Site icon ETHIO12.COM

የአየር ወለድ – በአዲስ ክብር

-የ61 አመቱ የእድሜ ባለፀጋ የአየር ወለድ ት/ቤት አሁናዊ ገፅታ፡፡

በኮማንዶና አየር ወለድ ኃይል ማሰልጠኛ ማዕከል ስር ካሉ ትምህርት ቤቶች መካከከል አንዱ የአየር ወለድ ትምህር ቤት ነው፡፡ ይህ ትምህርት ቤት ተዋጊ አየር ወለዶችን በማሰልጠን ለ61 አመታት በብቸኝነት ያገለገለ የሀገር ባለውለታ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ አሁንም ይህንን ተግባሩን አጠናክሮ እየቀጠለ ሲሆን በአሁኑ ጊዜም ወደ ተሻለ ደረጃ እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡

በአየር ወለድ ትምህርት ቤቱ ከትላንት እስከ ዛሬ ያሉ አሰልጣኞች እና አመራሮች እንዲሁም አዲስ እየገቡ ያሉ ተተኪ ሙያተኞች ታሪኩን እንዲህ አውገተውናል፡፡

በ1959 ዓ/ም ወደ ሠራዊቱ በመቀላቀል በአየር ወለድ ሰልጥነው ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡ ሌ/ኮሎኔል ደስታ ኃ/ገብርኤል ይባላሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜም በሙያቸው ትምህርት ቤቱን ለማዘመን በሚደረገው ስራ ላይ የድርሻቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡

በዚህ የአየር ወለድ ትምህርት ቤት ስልጠና የወሰዱት ሌ/ኮ ደስታ እንደነገሩን የአየር ወለድ ትምህርት ቤት የተቋቋመው በህዳር 19 ቀን 1953 ዓ/ም ነው፡፡ በወቅቱም 183 ባለሌላ ማዕረግተኛ እና አስር መኮንኖች ከሠራዊቱ ተመልምለው እስራኤል ሀገር በመሄድ የአየር ወለድ ስልጠና በመውሰድ ተመልሰው ሲመጡ የአየር ወለድ ትምህርት ቤት እንዲመሠረት ተደርጓል።

በዚህ ሁኔታ የተመሠረተው የአየር ወለድ ትምህርት ቤት ተዋጊ አየር ወለድ ሰራዊት ሲያሰለጥን ቆይቶ በ1969 ዓ/ም ስራ አቁሞ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በ1973 ዓ/ም እንደገና ተከፍቶ የማሰልጠን ተግባሩን ማከናወን እንደጀመረ ሌ/ኮ ደስታ ነግረውናል።

በአንድ ሻምበል የተጀመረው የአየር ወለድ ክፍል ምስረታም በወቅቱ ወደ ብርጌድ ማድረስ የተቻለ ሲሆን ቀስበቀስም የአየር ወለድ ሠራዊት በክፍለ ጦር ደረጃ ማደራጀት እንደተቻለም ያስረዳሉ፡፡

ትምህርት ቤቱ በ1983 ዓ/ም በነበረው የመንግስት ለውጥ ምክንያት ተዘግቶ የቆየ ሲሆን ከ15 ዓመት በኋላ እንደገና በ1998 ዓ/ም በቀድሞ የአየር ወለድ አባላት አመካኝነት እንደገና ተከፍቶ የአየር ወለድ ከፍልን በማሰልጠን መልሶ ማደራጀት ተጀመረ፡፡

የአየር ወለድ ት/ቤት በ1953 ዓ/ም ከተመሰረተበት ወቅት ጀምሮ ከተራ ተዋጊ እስከ ከፍተኛ አመራሮችን ማፍራት የቻለ ት/ቤት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህልም እነ ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ፣ ጄኔራል ተመስገን ገመቹ፣ ጄኔራል ተስፋዬ ኃ/ማርያም፣ ጄኔራል ጌታቸው ናደውን እና በአሁኑ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ የሚገኙትን የኮማንዶና የአየር ወለድ ኃይል አዛዥ ክቡር ሌ/ጄኔራል ሹማ አብደታን እና የመከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወደር የሌለው የጥቁር አንባሳ ሜዳይ ተሸላሚ ክቡር ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን ያፈራ የሀገር ባለውለታ ትምህርት ቤት ነው፡፡

ይህን ታሪክ ያወጉን ሌ/ኮሎኔል ደስታ ኃ/ገብርኤል ከ55 አመት በኋላም የመከላከያን የዘመናዊ ሠራዊት ግንባታን ለማሳካት በአየር ወለድ ት/ቤት እየተጉ ነበር ያገኘናቸው፡፡

የዛሬ 55 አመት የተመገብኩበትን ቤት ተመልሼ ዛሬ ልመገብበት በቅቻለው፡፡ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ ከዛሬ 61 ዓ/ም በፊት እንደተገነባ ቤቶቹ ጭምር ሳይቀር እስከ አሁን አገልግሎት ላይ ቆይቷል፡፡

