የግል ባንኮች ሰባ ከመቶ የውጭ ምንዛሬ ገቢያቸውን ለብሄራዊ ባንክ ገቢ ገቢ እንዲያደረጉ ታዘዘ

የኢትዮጵያ ባንኮች በተለያዩ መንገዶች እጃቸው ከሚገባው የውጭ ምንዛሪ 70 በመቶውን ወደ ማዕከላዊ ባንክ እንዲያስተላልፉ ታዘዋል። ከነሐሴ 2013 ዓ.ም ወዲህ ባሉት ወራት ባንኮች የወጪ ንግድ እና ሐዋላን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ከሚሰበስቡት የውጭ ምንዛሪ 50 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ ሲያስረክቡ ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ ባንኮች ከሸቀጦች እና አገልግሎቶች የወጪ ንግድ እንዲሁም ከሐዋላ ከሚሰበስቡት የውጭ ምንዛሪ 70 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ እንዲያስረክቡ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል። ይኸ ውሳኔ ባንኮች መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ከሚሰጡት አገልግሎት የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ ይጨምራል። ከፍተኛ የባንክ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሙሼ ሰሙ “ኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን የሚያስተዳድር የሚመራ አካል ብሔራዊ ባንክ ነው። ስለዚህ አሁን ከተፈጠረው የኤኮኖሚ ችግር አኳያ የባለቤትነት ሥልጣኑን ተጠቅሞ ከውጪ በኤክስፖርት፣ በአገልግሎት፣ በግል የሚላከውን ገንዘብ፣ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከሚያስገቡት ገንዘብ ውስጥ 70 በመቶው ወደ መንግሥት ካዝና እንዲገባ [ተወስኗል።]

ይኸ ወደ መንግሥት ካዝና የሚገባው ዶላር አሁን የተፈጠረውን የዶላር እጥረት ለመቅረፍ እንዲያገለግል ለማድረግ ነው” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አቶ ሙሼ “ከዚህ በፊት ኤክስፖርተሮች ወይም የዶላር ምንጭ ባለቤት የሆኑ ሰዎች ዶላራቸውን ተደራድረው እንዲሸጡ ሕጋዊ ፈቃድ አልነበራቸውም። በፊት ራሳቸው ብቻ ነበር ማስመጣት የሚፈቀድላቸው። አሁን ግን 20 በመቶው ከሚያገኙት ድርሻቸው ውስጥ ከማንኛውም ነጋዴ ጋር ተደራድረው እንዲሸጡ ተፈቅዶላቸዋል። የድርድሩን ተመን ጣሪያ [የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ] እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል” በማለት አክለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ የፈረሙበት እና ከትላንት በስቲያ ሰኞ ጥር 2 ቀን 2014 ዓ.ም በተጻፈው ደብዳቤ ይፋ የተደረገው መመሪያ ከአራት ወራት ገደማ በፊት የነበረውን አሰራር የሻረ ነው። ባንኮች እጃቸው ከሚገባው የውጭ ምንዛሪ እስከ ነሐሴ 2013 ዓ.ም. ድረስ 30 በመቶውን ብቻ ለብሔራዊ ባንክ ሲያስረክቡ ቆይተዋል። ይሁንና በነሐሴ ወር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መጠኑን ወደ 50 በመቶ ከፍ የሚያደርግ ውሳኔ አሳልፏል። ባለፈው ሰኞ ይፋ የሆነው መመሪያ ባንኮች ለብሔራዊ ባንክ የሚያስረክቡትን የውጭ ምንዛሪ መጠን እንደገና በ20 በመቶ ከፍ በማድረግ 70 በመቶ አድርሶታል። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ “ፍትኃዊ” ለመሆኑ ጥያቄ አላቸው።

