Site icon ETHIO12.COM

የሩስያ ጦር ሊማን ያዘ፤ ዩክሬን በጥቁር ባሕር ወደብ ጎተሮች ያከማቸችውን እህል እንድትሸጥ ፑቲን እወያያለሁ አሉ

የሩሲያ ጦር በምሥራቃዊ ዩክሬን ስልታዊ ጠቀሜታ አላት የተባለች ከተማ መኦቅጣጠሩ ትገለጸ። ፑቲን ዩክሬን በጥቁር ባህር ወደብ ጎተራዎቿ ያከማቸችውን እህል ወደ ሌለኦች አገራት መላክ በምትችልባቸው አማራጮች ላይ ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውን አስታወቁ።

የሩሲያ ጦር በምሥራቃዊ ዩክሬን ዶንባስ ግዛት የምትገኘውን ሊማን የተባለች አነስተኛ ከተማ መቆጣጠሩን አረጋገጠ። የጦሩ ማረጋገጫ የተሰማው ከዩክሬን መገንጠልን የሚያቀነቅኑ የሩሲያ ደጋፊ ታጣቂዎች ስልታዊ ጠቀሜታ አላት የተባለችን ከተማ ትላንት አርብ እንደተቆጣጠሩ ከገለጹ በኋላ ነው። የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢጎር ኮናሼንኮቭ “በዶኔትስክ ሕዝቦች ሪፐብሊክ ኃይሎች እና በሩሲያ ጦር ጥምር እርምጃ የክራስኒ ሊማን ከተማ ከዩክሬን ብሔርተኞች ሙሉ በሙሉ ነጻ ወጥታለች” ብለዋል።የዩክሬን ጦር ከተማይቱን ተቆጣጥሮ ለመቆየት በተደረገ ውጊያ ከፍተኛ መሰናክል እንደገጠመው በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል። የሊማን ከተማ ምሥራቃዊ ዩክሬንን ከደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል የሚያስተሳስሩ የባቡር እና የአውራ ጎዳና መሠረተ-ልማቶች የሚገኙባት በመሆኗ ስልታዊ ጠቀሜታዋ ከፍ ያለ ነው። ሩሲያ ከተማይቱን መቆጣጠሯ በዶንባስ ግዛት በዩክሬን ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ወደሚገኙት የዶኔትስክ እና ሉሐንስክ ከተሞች ለመገስገስ አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። በሉሐንስክ ግዛት በሚገኙ ሁለት ከተሞች ዛሬ ቅዳሜ ውጊያ እየተደረገ ይገኛል። የሩሲያ ኃይሎች በከበቧት የሲቪየርዶኔትስክ ከተማ ብቻ በጦርነቱ 1,500 ሰዎች መገደላቸውን የከተማዋ ከንቲባ ተናግረዋል። ከጦርነቱ በፊት የ100,000 ሰዎች መኖሪያ በነበረችው በዚችው ከተማ የቀሩት ከ12,000 እስከ 13,000 ገደማ ብቻ ሲሆኑ 90 በመቶ ሕንጻዎቿ መውደማቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።

ፑቲን ዩክሬን እህል መላክ በምትችልባቸው አማራጮች ላይ ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውን ገለጹ

ዩክሬን በጥቁር ባሕር ወደቦች በሚገኙ ጎተራዎች የተከማቸ እህል ወደ ሌሎች አገራት መላክ በምትችልባቸው አማራጮች ላይ ለመነጋገር ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ፈቃደኛነታቸውን አሳዩ። ጽህፈት ቤታቸው ክሬምሊን ባወጣው መግለጫ እንዳለው ፑቲን ዛሬ ቅዳሜ ከጀርመኑ መራሔ-መንግሥት እና ከፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ጋር ባደረጓቸው የስልክ ውይይቶች በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውን አሳውቀዋል። የክሬምሊን መግለጫ “የዩክሬን እህል ከጥቁር ባህር ወደቦች ወደ ውጪ መላክን ጨምሮ እህል ያለገደብ ወደ ውጪ የሚላክባቸውን አማራጮች ለማግኘት ሩሲያ በበኩሏ ፈቃደኛ ነች” ብሏል። ሩሲያ የተጣሉባት ማዕቀቦች ከተነሱ ወደ ውጪ የምትልከውን የአፈር ማዳበሪያ እና የግብርና ምርቶች ለመጨመር ፈቃደኛ እንደሆነች ፑቲን ለጀርመኑ መራሔ-መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ እና ለፈረንሳዩፕሬዝደንት ኤማኑዌል ማክሮ ተናግረዋል። ፑቲን ይኸንኑ ጉዳይ ከዚህ ቀደም ከጣልያን እና ከኦስትሪያ መሪዎች ጋር ባደረጉት ንግግር አንስተው ነበር። ዩክሬን እና ምዕራባውያን አገሮች ሩሲያ ዩክሬንን በመውረሯ የተፈጠረውን ዓለም አቀፍ የምግብ ቀውስ የፑቲን መንግሥት እንደመሣሪያ ተጠቅሟል ሲሉ ይወነጅላሉ። ከጦርነቱ በኋላ የእህል፣ የምግብ ማብሰያ ዘይት፣ የነዳጅ እና የማዳበሪያ ዋጋ አሻቅቧል። ፑቲን ምዕራባውያን አገራት ለዩክሬን የጦር መሳሪያ መላካቸውን መቀጠላቸው አደገኛ እንደሚሆን ሾልዝ እና ማክሮንን አስጠንቅቀዋል ተብሏል። በክሬምሊን መግለጫ መሠረት ፕሬዝዳንት ፑቲን የጦር መሳሪያ አቅርቦቱ ሁኔታውን የበለጠ የማያረጋጋ እንዲሁም ሰብዓዊ ቀውሱን የሚያባብስ እንደሚሆን ተናግረዋል። የሩሲያ ፕሬዝደንት ከዩክሬን ጋር የተቋረጠውን ድርድር እንደገና ለመጀመር ፈቃደኛ መሆናቸውን እንዳሳወቁ ክሬምሊን ገልጿል። DW


Exit mobile version