ETHIO12.COM

የዳውድ ኢብሳ ደብዳቤና የጸጋዬ አራራ ተቃውሞ ተገጣጠመ፤ ጃዋር አዲስ ቀለበት ውስጥ ገብቷል

ጃዋር መሐመድ በማንኛውም ጌ ሊቀጥል በሚችል ወይም ክስ ማቋረጥ ከእስር ከወጣ በሁዋላ አነጋጋሪ ቃለ ምልልስ ሰጥቷል። የኡቡንቱ ጠያቂዎች ከጃዋር ጋር ያካሄዱትን የቤተሰብ ውይይት የሚመስል ቪዲዮ ካሰራጩ በሁዋላ ጃዋር ላይ ቀድሞ ተቃውሞ የሰነዘረው ጻጋዬ አራርሳ ነው። የጸጋዬን ተቃውሞ ተከትሎ ኦነግ አንስቶት የማያውቀውን “የአርማዬን አትጠቀም” ጥያቄ ማስከተሉ ነገሩ ” በመናበብ የሚከናወን ነው” የሚል አስተያየት አስነስቷል። መረራ “ጉዳዩ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም” ሲሉ አጣጥለውታል።

የአቶ ዳውድ ደብዳቤ

እርግጥ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 133 መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎች የሌላውን ድርጅት አርማ  አመሳስሎ ከመጠቀም አርማ ወይም የምርጫ ምልክት በማመሳሰል መጠቀም መታቀብ እንዳለባቸው ያዛል። በዚህ መነሻ የኦነግ ጥያቄ ህጋዊነት ቢኖረውም ዋናው ጉዳይ የአርማ እንዳልሆነ እየተገለጸ ነው።

አቶ ጠጋዬ አራርሳ ተቀማጭነቱ ካናዳ ከሆነና የትህነግን ዓላማ በማራመድ ከሚታወቅ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ” ጃዋር ሴንትራሊስት ነው” በአቶ ጸጋዬ ንግግር በፖለቲካዊ አውድ ትርጉሙ ” መሃል ሰፋሪ” ሲሉ ደረጃ አውጥተውለታል። ጠያቄው ” ለምን” ሲል ምክንያት ፈልጎ እድሉን ለአቶ ጸጋዬ ሲሰጥ ” ጃዋር ኦፌኮን ሲቀላቀል ነው መሃል ሰፋሪ መሆኑንን ያረጋገጠው። የአሁኑ የዚያ ተከታይ ነው። አዲስ ነገር አይደለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

አቶ ጸጋዬ ፕሮፌሰር መረራ የሚመሩትን ኦፌኮን ኦሮሞ ኦሮሞ የማይሸት፣ የአማራ ጥላ ያጠላበት፣ ኢትዮጵያዊነት የሚታይበት፣ ለኦሮሞ ትግል የማይመጥን እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲያስታውቁ የኖሩ ሰው መሆናቸው ይታወሳል። እንደ አቶ ጸጋዬና ደጋፊዎቻቸው እምነት የመረራ ፓርቲ ” ሸዋ ተኮር” ወይም እሳቸው እንደሚያራምዱት አይነት “አክራሪ” አይደለም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኦፌኮ ውስጥ “አማርኛ አትናገሩ፣ አማራ አትግቡ፣ ከአማራ ጋር አትነገዱ” የሚሉ ጉዳዮች መሰማታቸው ብዥታ የፈጠረ ቢሆንም ኦፌኮና የአቶ ቡላቻ ፓርቲ በመካከለኛ አቋም የሚታወቁ፣ የኦሮሚያን ጉዳይ በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ የሚመለከቱ ናቸው። አቶ ጸጋዬ እንዳሉት ጃዋር ኦፌኮን ሲቀላቀል ጉዳዩ አብቅቷል።

እነ አቶ ጸጋዬና እነ ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል በገሃድ ከትህነግ ጋር አብረው የሚሰሩና ” ሸኔ” ከሚባለው ሃይል ጋር ” የኦሮሞ ነጻ አውጪ ጦር” ብለው በመጥራት አስፈላጊውን ድጋፍ የማሰባሰብና የትግሉን ስትራቴጂ የመምራት ስራ እንደሚሰሩ በተደጋጋሚ ይፋ አድርገዋል። አሁንም እያደረጉ ነው። ይኑር ይፍረስ በውል በማይታወቀው ትህነግ በሚመራው ጥምረት ውስጥም ተሳታፊ ናቸው። ይህ የማይታወቁ ድርጅቶችን አካቶ ተመሰረተ የተባለው ጥምረት በጠብ መንጃ ትግል መንግስትን ለመጣል የሚሰራና ትህነግ አዲስ አበባ ሊገባ ነው በተባለበት ወቅት የተቋቋመ ነው።

