Site icon ETHIO12.COM

አብዱላሂ ፋርማጆ ለአዲሱን ፕሬዝዳንት «ሁሉም ወገኖቼ እንዲደግፉህና እንዲጸልዩልህም እጠይቃለሁ»

ሀሰን ሼክ መሀሙድ በሶማሊያ ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ የተመረጡ የመጀመሪያ ሰው

– ሀሰን ሼክ መሀሙድ በሶማሊያ ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ የተመረጡ የመጀመሪያ ሰው

“ሰላም የሰፈነባት እና ከዓለም ጋር ሰላም ያላት ሀገር ለማድረግ እሰራለሁ”- አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት

ሀሰን ሼክ መሀሙድ በሶማሊያ ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ የተመረጡ የመጀመሪያ ሰው ናቸው

ትናንት ከዓመታት በኋላ በድጋሚ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ሃገራቸውን ሰላም ለማድረግ እንደሚሰሩ አስታወቁ፡፡

“ሰላም የሰፈነባት እና ከዓለም ጋር ሰላም ያላት ሀገር ለማድረግ እሰራለሁ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሀሰን ሼክ መሀሙድ 10ኛው የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡

ትናንት በሞርታርና በተኩስ እሩምታ ስትናጥ የዋለችው ሶማሊያ ታሪካዊ የተባለለት ፕሬዝዳንትዊ ምርጫ አካሂዳለች ፡፡

በምርጫው በስልጣን ላይ ነበሩትና የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም በማሰብ ምርጫው እንዳይካሄድ አጓተዋል በሚል የሚወቀሱት ፕሬዝዳንት መሃመድ አብዱላሂ (ፋርማጆ) ሽንፈት ገጥሟቸዋል፡፡

36 እጩዎችን ያሳተፈውና የማራቶን ምርጫ ነው የተባለለት የሶማሊያ ምርጫ በመጨረሻም በ214 ፓርላማ አባላት የላቀ ድምጽ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በፕሬዝዳንትነት መምረጣቸው ይፋ ሆኗል፡፡

በዚህም ሀሰን ሼክ መሀሙድ የሶማሊያ 10ኛው ፕሬዝዳንት ሆነዋል፡፡

አዲሱ ፕሬዝዳንት በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ምርጫ በስኬት መጠናቀቁን አድንቀዋል፡፡

ሀሰን ሼክ መሀሙድ “ፕሬዝዳንቱ (ፋርማጆ) ከጎኔ መገኘታቸው በእውነት የሚያስመሰግናቸው ነው፣ ወደ ፊት መሄድ እንጂ ወደ ኋላ መመለስ አይጠበቅብንም፤ ማንኛውንም ቅሬታ ማዳን አለብን” ሲሉም ተደምጠዋል።

ሶማሊያን “ሰላም የሰፈነባትና ከዓለም ጋር ሰላም ያላት ሀገር አደርጋታለሁ” ሲሉም ቃል ገብቷል ፕሬዝዳንቱ፡፡

ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ፋርማጆ በበኩላቸው በሼክ መሀሙድ መመረጥ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡ ለስኬታማነታቸው መልካሙን ሁሉ የተመኙም ሲሆን ድጋፍ እንዳይለያቸው ጠይቀዋል፡፡

“ወንድሜ ሀሰን ሼክ መሀሙድ የሀገራችን 10ኛ ፕሬዝዳንት ሆነው በመመረጡ እንኳን ደስ አለህ፤ ለስኬታማነትህ ሁሉም ወገኖቼ እንዲደግፉህ እና እንዲጸልዩልህም እጠይቃለሁ” ሲሉም ነው ፋርማጆ በትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩት፡፡

ሰላማዊ ምርጫ እንዲደረግ አስተዋጾ ያደረጉት አካላትን ሁሉ አስግነዋል ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መሀመድ ሁሴን ሮብልም ለተመራጭጩ ፕሬዝዳንት የደስታ መልዕክትን ልከዋል፡፡

“ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በድጋሚ የሶማሊያ ፌደራላዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ሆነው በመመረጥዎ እንኳን ደስ ያለዎት ለማለት እወዳለሁ። የጋራ በሆኑ የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርበን እንደምንሰራ እምነቴ ነው” ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ሀሰን ሼክ መሀሙድ ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ፋርማጆን በማሸነፍ በሶማሊያ ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ የተመረጡ የመጀመሪያ ሰው ናቸው፡፡

አዲሱ ፕሬዝዳንት እ.ኤ.አ ከመስከረም 2012 እስከ የካቲት 2017 ድረስ በፕሬዝዳንትነት ማገልገላቸው የሚታወስ ነው፡፡

በወቅቱ ከነበረው የኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመቀናጀትም በተለይም ሽብርተኝነትን ከመዋጋት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ስራ እንደሰሩ ይነገርላቸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለረሃብ የሚያጋልጥ ከባድ ድርቅን ጨምሮ ብዙ የተወሳሰቡ ችግሮች ያሉባት ሀገረ ሶማሊያ ለአዲሱ ፕሬዝዳንት ቀላል የቤት ስራ ይዛ እንደማትቆይ እየተነገረ ነው፡፡

አዲሱ ፕሬዝዳንት ሰላማዊ ሶማሊያን እውን ለማድረግ ለወራት በዘለቀው የፖለቲካ ትርምስ እና የእርስ በርስ ሽኩቻ፣ በአስፈጻሚ ደረጃም ሆነ በማዕከላዊ መንግስት እና በክልል ባለስልጣናት መካከል ያለውን የግንኙነት መሻከር ማስተከከል ይጠበቅባቸዋልም ተብሏል፡፡

የሶማሊያ ዓለም አቀፍ አጋሮች ምርጫ መዘግየቱ፣ የፖለቲካዊ ሽኩቻ መኖሩ እንዲሁም ከአስር አመታት በላይ መንግስትን ለመጣል ሲዋጉ ከነበሩት የአልሸባብ አማፂያን ጋር የሚደረገው ውጊያ ሀገሪቱን ወደለየለት ቀውስ እንዳያስገባት ደጋግመው ሲያስጠነቅቁ መቆየታቸው የሚታወስ ነው

Source Alain

Exit mobile version