ባንኮች “በጣም ለፍተው፣ ደንበኛ ይዘው የሚሰበስቡት የውጭ ምንዛሪ ነው። ብሔራዊ ባንክ ያንን የውጭ ምንዛሪ ´አስፈላጊ ለሆኑ ሥራዎች አውለዋለሁ` ነው የሚለው። መልዕክቱ የግል ባንኮች የውጭ ምንዛሪውን የሚፈቅዱት ለኤኮኖሚው ስትራቴጂክ ላልሆነ [ሥራ] ነው የሚል ነው” የሚሉት አቶ አብዱልመናን ውሳኔው “የግል ባንኮች የውጭ ምንዛሪ የመሰብሰብ ፍላጎታቸውን ያዳክማል። ለብሔራዊ ባንክ የሚያስረክቡት በበዛ ቁጥር የውጪ ምንዛሪ ለመሰብሰብ ምን ፍላጎት ይኖራቸዋል? 70 በመቶ ለብሔራዊ ባንክ እንዲያስረክቡ መወሰኑ ፍትኃዊ አይደለም” ብለዋል።

ከአንድ አመት በላይ የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እና ያስከተለው ብርቱ ቀውስ የወጪ ንግድ እና መዋዕለ-ንዋይን ጨምሮ በአገሪቱ ምጣኔ ሐብት ላይ ብርቱ ተጽዕኖ ያሳደረ ነው።

ከአንድ አመት በላይ የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እና ያስከተለው ቀውስ የወጪ ንግድ እና መዋዕለ-ንዋይን ጨምሮ በአገሪቱ ምጣኔ ሐብት ላይ ብርቱ ተጽዕኖ ያሳደረ ነው። ይኸ ጦርነት የአገሪቱን ኅልውና ጭምር የተፈታተነ መሆኑን የሚያስታውሱት የባንክ ባለሙያው አቶ ሙሼ “አገሪቱ ያላት የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል። የውጭ ንግድ ተዳክሟል። በዕርዳታ እና በድጎማ ወይም በብድር ይመጣ የነበረው ዶላር እየቆመ ነው። ከዚህ ነባራዊ ሁኔታ ተነስተህ ስትመዝነው የፍትኃዊነት ጥያቄ ቦታ ያለው አይመስለኝም” ሲሉ ይናገራሉ።

“መጀመሪያ ለመነገድም፣ ለመሸጥም፣ ለማትረፍም ለመኖርም አገሪቱ ታስፈልጋለች። ከፍትኃዊነት ጽንሰ-ሐሳብ አኳያ ካየኸው ሰዎች እየተገደሉ፣ እየተሰደዱ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተካሔደባቸው፣ ንብረታቸው እየወደመ፣ በጦርነት እየሞቱ ነው። እነዚህ ሰዎችን ለማቋቋም፤ ለእነዚህ ሰዎች ምግብ ለማቅረብ፣ መድሐኒት ለማቅረብ፤ የተዘረፉትን፣ የወደመውን ንብረት እንደገና ለመተካት መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ያስፈልገዋል” የሚሉት የባንክ ባለሙያው የኢትዮጵያ መንግሥት “ያን የውጭ ምንዛሪ ለአጭር ጊዜ ወስዶ ይኸን ማድረጉ ፍትኃዊነቱን አያዛባውም” ሲሉ አስረድተዋል።

ይኸ አሰራር እስከ መቼ ይዘልቃል?

ለአስራ ሶስት ወራት የዘለቀው ጦርነት ወትሮም በገቢ እና ወጪ ንግድ ሚዛን መዛባት ሳቢያ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚፈትነው የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ላይ የፈጠረው ራስ ምታት ብርቱ ነው።  የኢትዮጵያ መንግሥት በጦርነቱ የደረሰውን ምጣኔ-ሐብታዊ ጉዳት ማጥናት መጀመሩን ይፋ አድርጓል። እስከዚያው ድረስ የጉዳቱን መጠን፤ ለማገገም የሚያስፈልገውን ገንዘብ እና የሚወስደውን ጊዜ ማወቅ አይቻልም። እንዲህ ባለው አውድ አሁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢራዊ ያደረገው መመሪያ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ከሆነ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አቶ ሙሼን ያሳስባቸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያስተላለፈው ውሳኔ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ለመሰብሰብ ያላቸው ፍላጎት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ግፋ ሲልም የወጪ ንግዱን ሊጎዳ እንደሚችል ዘርፉን የሚከታተሉ ባለሙያዎች ሥጋት አላቸው።

