ETHIO12.COM

ሪፖርተር “አውድ በማሳት ደቡብ ሱዳን ወረራ ፈጸመች” ሲል ያሰራጨው ዜና እየተመረመረ መሆኑ ተሰማ

ሪፖርተር ጋዜጣ “አነጋገርኳቸው” ሲል ስማቸውን የጠቀሳቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ “ሪፖርተር የዜናውን አውድ ስቷል” ሲሉ ዜናው እንዲስተካከል ጠየቁ። የዜናው እንደምታ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እጅግ በጥንቃቄ የምትይዘውን የደቡብ ሱዳንን ወዳጅነት የሚያጠላሽ በመሆኑ በጥብቅ እንደሚመረመር ተመለከተ። ለፅንፈኛ ሀይሎች አጀንዳ ጆሮ መስጠት እንደማይገባ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት አመልክቷል።

በግብጽ አቀናባሪነት ሱዳ በሚገኙ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር / ትህነግ ምልምሎችና ራሷ ሱዳን በጋር ኢትዮጵያ ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት በመቃወምና መተላለፊያ በመዝጋት ደቡብ ሱዳንን የኢትዮጵያ የችግር ወቅት ወዳጅ መሆኗ ይታወሳል። “አውዱን ስቷል” የተባለው ