Site icon ETHIO12.COM

የአውሮፓ ሀገራት ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እያስመዘገቡ ነው

ሀገራቱ ባለፉት ሶስት አስርት አመታት ውስጥ አይተውት የማያውቁት የዋጋ ግሽበት ነው እያስመዘገቡ ያሉት።

ለዚህ የዋጋ ግሽበት መባባስ ዛሬም ድረስ መፍትሄ ያልተገኘለትና ዓለም በጠቅላላ ያናጋው የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት እንደሆነ ይገለፃል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በዩሮዞን ሀገራት በ30 እና 40 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ የዋጋ ግሽበት መመዝገቡን መረጃ መለዋወጣችን አይዘነጋም።

ከሰሞኑን ይፋ በሆነ መረጃ ደግሞ፥ በቼክ በሚያዝያ ወር ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት 14.2% ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ይህም ከ1993 ወዲህ (ከ29 ዓመታት በኃላ የተመዘገበ) ከፍተኛው የዋጋ ግሽበት ነው።

እንዲሁ በዴንማርክ አመታዊ የዋጋ ግሽበት በሚያዝያ ወር ወደ 6.7 % የጨመረ ሲሆን ይህም ከ1984 ወዲህ (ከ38 ዓመታት ወዲህ የተመዘገበ) ከፍተኛው የዋጋ ግሽበት ነው።

በግሪክ (የዩሮዞን ሀገር ናት) በሚያዝያ ወር 10.2 በመቶ ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት ተመዝግቧል፤ ይህም ከ1995 ወዲህ (ከ28 ዓመታት በኃላ) ከፍተኛው ነው።

በሀገራቱ የምግብ ፣ የኃይል (ነዳጅ) ፣ የትራንስፖርት ፣ የቤት ውስጥ መገልገያዎች ዋጋ ማሻቀቡ ነው የተጠቆመው።

” ጦርነት መቼ እንደሚጀመር እንጂ መቼና እንዴት እንደሚጠናቀቅ አይታወቅም ” ይባላል ፤ በሩስያ እና ዩክሬን መካከል የሚካሄደው ጦርነት ፤ ጦርነቱን ተከትሎ ምዕራባውያን በሩስያ ላይ የማዕቀብ ናዳ ማውረዳቸውና አሁንም ሌሎች ማዕቀቦችን ለመጫን እያቀዱ መሆናቸው ቀጣዩን ጊዜ ለዓለም ህዝብ እና ኢኮኖሚ እጅግ ፈታኝ እና አስቸጋሪ ያደርገዋል ተብሎ ተሰግቷል።

በተለይ በአፍሪካ እና ሌሎች አህጉራት ያሉ ታዳጊ ሀገራት የሚደርስባቸው ጫና ከሚታሰበውም በላይ ነው።

Via – @tikvahuniversity

Exit mobile version