Site icon ETHIO12.COM

ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት የሰረቁ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት የሰረቁ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ለአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር የተዘረጉ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የስርቆት ወንጀል ሲፈፅሙ የተገኙ ስድስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገልጿል፡፡

በአገልግሎቱ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ማስተባበሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢልቱማ ቂጣታ እንደገለፁት፡- ስርቆቱ የተፈፀመው ከሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም እስከ 16 ቀን 2014 ዓ.ም ባሉት ቀናት ነው፡፡

ድርጊቱ ከተፈፀመባቸው አካበባቢዎች መካከል በተለምዶ መሿለኪያ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፊት ለፊት እና ባምቢስ ወደ ኡራኤል ባለው መንገድ በተዘረጉ የመካከለኛ ቮልቴጅ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኬብሎች ላይ መሆኑን ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

የተዘረፈው የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት 1 ሺህ 765 ሜትር የሚሽፍን የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኬብል ሲሆን፤ 3 ሚሊዮን 829 ሺህ 180 ብር የሚገመት ኪሳራ በተቋሙ ላይ መድረሱንም ገልፀዋል፡፡

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት የአዲስ አበባ ፖሊስ ከፊደራል ፖሊስ እና በአከባቢው በነበሩ የድርጅት ጠባቂዎች በመተባበር መሆኑን የገለፁት አቶ ቢሊሱማ፤ አሁን በካዛንቺስ 6ተኛ ፖሊስ ጣቢያ በምርመራ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ሌሎች በዘረፋው የተሳተፉ ግብረ አበሮችንም ለመያዝ ከፍተኛ ክትትል እያደረገ መሆኑን ተጠቁሟል።

በባቡር መሰረተ-ልማት ላይ እየደረሰ ያለው ዘረፋ በከፍተኛ ደረጃ እየተባባሰ የመጣ ሲሆን፤ በ2013 እና በ2014 ዓ.ም ብቻ ግምቱ 29 ሚሊዮን 923 ሺህ 255 ብር የሚያወጣ 18 ሺህ 167 ሜትር ኬብል መዘረፉን አቶ ቢሊሱማ ተናግረዋል፡፡

ለኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ስርቆት መባባስ ዋናው ምክንያት እጅ ከፍንጅ የሚያዙ ዘራፊዎች ላይ በተቀመጠው ህግና ደንብ መሰርት ተመጣጣኝና አስተማሪ የእርምት እርምጃ እየተወሰደ ባለሆኑ መሆኑንን ጨምረው ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ እና ፌደራል ፖሊስ ዘራፊዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው፤ የጀመሩትን የክትትልና ቁጥጥር ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል፡፡

እየተዘረፈ ያለው የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ከፍተኛ የሃገርና የህዝብ ሃብት በመሆኑ ህብረተሰቡ እንደራሱ ንብረት አድርጎ ሊጠብቀው እንደሚገባና አጠራጣሪ ነገር ሲመለከት በአካባቢው ለሚገኘ የፀጥታ አካል ሊያሳውቅ ይገባል ብለዋል፡፡

እንዲሁም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ቢሮም በመሰረተ ልማቱ ላይ የሚደረሰውን ጉዳትና ስርቆት እንዲቀንስ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ እንዳለበትና የጥገና ሥራው በቶሎ ለማጠናቀቅ እንዲቻል ተገቢውን ክፍያ በወቅቱ መፈፀም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

(ኢ.ፕ.ድ)

Exit mobile version