Site icon ETHIO12.COM

ንግድ ባንክ ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ ከ50 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለ2014/15 ዓ.ም የምርት ዘመን ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ ከ50 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን አስታውቋል።

መንግስት የግብርና ዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ ሰፊ ዕቅድ ይዞ እየሰራ ሲሆን፤ ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ የግብርና ግብዓቶችን ማሟላት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በተለይ ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ጂኦ-ፖለቲካ ምክንያት እየተፈተነ ያለውን የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር ለመፍታት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑም ነው የሚገለጸው፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ ባንኩ በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ምክንያት በግብርናው ዘርፍ የተያዘው አገራዊ እቅድ እንዳይስተጓጉል ትልቅ ስራ ሰርቷል ብለዋል።

የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ዓለምን የፈተነ የዋጋ ንረት ማስከተሉን ጠቅሰው፤ ከፍተኛ የማዳበሪያ አምራች የሆኑት የሁለቱ አገሮች ግጭት የአፈር ማዳበሪያ ዋጋና አቅርቦት ላይ ተግዳሮት መፍጠሩን ተናግረዋል።

ሌሎች የአፈር ማዳበሪያ አምራች አገራትም በጦርነቱ ምክንያት ምርታቸውን ለገበያ በማቅረብ ረገድ ችግር እንደገጠማቸውም ገልጸዋል።

በዚህም ከጦርነቱ በፊት 700 ዶላር ይሸጥ የነበረው የአንድ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ጦርነቱ እንደተጀመረ ከእጥፍ በላይ መጨመሩን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ያለው የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር እስከ አራት እጥፍ ጭማሪ ማሳየቱንም ነው የጠቀሱት።

ባንኩ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ከሚያደርግባቸው ዘርፎች አንዱ ግብርና መሆኑን ጠቅሰው፤ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ትልቅ ድርሻ እንደሚይዝ ተናግረዋል። ነገር ግን የአፈር ማዳበሪያ አቅራቢ አገራት እንደ ከዚህ ቀደሙ በዱቤ ለመሸጥ አለመፈለጋቸው ትልቅ ፈተና ነበር ብለዋል። አምና በዱቤ የተገዛው የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ እየተከፈለ ባለበት በዚህን ወቅት የማዳበሪያ ዋጋ እጅግ መናሩ ደግሞ ችግሩን ውስብስብ እንዳደረገው አብራርተዋል፡፡

ኢዜአ እንደዘገበው የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ቢጨምርም ከዚህ የሚቀድም አንገብጋቢ ጉዳይ ባለመኖሩ ለሌሎች ዘርፎች ሊውል የነበረ ገንዘብ ጭምር ወደ ግብርናው እንዲዞር መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ ከ50 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ገልጸዋል። በከፍተኛ ጥረትና ርብርብ ከውጭ የተገዛው ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ መደረጉን ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ በተለይ ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል። via OBN

Exit mobile version