እነ ኤርሚያስ ለገሰን አማራ ምን ቢበድላቸው ነው በዚህ መጠን ሊበቀሉት ፈለጉ?

እነ ኤርሚያስ ለገሰ አርብ ምሽት አንድ ፕሮግራም ሰርተዋል። በዚህ ፕሮግራም ዋና ሀሳባቸው አማራ ክልል ላይ አዲስ መንግስት መመስረት የለበትም የሚል ነው። በፕሮግራሙ: 

1) አማራ ክልል ላይ ጭካኔና ውድመት እየፈፀመ ያለውን የትግሬ ወራሪ ኃይል TDF እያለ የትግሬ ወራሪ ራሱን የሚጠራበትን ይፋዊ ስሙ አድርጎ፣ ይህ ቡድን ምርጥ ተሞክሮ እንደሆነ ይናገራል። የትግራይ ወራሪ ኃይልን ጥሩ ምሳሌ ሲያደርግ፣ የትግራይን ወራሪ ኃይል እውቅና ሰጥቶ ትክክለኛና ሌላውም ምሳሌ ሊያደርገው የሚገባ ነው ሲል ምን ማለት እንደሆነ ግልፅ ነው። አማራን ለማጥፋት እየሰራ ያለን ኃይል ነው ምርጥ ተሞክሮ እያለ የሚያስተዋውቀው፣ የሚያሞካሸው። አማራው ላይ ይህን ያህል ውድመት እየፈፀመ ያለውን ቡድን ጠቅሶ አማራውም ይህን የሚመስል ቡድን ነው መንግስት ሊይዝ የሚገባው ይላል። ይህ ማለት የትግራይ ወራሪ ኃይል ትግራይ ላይ ስልጣን ለመያዝ ትክክለኛ ቡድን ነው ማለቱ ነው። በእርግጥም የትግራይ ወራሪ ኃይልን ሲጠቅስ ለአማራ ብሎ አይደለም። ለትግራይ ወራሪ ኃይል እውቅና ለመስጠት ነው። በአማራ ላይ ውድመት እየፈፀመ፣ ጭፍጨፋ እየፈፀመ ያለውን ቡድን እያሞካሸ ነው።

2) እጅግ በሀሰት መረጃ የአማራ ወጣት ወደመከላከያ ሰራዊት እንዳይቀላቀል እየመለሱት ነው ብለዋል። ሰሞኑን የአማራ አክቲቪስቶች፣ ፖሊስ ኮምሽን ገፅ፣ የአብንና የብልፅግና የፓርቲ ገፆች ወጣቱ መከላከያ ሰራዊት እንዲቀላቀል ሲወተውቱ አይተው ነው። ባለሀብቶች ሕዝብ ድረስ ሄደው ወጣቱ መከላከያ እንዲገባ እየቀሰቀሱ ነው። 360 የሚሰሩት ሰዎች ግን የአማራ ወጣት መከላከያ ሰራዊቱን እንዳይቀላቀል “ከሰራዊቱ እንዳይቀላቀል እየመለሱት ነው” እያሉ በሀሰት ዘመቻ ጀምረዋል። ይህ ሆን ተብሎ ወጣቱ ሰራዊቱን እንዳይቀላቀል ነው። 