አሁን ግን መከላከያ ባደረገው ሪፎርም እና ሠራዊትን ለማጠናከር ባለው ራዕይ ትምህርት ቤቱን በዘመናዊ መንገድ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ የስልጠና ወረዳ፣ የጅምናዚዬም መስሪያ መሰናክሎች ሳይቀሩ በአዲስ መልክ ተሰርተዋል፡፡

ዛሬ ኖሬ ትምህርት ቤቱ እንደ አዲስ ተገንብቶ ለውጥ ሲያሳይ በአይኔ በማየት ታላቅ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ ዘመኑን በሚመጥን ደራጃ ለሀገራችን የዘመነ የማይበገር ጠንካራ ተዋጊ የአየር ወለድ ሠራዊትን ማፍራቱን አጠናክሮ ይቀጥልበታል ብለውናል፡፡

የትምህርት ቤቱ ዋና አዛዥ የሆኑት ኮሎኔል አለማየሁ ጨዋቃ በበኩላቸው ከተቋማዊ ሪፎርሙ በኋላ በርካታ ስራዎች በማሰልጠኛው ተሰርተዋል፡፡ አሁንም ስራው ተጠናክሮ ቀጥለዋል፡፡ ት/ቤቱ በርካታ ተዋጊ አየር ወለዶችንም አሰልጥኗል፡ ያሰለጠናቸው ተዋጊ አየር ወለዶችን በህግ-ማስከበርና በህልውና ዘመቻው በመሳተፍ ውስብስብ ግዳጆችን በብቃት እና በታላቅ ጅግንነት የላቀ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡

ለትምህርት ቤት ግንባታው ተቋሙም ከፍተኛ ትኩረት በማድርግ በአንክሮ እየተከታተለ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ልክ እንደትላንቱ ብቻም ሳይሆን በተሻለ ደረጃ በየትኛውም ቦታ የትኛውንም ምድራዊ ፈተና በማለፍ ሀገራዊ ግዳጁን የሚወጣ አየር ወለድ ለመገንባት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

የትምህርት ቤቱ ግንባታ አጠቃላይ ጥራት ተቆጣጣር የሆኑት መቶ አለቃ ኢ/ር በቃል ካሳሁን የትምህርት ቤቱ የጂምናዝየም ወረዳ ወቅቱን በመጠነ እና በዘመናዊ መንገድ በጥራት ተገንብቶ ማለቁን ገልፀውልናል፡፡

በእንጨት ተሰርተው የነበሩ በኮንክሪትና በብረት ተቀይረዋል፡፡ ይህም ከ50-60 አመት እንደሚያገለግል ታሳብ ተደርጎ የተገነባ ግንባታ መሆኑን ተናግሯል፡፡

የጥራት ተቆጣጣሪው ኢንጂነር በቃሉ ካሳሁን እና የፕሮጀክቱ ሳይት መሪ ፶/አለቃ ኢንጂነር ፋንታሁን ተማረ በጋራ በገለፁልን መሰረት የትምህርት ቤቱን ደረጃ ለማሳደግ እና ለስልጠና ምቹ ለማድረግም በአጠቃላይ ሰላሳ አራት ብሎክ ቤቶች በግንባታ ላይ ይገኛሉ፡፡

ግንባታውም የአሰልጣኝ፣ የመኮንኖች፣ የሰልጣኞች መኖሪያ፣ ቢሮዎች፣ ካፍቴሪያ፣ ሆስፒታል፣ ትላልቅ መጋዘኖችን፣ የአይ ቲ ክፍል፣ ቤተ-መፅሐፍት፣ የመማሪያ ክፍል የመሣሰሉትን ያካታተ ዘመናዊ ግንባታ ነው፡፡

፶/አለቃ ኢንጅነር ፋንታሁን ተማረ ይህንን ግንባታ እዚህ ደረጃ ያደርሰነው በብዙ ፈተናዎችን አልፈን ባደረግነው ከፍተኛ ጥረት ነው፡፡ የሚመለከተው አመራርም ማድረግ ያለበትን ጥረት ሁሉ አድርጓል፡፡

እንደሚታወቀው ሀገራችን ከነበረችበት ሁኔታ አኳያ ግንባታውን በሚፈለገው ደረጃ ለማስኬድም አዳጋች ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ ሆኖም ግን ይህንን ተቋቁመን ግንባታውን ከ 70% በላይ አድረሰናል፡፡

በመጀመሪያ መሰረቱን ከማነጽ ጀምሮ የመሬቱ ተፈጥሮያዊ ሁኔታ ከታች አለታማ እና ድንጋያማ ስለነበረ ከማሽነሪ ጀምሮ ብዙ መስዋዕትነት አስከፍሎናል በማለት ሂደቱን በማስታወስ አውግተውናል፡፡