ጃዋር ” ብዙ ዓመት ሳወራ ኖሪአያለሁ፣ አሁን ደግሞ ላድምጥ ብዬ ነው” ሲል በዝምታ መቆየቱን ባስታወቀበት ቪዲዮ ደጋግሞ ያነሳው ” ሰላም” የሚለውን ቃልና ” ጠመንጃ ያነሱ” ያላቸውን በገሃድ እንደማይደግፍ ማስታወቁ ነው ለእነ ጸጋዬ ቡድን የተቃውሞ ምላሽ መነሻ የሆነው። በዚህ መነሻ ነው አፍቃሪ ትህነግ የሆነው ሚድያ አቶ ጸጋዬን ጋብዞ ጃዋርን ያስተቸው።

ይህን ተከትሎ አቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመሩት ክፋዩ ኦነግ ” አርማዬን አክብሩ” ሲል ለኦፌኮ ደብዳቤ የጻፈው። ለትግል ሲወጣ አንድ የነበረውና አራት ቦታ ተከፍሎ ወደ አገር ቤት ከተመለሰው ኦነግ አቶ ዳውድ የሚመሩት ኦነግ ሸኔ የሚል ቅጽል የያዘ እንደነበር ይታወሳል። በድርጅቱ ባለቤትነት ስምምነት ባለመኖሩ አባ ቢያ፣ በቅርቡ ያለፉት ገላሳ ዲልቦ፣ ከማል ገልቹና አቶ ዳውድ ሁሉም ለመለያነት ያገለግል ዘንዳ ተቀጽላ በማድረግ ሲጠሩ ነበር የአቶ ዳውድ “ኦነግ ሸኔ” ወይም አምስተኛው ኦነግ የተባለው ስም የመረጡት።

ለማስታወስ ያህል በለውጡ ማግስት ዳውድ ኢብሣ ፣ አባ ነጋ፣ ገላሳ ዲልቦና ጄኔራል ከማል ገልቹ ሁሉም ኦነግ ላይ ቅጥያ ጨምረው ወደ አዲስ አበባ ገቡ።አራት መልክ ይዞ ወደ አገር ቤት ሲገባ ሕዝብ ወዲያውኑ ያነሳው ጥያቄ “ለምን አንድ አትሆኑም? አንድ ሁኑና ኑ” የሚል ነበር። እነዚህ አራት ክንፎች እንኳን አንድ ሊሆኑ ይባስ ብሎ አቶ ዳውድ ኢብሣ የሚመሩት ኦነግ ሸኔ ውስጥ ሌላ የሚታወቅና የማይታወቅ ስንጥቅ ተፈጠረ። መሰነጠቁን ተከትሎ ዳውድ የሚመሩት ኦነግ ሸኔ በውስጡ በተነሳ የአቋም ልዩነትና ውስጥ ለውስጥ በሚከናወን የተለያዩ ጉዳዮች ሳቢያ ለሁለት የተከፈለበት ምክንያት ይፋ ሆነ። አንዱና ዋና ጉዳይ ዳውድ በሁለት መለያ እንደሚጫወቱ መገለጹ ነው። ምንም እንኳን ዳውድ ጉዳዩን ቢያጣጥሉትም ወቃሾቹ በተደጋጋሚ በስብሰባቸው ይህን ጉዳይ በማንሳት እንዲስተካከል መጠየቃቸውን ቃለ ጉባኤ አጣቅሰው ገልጸዋል።

“ወደ አገር ቤት የገባነው በሰላማዊ መነገድ ለመታገል ነው። ከትህነግ ጋር በድብቅ የምንሰራበት ሞራል የለንም። ትህነግ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የፈጸመው ግፍ በቀላሉ የሚረሳ አይደለም። ከትህነግ ጋር መስማማት ኦሮሞንና የኢትዮጵያን ሕዝብ መካድ ነው” ሲሉ ዳውድን የወቀሱት የኦነግ ስራ አስፈጻሚዎች በአቶ አራርሳ መሪነት ሌላ ኦነግ መሰረቱ። ዳውድ ኢብሳ በበኩላቸው ” ከብልጽግና ጋር ያበሩ” ሲሉ በዲሲፒሊን ቅጣት እንደጣሉ አስታወቁ።