3) ኢትዮ 360 ትህነግ አማራን ሲወጋ ዜና ሲሰራላቸውና ፕሮግራም ሲሰራ ነው የከረመው። ሀብታሙ አያሌውን ታመመ ይሉታል እንጅ ከኤርሚያስ ጋር መስማማት ስላልቻለ ነው። ኤርሚያስ ለትህነግ ሽፋን ሲሰጥ በቀጥታ ስርጭት ትህነግን እየተከላከለ እንደሆነ ሀብታሙ ተናግሮት በእነ ኤርሚያስ መንጋ ውርጅብኝ ወርዶበት ነው ከዛ በኋላ የጠፋው። ሀብታሙ የሕዝብ ጉዳይ ግድ ሲለው እነ ኤርሚያስ ግን ግዳቸው አይደለም። ትህነግን ሲደግፍ የከረሙት እነ ኤርሚያስ ዛሬ ታዲያ ጦርነት ይቁም ይላል። ደግሞ ጦርነቱ ቦታ ላይ ብዙ ሰው አልቋል፣ መቅበር ስላልተቻለ አስከሬኑ አልተነሳም እያለ ያወራል። ይሄን አንድ ጋዜጠኛ ሄዶ አይቶ ነገረኝ ይላል። ይህን ደግሞ የአማራው ወገን ያስመስለዋል። ጋዜጠኛው ሊሄድ የሚችለው በተለቀቁት ቦታ ነው።  አማራው ይህን ያህል ሰው በጦርነት አላለቀበትም። የሞተውም ሳይቀበር ሊቀር አይችልም። ያልተቀበረው የትህነግ ሀይል ስለመሆኑ በየቴሌግራም ገፁ ይለጠፋል። ዞሮ ዞሮ እነ ኤርሚያስ የተከፈላቸው ከትህነግ ስለሆነ የሞተውና የወዳደቀው የትህነግ ኃይል ግድ ቢለው ይሆናል ጦርነት ይቁም የሚለው። ይህን አንስቶ ጦርነት ካልቆመ ይላል። ወጣቱ ወደጦርነት አይሂድ ይላል። ትህነግ አማራው ድረስ መጥቷል። ወደ ጦርነት አትሂዱ እያሉ የሚቀሰቅሱት ሕዝቡን ከወረራ ለመጠበቅ ወደ መከላከያ፣ ወደ ልዩ ኃይል ወዘተ የሚቀላቀለውን ወጣት መሆኑ ነው። ክተት አዋጅ የታወጀለትን ወጣት እንጅ ወረራ የፈፀመውን የትህነግ ኃይል ጦርነት ይቅርባችሁ ብሎ ሊቀሰቅሰው አይችልም። 

4) እነ ኤርሚያስ አማራጭ ያደረጉት የሌለ ቡድን ነው። ያልተቋቋመ ቡድንን ይዞ አማራጭ ሲያስመስል አማራውን መንግስት አልባ ለማድረግ ነው። አማራው በደካማው ብልፅግናም ብዙ ጫና እየደረሰበት ነው። እነ ኤርሚያስ የሌለ ቡድን ጠርተው የመንግስት ጉዳይ የሚያነሱት መንግስት አልባ ለማድረግ ነው። 

5) እነ ኤርሚያስ አንድ ደካማ ጎን ይዘው መጥተዋል። የአማራ ብልፅግና መንግስት መመስረት የለበትም ብለዋል። የአማራ ብልፅግናን መተቸት ተገቢ ነው። ነገር ግን “ለውጥ” ከተባለ ጀምሮ የእነ ኤርሚያስን ያህል የአማራ ብልፅግናን የደገፈ የለም። እንዲያውም ቃል በቃል “ተስፋ ያለኝ በአማራ ብልፅግና ብቻ ነው” ብሏል። ዛሬ የአማራ ብልፅግናን መንግስት መመስረት የለበትም ያለው ከአማራ ብልፅግና ጋር የተለየ ጠብ ስላለው አይደለም። ይልቁንም ይህ አጀንዳ ለጠላት ስለሚጠቅም ነው። የአማራ ብልፅግናን የፈለገው ለሽፋን ነው። ትህነግ ኤርትራና አማራ ክልል ላይ ነው ትኩረት ያደረገው። እነ ጌታቸው ረዳ አገኘሁ ተሻገር ወዘተ እያሉ ብልፅግና ላይ ትኩረት የሚያደርጉ የሚያስመስሉት ብልፅግናን ብቻ ስለሚጠሉ አይደለም። የአገኘሁ ተሻገርን ጎተራ ቀድደው እህል አልዘረፉም። የአገኘሁ ተሻገርን ከብቶች ገድለው አልሄዱም። የአገኘሁ ተሻገርን ሀብት አልዘረፉም። 