ፕሮጀክቱ ትውልድ የሚገነባበት ትልቅ ተቋም ነው፡፡ ዝም ብሎ የይድረስ የሚሰራ ስራ አይደልም፡፡ ከዚህ አኳያ ተቋማችንና እና ሀገራችን የጣሉብን ትልቅ ኃላፊነት መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ በዚህ መንፈስ ግንባታውን በጥራት እየሰራን ነው፡፡ ከጥቂት ወራቶች በኋላም ግንባታውን ሙሉ በሙሉ ጨርሰን እናሰረክባለን ብለውናል ሁለቱም ባለሙያዎች፡፡

፶/አለቃ ኢንጂነር ፋንታሁን እኛ ኢንጂነሮችም ወታደሮችም ነን፡፡ እንገነባለን ሀገራችን በጠላት ስትነካ ደግሞ እንዋጋልን፡፡ ወታደር ማለት በሁለት በኩል የተሳለ ሴይፍ ነው፡፡ ሰዎች ወታደርን ከጦርነት ጋር ብቻ ነው የሚያይዙት። ወታደር የከፍተኛ ሙያ ባለቤት ነው፡፡ እኛም የዚሁ አካል ነን በማለት ስለውትድርና ሙያ ክብርን ከፍታን ገልፀዋል፡፡

ማስተላለፍ የሚፈልገው መልዕክት ይላል ኢንጂነር ፋንታሁን በሀገር መከላከያ ውስጥ ዶክተሮች፣ ፓይለት፣ ኢንጂነሮች፣ መሀንደሶች፣ የግብርና፣ የህዝብ ግንኙነት፣ ምርጥ የማኔጅመንት ሰራተኞች፣ አካወንታንት፣ አርክቲክቸሮች ወዘተ… አሉ ወታደር ሙያው መተኮስ ብቻ አይደለም፡፡

ውትድርና እውቀት የሚገኝበት፣ የፈጠራ ሰዎች ያሉበት በመሆኑ መከላከያ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች የሚፈልቁበት ተቋም ነው፡፡ በእርግጥ ማንኛውም ሰው በጥረቱ የፈለገውን መሆን ይችላል፡፡ ሁሉም ሰው ግን ወታደር መሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም ውትድርና ማንም ሰው ፈልጎ የማያገኘው ሙያ ነው፡፡ ምክንያቱም ዕድሜ፣ አካላዊ ብቃት፣ የዲሲፕሊን ደረጃ ወዘተ… ይገድበዋልና፡፡

ውትድርና ታሪክ የሚፃፍበትም አውድ ነው፡፡ ታላለቅ ሰዎች የሚፈልቁበትም ነው፡፡ በመሆኑም ችሎታና ብቃቱ ያለው ዕድሜው የሚፈቅድለት ሰው ሁሉ ወደ ተቋሙ በመግባት በእውቀቱ ተጠቅሞ ጥሩ ስራ በመስራት ሀገርን ለትውልድ ማስተላለፍ አለበት፡፡

ሰው ማለት ለግሉ የኖረ ሳይሆን ለህዝብ እና ለሀገር ኖሮ የማይደበዝዝ ታሪክ የፃፈ ሰው ነውና እኛ እናልፋለን፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው ሰርተን ለቀጣዩ ትውልድ ታሪክ አስቀምጠን ማለፍ ነው፡፡

እኛ ለሀገራችን ወታደር ሆነን በአንድ እጅ ክላሽ ይዘን አሁን እየገነባን ያለነው ለትውልድ የሚበቃ ግንባታ አንዱ የታሪካችን አካል ነው፡፡ ነገም ሌላ ታሪክ እንሰራለን በማለት ፶/አለቃ ኢንጂነር ፋንታሁን መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

የአየር ወለድ ትምህርት ቤት ግንባታ የመከላከያ መሀንዲስ ዋና መምሪያ ራሱን ችሎ ከሚገነባቸው ግንባታዎች መካከል አንዱ በመሆኑ በዚህም እንኮራለን ሲሉ ሁለቱም ወታደር ኢንጂነሮች ተናግረዋል፡፡

ለሀገር ዕድገትና ብልፅግና ደግሞ ሠራዊት ወሳኝ ነው፡፡ ጠንካራ ሠራዊት ለሀገራዊ ልማት ለዜጎች ብልፅግና ጠንካራ መሰረት ነው፡፡ ጠንካራ ሠራዊት ያለው ሀገር የእድገትና ልማት እቅድን ያለምንም የሰላም ስጋት ማሳካት ይችላል፡ በመሆኑም ሁላችንም ይህንን መልዕክት ተገንዝበን ሀገራችንን ባለን ሙያ እና ችሎታ በታማኝነትና በቅንነት እናገልግል መልዕክታችን ነው፡፡

አብዱራህማን ሀሠን
ፎቶግራፍ አብዱራህማን ሀሠን defence FB

Exit mobile version