Site icon ETHIO12.COM

አሸባሪው ህወሓት ለመዝመት ፍቃደኛ ያልሆኑ ልጆች ወላጆችን እያሰረ መሆኑ ተነገረ

ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ የገባው አሸባሪው የህወሓት ቡድን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ልጆቻቸው ያልዘመቱ ወላጆችን እያሰረ እንደሚገኝ የቤተሰብ አባላት ለቢቢሲ ተናገሩ።

ቢቢሲ ያነጋገረው አንድ የትግራይ ተወላጅ፤ ልጆች ለመዝመት ፍቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ወላጅ አባቱ እና አጎቱ እንደታሰሩ ገልጿል።

ለራሱና ለቤተሰቡ ደኅንነት ሲል ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው ወጣት፤ “ቢያንስ ከቤተሰብ አንድ ሰው ለውድትርና መላክ የሚል ሕግ አለ” ይላል።

ይህ በአሁኑ ወቅት ከትግራይ ክልል ውጪ የሚገኘው ወጣት፤ “አባቴን ልጅህን አምጣህ አሉት። ማምጣት ስላልቻለ ለአንድ ወር አሰሩት። ከዚያ ደግሞ ወንድሜን እንዲያመጣ ብለው ለቀውት ነበር። አሁን ያለበትን ሁኔታ ባላውቅም ለመጨረሻ ጊዜ በስልክ ሳገኛቸው አባቴን አስረውት ነበር” በማለት ይናገራል።

ይህ ወጣት እንደሚለው አዋቂ የሆነው ወንድሙ በዚህ ጦርነት ተሳታፊ የመሆን ፍላጎት የለውም። “ወንድሜ እኮ ትልቅ ነው። ከፈለገ የአባቴን ፍቃድ ሳይጠይቅ ይሄድ ነበር። የያዙት ግን አባቴን ነው” በማለት ይናገራል።

ልጆቻቸውን ወደ ጦር ሜዳ ባለመላካቸው አጎቱም ጭምር ለእስር መዳረጋቸውን ይህ ወጣት ይናገራል። “ከሁለት ወር በፊት አጎቴንም ሴት ልጁን አምጣ ብለው አስረውት ነበር። 18 ዓመት እንኳን አይሆናትም” ይላል።

“የደረሱ ልጆች የሉትም። በቤቱ ውስጥ ከትንንሾቹ መካከል ተለቅ ያለችው እሷ ነች። ስልክ ስለሌለ አሁን ያሉበትን ሁኔታ አላውቅም” ይላል።

ይህ ወጣት እንደሚለው ከሆነ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የትግራይ ክፍል እያስተዳደረ ያለው ህወሓት ለመዝመት ፍቃደኛ ያልሆኑ ልጆች ወላጆችን ማሰር ከመጀመሩ በፊት ሰዎችን አስገድዶ ወደ ጦር ሜዳ ይልክ ነበር ይላል።

“ከዚህ በፊት በኃይል አስገድዶ የመወስደ ተግባር ነበር። ይሄ ብዙ አላስኬድ አላቸው። ከዚያ ‘ወላጆችን ብንይዝ [ወደ ትግል]’ ይገባሉ የሚል አካሄደ መጥቷል። ይሄ በትግራይ በጣም ችግር እየሆነ ነው። እንደ ሕግ ነው የወረደው” በማለት ያብራራል።

ከዚህ ወጣት በተጨማሪ በጦርነቱ ለመዋጋት ፍላጎት ስለሌላቸው ወላጆቻቸው እንደተሳሩባቸው ከሚናገሩት መካከል በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆኑት አቶ ክብሮም በርሀ ይገኙበታል።

የባይቶና ዓባይ ትግራይ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ክብሮም በርሀ ታናሽ እህታቸው ለመዝመት ፍላጎት ስለሌላት ወላጅ እናታቸው በህወሓት መታሰራቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“እኛ ቤት ሁሉም ስደት ላይ ናቸው። ከ18 ዓመት በታች የሆነች እህቴ ብቻ አለች [በትግራይ]። እህቴ ‘ለምን ትግል አልሄደችም’ ብለው ነው እናቴ ያሰሯት” ሲሉ ተናግረዋል።

ህወሓት በበኩሉ ከዚህ በፊት ልጆች ለምን አልዘመቱም በሚል ወላጆችን የማሰር ምልክቶች ቢኖሩም አሁን ላይ ግን ይህ ቆሟል ይላል።

አቶ ክብሮም በርሀ ግን “ትግል መሄድ አለመሄድ የግል ምርጫ ነው፤ ወደ ትግል አልወጣህም ተብሎ ወላጅን ማሰር ግን በዓለም ታይቶ የሚታወቅ ነገር አይደለም” ይላሉ።

አቶ ክብሮም ልጅ አልዘምትም ካለ የታመሙ ወላጆች ሳይቀሩ ለእስር እንደሚዳረጉ የገለጹ ሲሆን ፍርድ ቤት የሚቀርቡበት ሁኔታ ሳይኖር በርካታ ሰዎችም ትምህር ቤቶች ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ ይናገራሉ።

ሌላኛው ቢቢሲ ያነጋገረው የትግራይ ክልል ነዋሪ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉ ገልጾ ከእነዚህም መካከል አንዱ ወላጆች ልጆቻቸውን ለትግል እንዲልኩ መገደዳቸው መሆኑን ይገልጻል።

ለደኅንነቱ ሲባል ስሙን የማንጠቅሰው የትግራይ ክልል ነዋሪ፤ “ልጆቻችሁን አዋጡ እየተባልን ነው። መስተዳድር የለንም” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል። via EBC

Exit mobile version