ጠላታቸው የአማራ ሕዝብ ሆኖ ሰበብ አድርገው የሚመቱት ግን በእነ አገኘሁ ነው። እነ ኤርሚያስም ብልፅግናን ስለሚጠሉት አይደለም። የአማራ ብልፅግናንማ እጀጉን እናምነዋለን ብለው ቀስቅሰውለት ያውቃሉ። ከሌላው ብልፅግና የሚሻለው አማራ ብልፅግና ነው ብለው ነበር። ዛሬ ግን የኦሮሚያ ብልፅግና መንግስት መመስረት የለበትም ሳይሉ፣ የደቡብ ብልፅግና መንግስት መመስረት የለበትም ሳይሉ፣ የአፋር ብልፅግና መንግስት መመስረት የለበትም ሳይሉ የአማራ ብልፅግና መንግስት መመስረት የለበትም የሚሉት ከክልል ብልፅግናዎች የአማራ ብልፅግና ጋር ፀብ ስላላቸው አይደለም። ፀባቸው ከአማራ ሕዝብ ጋር ስለሆነ ነው።

ሁላችንም የምንተቸው፣ የአማራ ወጣት ሰልፍ ሲወጣበት የከረመው ብልፅግናን አሁን ዝም ያለው የጦርነት ወቅት ስለሆነ ነው። እነ አብን በአንድ ኮማንድ ስር ሆነው ከአማራ ብልፅግና ጋር እየሰሩ ያሉት ወቅቱ ከፖለቲካ ልዩነት ይልቅ መተባበርን ስለሚጠይቅ እንጅ አማራ ብልፅግና ስለተመቻቸው አይደለም። አብን፣ ፋኖ፣ ሕዝብ፣ ባለሀብቱ፣ ዳያስፖራው ከእነ ኤርሚያስ ያነሰ ለአማራ ስለሚቆረቆር አይደለም ከአማራ ብልፅግና ጋር ሆኖ ይህን ፈታኝ ወቅት ለማለፍ የፈለገው። እነ ኤርሚያስ ብልፅግናን ሰበብ አድርገው አጀንዳ ያመጡት ከአብንና ከሌሎቹ ተቆርቋሪ ሆነው አይደለም። 

እነ ኤርሚያስ ግን በዚህ ጦርነት ወቅት ሌላ ሰጣ ገባ ውስጥ ገብተን ጦርነቱን እንድንሸነፍ ለትህነግ እየሰሩ ነው። በዜናዎቻቸው መከላከያ ሰራዊቱ አማራን በመድፍ መታ እያሉ አስተላልፈዋል። አማራ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር እንዲያቆር ሰርተዋል። አሁን ደግሞ ከሁሉም ለይተው አማራ ክልል መንግስት መኖር የለበትም ብለዋል። 

ይሁንና ምንም ከሚገባው እጅግ ያነሰ ቢሆንም አማራ ከአራት አምስት ባይበልጡም የዘንድሮን ያህል ተወክሎ አያውቅም። አብን የተወሰኑ ሰዎችን ለፓርላማ፣ ከዚህ የተሻሉትን ለክልል ምክር ቤት አስመርጧል። እስከዛሬ እንደ አብን ያሉ የአማራ ወኪሎች በመንግስት ምስረታ ወቅት ተገኝተው አያውቁም። ዘንድሮ ቢያንስም ታማኝ የአማራ ልጆች የፌደራልም የክልልም ምክር ቤትን ተቀላቅለዋል። ብልፅግናም የአማራው ጉድ ነው። የአማራ ሕዝብ እዳ ነው። አሁን ከአማራ ብልፅግና ከፍ ያለ ጉዳይ አለው። እነ ኤርሚያስ ግን የአማራ ብልፅግናን አስታክከው እያጠቁት ያሉት አማራን ነው። ግን ይሄን ያህል ነክሰው የያዙት አማራው ምን ቢያደርጋቸው ነው? 

የእነ ኤርሚያስ ለገሰን በማር የተለወሰ መርዝ አጀንዳ አፉን ከፍቶ የሚሰማ አማራ ካለ እሱ አሁን መንቃት አለበት። ቢያንሰ በዚህ የጦርነት ወቅት ይህን መርዛቸውን ሲያርከፈክፉበት ዝም ማለት የለበትም።

(ጌታቸው ሽፈራው)

Leave a Reply