“አንድ ኩባንያ ሸቀጥ ወደ ውጪ የሚልከው ከዘርፉ ትርፍ ስለሚያገኝ ብቻ አይደለም። ለውጪ ገበያ ከሚያቀርበው ሸቀጥ የሚያገኘው ትርፍ በጣም ትንሽ ነው። በአብዛኛው ዶላሩን ለአስመጪ በመሸጥ የሚያገኘው ትርፍ ነው። ይኸ ኢ-መደበኛ አሰራር ነው። በአንድ በኩል ደግሞ ሕገ-ወጥ ነው” የሚሉት አቶ ሙሼ “የወጪ ንግዱን ለመደገፍ ከመንግሥት በኩል የሚሰጠው ማበረታቻ በቂ ስላልሆነ በተዘዋዋሪ ሰዎች ይኸንን ዕድል እየተጠቀሙ በድፍረት ምርት ወደ ውጪ ይልኩ” እንደነበር አስረድተዋል። እንደ ባንክ ባለሙያው ማብራሪያ ከሆነ  “ብከስርም ያንን ዶላር በተለያየ መንገድ አገር ውስጥ ላለ አስመጪ ሸጬ ከዛ በማገኘው ጥቅም አገሪቱ ያላትን የአቅርቦት ፍላጎት አሟላለሁ የሚል እምነት” ነበር።

አቶ ሙሼ “ባንኮችም ቀላል የማይባል የሰው ኃይል አሰማርተው የተለያየ ማበረታቻ እየሰጡ በቁሳቁስም፣ በንብረትም፣ በሐብትም ታግዘው ይኸንን ሥራ የሚሰሩት ጥቅም ስላለው ነው። ይኸ ጥቅማ ጥቅም ከተቋረጠ ንግድ ሳይሆን ሐይማኖት ነው የሚሆነው። ለጽድቅ የሚሰራ ሥራ ነው የሚሆነው ማለት ነው። ያንን ያደርጋሉ ወይ ነጋዴዎች? ምክንያቱም ላኪውም ነጋዴ ነው። ባንኮቹም ነጋዴዎች ናቸው። በሒደት ሥራውን እየገፉ ወደ ሌላ ዘርፍ ሊሔዱ ይችላሉ ወይንም ደግሞ ሥራው የሚጠበቀውን ያህል ማደግ ሊያዳግተው ይችላል። ማደግ ካዳገተው ደግሞ ይቺ ከተገኘውም ላይ ቀራርመን እንወስዳለን የሚባለውም ነገር ጠቅላላ ሊቆም ይችላል” የሚሉት አቶ ሙሼ ሰሙ “መልሰው  ገደቡ እስከ መቼ ጊዜ ነው?” ሲሉ ይጠይቃሉ። የባንክ ባለሙያው በመመሪያው ባንኮችን “ያሳጣቸውን ጥቅማ ጥቅም በሌላ በምን በምን መንገድ እንዲያካክሱ ያግዛቸዋል? የሚለውን ተመልክቶ እንደ አንድ የቢዝነስ ዘርፍ ያ ዘርፍ እንዳይዳከም ካላደረገው ጠቅላላውን ኤክስፖርቱ ሊሞት ይችላል” በማለት መመሪያው ለረዥም ጊዜ ቢቆይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባለፉት ወራት በተከታታይ ገቢራዊ ካደረጋቸው ክልከላዎች መካከል የባንክ ደንበኞች ከአንድ አካውንት ወደ ሌሎች አካውንቶች በሳምንት ከአምስት ጊዜ በላይ ጥሬ ገንዘብ እንዳያዘዋውሩ የጣለውን ገደብ አንስቷል። “ገደቦቹ የታቀደላቸውን ዓላማ ማሳካታቸውን” የገለጹት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ምክትል አስተዳዳሪ ሰለሞን ደስታ “የሚያስከትሉትን ዓሉታዊ ተጽዕኖዎች ለመፍታት” ክልከላው መነሳቱን እንደተናገሩ አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል። ይኸ ገደብ በብሔራዊ ባንክ መመሪያ ገቢራዊ የሆነው በጥር 2013 ዓ.ም. ነበር።

የኢትዮጵያ ባንኮች ከሸቀጦች እና አገልግሎቶች የወጪ ንግድ እንዲሁም ከሐዋላ ከሚሰበስቡት የውጭ ምንዛሪ 70 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ እንዲያስረክቡ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል።

