰዎችን ለመደገፍ በቀጣይ ስድስት ወራት 239 ሚሊዮን ዶላር ይፈልጋል ይላል የፋኦ መግለጫ via bbc

Exit mobile version