በዚህ መካከል ነው እንግዲህ አቶ ጃዋር መሳሪያ ያነገቡትን በሙሉ እንደማይደግፍ አስታውቆ ዳግም ወደ ሚዲያ ብቅ ያለው። አስከትሎም የምስጋና ጉዞ አውሮፓና አሜሪካ ለማድረግ የተነሳው። የጀርመኑ ጉዞ መጠናቀቁን ተከትሎ አቶ ዳውድ ለኦፌኮ በሳፉት ደብዳቤ ደብዳቤ በርዕስ ስር በሕጋዊ መልኩ በምርጫ ቦርድ የተመዘገበውን የኦነግን ባንዲራ የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር ጃዋር መሐመድ በሕገወጥ መልኩ መጠቀሙን ስለማስቆም” ይላል። አድራሻውም ለፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ነው።

ደብዳቤው በማሳረጊያው ከረር ያለ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። አክሎም “ደብዳቤው ከደረሳችሁ ቀን ጀምሮ አቶ ጃዋር የኦነግን ባንዲራ ከመጠቀም እንደምታስቆሙት፣ ጥያቄያችንን በተግባር ፈጽማችሁ እንደምታስታውቁን እናምናለን” ተስፋም እናደርጋለን” ይላል። ይህንኑ ጉዳይ እንዲያብራሩ የተጠየቁት መረራ ” አልተወያየንበትም። እዚህ ግባ የሚባል ጉዳይ አይደለም” ሲሉ ለቢቢሲ አስታውቀዋል።

“ኦነግ ሸኔ” የሚባለውን፣ ስሙን “የኦሮሞ ጦር” በሚል እየጠሩ ከውጭ በገንዘብም ሆነ በማስተባበርና በፕሮፓጋንዳ የሚረዱት እነ ጸጋዬ አራርሳ ከጃዋር ጋር ሆድና ጀርባ መሆናቸውን ተከትሎ ይህ ደብዳቤ ባልተለመደ መልኩ መጻፉ ከአራማው የባለቤትነት ጥያቄ በላይ ቀልብ የሳበውም በዚህ ምክንያት ነው። ምክንያቱም ዳውድ ከዚህ ሃይል ጋር እንዳሉበት አብረዋቸው በነበሩ የስራ አስፈጻሚዎች በተደጋጋሚ ከመገለጹ ጋር ተያይዞ የሚነሱ አስተያየቶች ጃዋር “መሳሪያ ያነገቡ ሃይሎችን” አልደግፍም ማለቱ ቅሬታ ማስነሳቱም የዚሁ ስሌት ውጤት እንደሆነ አስተያት ሰጪዎቹ ያክላሉ።

የጃዋር የምስጋና ገለቶማ ጉዞ ገና ከመጀመሩ ይህ ተቃውሞ መሰማቱ በጉዞውና በሚያካሂዳቸው ስብሰባዎቹን ላይ ጫና ይኑረው አይኑረው ለጊዜው አልታወቀም። ልዩነቱም ወዴት አቅጣጫ እንደሚወስዳቸው አልለየም።

ጃዋርና መረራ ዳውድ ኢብሳ የሚመሩትን ኦነግ በገሃድ ማውገዛቸው ይታወሳል። ፕሮፌሰር መረራ በጥናት ጽሁፋቸው ኦነግን በጠንካራ ማጣቀሻ አውግዘው ” ኦሮሞ ግንድ ነው ከማን ነው የሚገነጠለው? ቅርንጫፍ እንጂ ግንድ አይገነጠልም” በሚል የኦነግን አቋም ማራከሳቸው ይታወሳል። አቶ ጃዋርም ወደ ፖለቲካው ሲመጡ ኦነግን ” አስመራ የተያዘ እስረኛ” ሲሉ ያለ አንዳች ፋይዳ እድሜ የፈጀ በማለት በተደጋጋሚ ማውገዙ ይታወሳል።

አቶ ዳውድ ከደሙ ንጹህ እንደሆኑና መንግስት ጫና እያደረገባቸው ስራቸውን ለመስራት መቸገራቸውን በተደጋጋሚ በማስታወቅ በቀር አንድም ቀን በሚቀርቡባቸው ክሶች ዙሪያ መረጃ አለመቅረቡን ሲያስታውቁ እንደነበር አይዘነጋም።

አቶ ጃዋር ይህ እስከተጻፈ ድረስ ጉዳዩን አስመልክቶ ያለው ነገር የለም። ኦፌኮ በጉዳይ ዙሪያ መክሮ ምላሽ እንደሚሰጥ ለቢቢሲ አስታውቋል።

Subscrib and get info … news

Exit mobile version