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ደንበኞች በጥሬም ይሁን በባንክ በኩል የሚያዘዋውሩትን የገንዘብ መጠን የመገደብ ሥልጣን አለወይ? ሲሉ ያጠይቃሉ። “እርግጥ ነው አንድ ማዕከላዊ ባንክ [ሕገ-ወጥ] የገንዘብ ዝውውርን መከላከከል አለበት። ነገር ግን [ሕገ-ወጥ] የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል ሲባል ወይም ከባንክ ውጪ ያለውን ገንዘብ ወደ ባንክ ለማስገባት ቢፈልግ ወይም የጎንዮሽ ግብይትን ለማዳከም ሲል እንደዚህ ጨካኝ የሆነ መመሪያ [ማውጣት]ይችላል ወይ?” እያሉ የሚጠይቁት አቶ አብዱልመናን በቅርቡ የተነሳውን ክልከላ ምሳሌ በማድረግ በደንበኞች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አብራርተዋል።

“አንድ ደንበኛ በሳምንት አምስት ጊዜ ብቻ ገንዘብ ማዘዋወር ትችላለህ ያልከው እንደሆነ ከዚያ በላይ የሚፈልግ የሥራ ዘርፍ ቢኖረው አይችልም ማለት ነው። አንዳንድ የሥራ አይነቶች አስርም ሀያም፤ ከዚያ ባሻገር በባንክ ብቻ ሳይሆን በጥሬ ገንዘብም መጠቀም ሊፈልግ ይችላል። በድንበር አካባቢዎች አብዛኞቹ የገንዘብ ልውውጦች በጥሬ ገንዘብ ነው የሚካሔዱት። ምክንያቱም በአቅራቢያው ወደ ሚገኝ የባንክ ቅርንጫፍ ለመድረስ እንኳ በጣም ሩቅ ነው። ኤሌክትሮኒክ የባንክ አገልግሎትም ያን ያህል የደረጀ አይደለም” በማለት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መገበያያ ገንዘብ ከተቀየረ ወዲህ በርከት ያሉ ክልከላዎች እና ገደቦች በብሔራዊ ባንክ በኩል ሥራ ላይ ውለዋል። አብዛኞቹ ክልከላዎች ከባንክ ውጪ በሰዎች እጅ የሚገኘውን ገንዘብ ወደ ፋይናንስ ተቋማት ለማስገባት እና ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር ያለሙ ናቸው። አቶ ሙሼ እንደሚሉት ግን ቀድሞም ኢ-መደበኛ የንግድ ሥርዓት በሚያይልበት የኢትዮጵያ ገበያ በመመሪያዎች ብቻ ዓላማዎቹን ማሳካት የሚሆን አይደለም።

“ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ገንዘብ በሰው እጅ ላይ ነው ያለው። ያ ገንዘብ ወደ ባንክ ቢመጣ እና ለኢንቨስትመንት ቢያገለግል ወይንም ቢቆጠብ እና ሌላውን ዘርፍ ቢያግዝ ጥሩ ነበር።” የሚሉት የባንክ ባለሙያው “ያንን ማድረግ ግን በአዋጅ በመፈክር አይሆንም” ባይ ናቸው።”ይኸ አገር በአብዛኛው የንግድ ሥርዓቱ ኢ-መደበኛ ነው። የንግድ ሥርዓቱን ሳታስተካክል የገንዘብ ዝውውሩን የምታዛባው ከሆነ የንግድ ሥርዓቱ ይወድቃል። የዕቃ እጥረት ይመጣል፤ ዋጋ ማስወደድ ይመጣል፤ የጥራት ጉድለት ይመጣል፤ ሕገ-ወጥ ይፋፋል። መንግሥትም በሕጋዊ መንገድ ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንዳያገኝ ያደርጋል” የሚሉት አቶ ሙሼ አሰራሩን ማቅለል፤ በነጋዴው ላይ ያልተገባ ጫና የማያድርበትን ሁኔታ ማመቻቸትን ጨምሮ ሥርዓቱን በቅጡ መፈተሽ እንደሚገባ አስረድተዋል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ


Leave a Reply