Site icon ETHIO12.COM

የዲጂታል መገበያያ ገንዘብ መጠቀም ዕውቅና ያልተሰጠው መሆኑን ብሄራዊ ባንክ አስታወቀ

– ህብረተሰቡ ከእንደዚህ አይነት ሕገ-ወጥ ተግባር እራሱን እንዲጠብቅ አሳስቧል።

የዲጂታል መገበያያ ገንዘብ ለግብይት ወይም ለክፍያ መጠቀም ዕውቅና ያልተሰጠው መሆኑን ብሄራዊ ባንክ አስታወቀ

በኢትዮጵያ እንደ ክሪፕቶ ከረንሲ፣ ቢትኮይን እና የመሳሰለው ምናባዊ ንብረትን (ዲጂታል መገበያያ ገንዘብ) ለግብይት ወይም ለክፍያ መጠቀም ዕውቅና ያልተሰጠው ድርጊት መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።

የዲጂታል መገበያያ ገንዘብን ለግብይት ወይም ለክፍያ መጠቀም ዕውቅና ያልተሰጠው ድርጊት በመሆኑ ህብረተሰቡ ከእንደዚህ አይነት ሕገ-ወጥ ተግባር እራሱን እንዲጠብቅ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ የገንዘብ መደብ ብር እንደሆነና በብሔራዊ ባንክ በሌላ አኳኋን ካልተፈቀደ በስተቀር በሀገሪቱ የሚከናወኑ ማናቸውም የገንዘብ ግንኙነቶች ሁሉ የሚከፈሉት በብር እንደሚሆን የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000 በግልጽ እንደሚደነግግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።

በክፍያ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 718/2003 መሠረት በየትኛውም የክፍያ መፈጸሚያ ሰነድም ሆነ ሥርዓት ያለ ብሔራዊ ባንክ ፍቃድ የገንዘብ ዝውውርም ሆነ ገንዘብ ነክ አገልግሎት መስጠት አይቻልም።

ነገር ግን ከጥናት ለመረዳት እንደተቻለው በአሁኑ ወቅት ከህግ እውቅና ውጪ የክሪፕቶ ከረንሲ፣ እንደ ቢትኮይን እና የመሳሰሉት የምናባዊ ንብረት (ዲጂታል መገበያያ ገንዘብ) አገልግሎት በኢትዮጵያ እየተስፋፋ መጥቷል ነው የተባለው።

በተጨማሪም ይህ ተግባር ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ውጪ ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር የሚደረግበት እና በተለይም በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ለማሸሽ ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል ነው ያለው ባንኩ።

ይህ እየተስተዋለ ያለው ምናባዊ ንብረትን (ዲጂታል መገበያያ ገንዘብን) ለግብይት ወይም ለክፍያ መጠቀም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕውቅና ያልተሰጠው ድርጊት በመሆኑ ህብረተሰቡ ከእንደዚህ አይነት ሕገ-ወጥ ተግባር እራሱን መጠበቅ ይኖርበታል ብሏል ባንኩ።

በመሆኑም ይህን ፈጽመው በሚገኙ አካላት ላይ ብሔራዊ ባንክ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የገለጸ ሲሆን፥ ህብረተሰቡም ይህንን ህገወጥ ተግባር የሚሠሩ አካላትን ሲመለከት ለብሔራዊ ባንክ እና ለሚመለከታቸው ሕግ አስከባሪ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪውን አቅርቧል።

(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version