ወደር የሌለው የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጀግና! ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ኃብተማርያም

የኢትዮጵያ ክብርና ነፃነት በቆራጥ ልጆቿ መሥዋዕትነት የተገኘ መሆኑ የማያጠያይቅ ነው፡፡ ለሀገራችን ሠላም፣ ለሠንደቅ ዓላማችን ክብር ሲሉ መሥዋዕትነት ከከፈሉ ጀግና ኢትዮጵያውያን መካከል ደግሞ ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ሃብተማርያም አንዱ ናቸው፡፡ ዛሬ ጳጉሜ 2 ለኢትዮጵያ ሀገራቸው መሥዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖች የሚታሰቡበት እና የሚዘከሩበት ቀን እንደመሆኑ በዛሬው የአውደ ሰብ አምዳችን ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ሃብተማርያምን ባለታሪካችን አድርገናቸዋል፡፡

ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማርያም ተወልደው ያደጉት በጉራጌ ዞን ከቸሀ ወረዳ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሲሰ መንደር ውስጥ ነው፡፡ እስከ 8ኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን እዚያው እምድብር ከተማ የተማሩ ሲሆን፣ በ1948 ዓመተ ምህረት የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተፈትነው በጥሩ ውጤት አጠናቀዋል፡፡

የ8ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም የአምቦ እርሻ ልማት ትምህርት ገብተው ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፤ በኋላም ወደ ጦር አካዳሚ በመግባት የ3 ዓመት ወታደራዊ ሳይንስና የአካዳሚ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በስመጥሩው የምርጥ መኮንኖች ማፍሪያ በሆነው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ (ሀረር) ጦር አካዳሚ ነው። 

ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ በመቀጠልም የጦር ሠራዊቱን በመቀላቀል የአየር ወለድ ሥልጠና የወሰዱ ሲሆን፤ ሙያቸውን ለማጠናከርም በእስራኤል የኮማንዶ ትምህርት፣ አሜሪካ የልዩ ኃይል፣ ሞስኮ እና ህንድን ጨምሮ በተለያዩ የውትድርና ሥልጠናዎችን ራሳቸውን አብቅተዋል፡፡  

በ1969 ዓ.ም የሶማሊያ ተስፋፊ ሃይል ኢትዮጵያን ወሮ ከጅግጅጋ እና ጎዴ አልፎ መጥቶ እስከ ሜኢሶ ድረስ በመቅረብ መሬቱን በፈንጅ አጥሮ ነበር፡፡ ይህ መሰናከል ለሠራዊቱ እና ለህዝቡ መሰረታዊ የሆኑ ነገሮች ለማቅረብ በጣም ችግር ፈጠረ፡፡ ይህን ችግር ለመፍታትም የሶማሊያ ግዛት ክልል ውስጥ ዘልቆ መግባት እና ፈንጅ መቅበር አንድ መንገድ የነበረ ሲሆን፣ ይህ ግዳጅም ለብ/ጀነራል ተስፋዬ ተሰጠ፡፡ እሳቸው የሚመሩት ቡድንም ድንበር አቋርጦ ሶስት ቀን እና ሌሊት ፈንጂ በመቅበር የጠላትን እንቅስቃሴ አወከ፤ ትልቅ ውጤትም ማምጣት ተቻለ፡፡

በ1970ዎቹ መግቢያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጠለፋ ምክንያት በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ችግር ውስጥ ገብቶ የነበረ ሲሆን፣ በዚህም አንዳንድ ቦታዎች ላይ በረራ በመቆሙ ድርጅቱ ለሠራተኞቹ እንኳን ደሞዝ መክፈል ያልተቻለበት ሁኔታ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ ችግሩን ለመፍታትም የበረራ ደህንነት እንዲቋቋም መንግሥት ሲወስን የድህንነት ቡድን እንዲያቋቁም ለብ/ጀነራል ተስፋዬ ኃላፊነት ተሰጣቸው፤ እሳቸውም የሰለጠኑ የደህንነት አባላት ከአውሮፕላኖቹ ጋር እንዲጓዙ በማድረግ ችግሮቹን መፍታት ችለዋል፡፡

See also  “ኢቦላ” – ለድሆች የቀረበ የወረርሽኝ ኢንቨስትመንት!?

በሰላም ለመኖር መሰረቱ ሥነ- ሥርዓት ነው የሚሉት ብርጋዴን ጄኔራል ተስፋዬ ሀ/ማርያም “በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ ጥይት በሚፈነዳበት ቦታ ሁሉ እኔ ያልተሳተፍኩበት በጣም ጥቂት ሲሆን፣ አብዛኛው በተሳተፍኩባቸው ቦታዎች በድል ወይም በስኬት ነው የተጠናቀቁት” በማለት ስለ ህይወት ተሞክሮአቸው ይገልጻሉ፡፡

በ1970ዎቹ እርሳቸው የሚመሩት የአየር ወለድ ጦር ናቅፋ ተራራ ላይ ለ6 ወራት በጠላት ተከቦ በህይወት ቆይቶ የጠላትን ከበባ ሰብሮ በህይወት እንደወጣ ሲነገሩ፣ ይህ ታሪካዊ ክስተት በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የተፈጠረ የአየር ወለድ ሠራዊት ጀብድ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡   

ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ሃ/ማርያም በሶማሊያ ጦርነት ወቅት ለሠሩት ገድል እና በናቅፋ በሰሩት ጀብድና የአመራር ብቃት ከሻለቃነት ወደ ኮሎኔልነት በአንዴ ማደግ የቻሉ ወይም በ5 ዓመት የሚደረስበትን ወታደራዊ ማዕረግ በፈጥነት ማግኘት የቻሉ ጀግና ናቸው፡፡ ጀነራሉ በኢትዮጵያ ታሪክ ለማንም ወታደር እና መኮንን ተሸልሞ የማያውቀውን “ወደር የሌለውን የሕብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጀግና ወታደራዊ ሜዳሊያም” ተሸልመዋል፡፡

ማንም ሰው ብቁ አሰልጣኝ ካገኝ አየር ወለድ መሆን እንደሚችል የሚገልጹት ብ/ጀነራል ተስፋዬ፣ እሳቸው ከሀረር ጦር አካዳሚ በመሰረታዊ ውትድርና ከሰለጠኑ በኋላ የአየር ወለድ ሥልጠና ያገኙት ከእስራኤሎች እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ 

“ኢትዮጵያ በየዘመኑ ጀግና የምታፈራ የጀግኖች ሀገር ናት” የሚሉት ብ/ጀነራል ተስፋዬ ሀብተማርያም ለዚህም መላው የሀገሪቱ ህዝብ ትልቅ ኩራት ሊሰማውና ተስፋ ሊሰንቅ እንደሚገባም ይናገራሉ።

“የሀገሪቱን ዕድገት ጎታች ሆኖ ፈተና ውስጥ የከተተን ነገር የእናት ጡት ነካሽ በሆኑ ከሀዲዎች በየጊዜው የሚከፈትብን ጦርነት ነው፤ ይህንን የህልውናችንን ጠላት ለመዋጋት ደግሞ ወጣቱ ከጦር ሜዳው ተሳትፎ ባልተናነሰ መልኩ መነሳትና አንድነት መፍጠር ይኖርበታል” ይላሉ። (ኢዜአ)


Leave a Reply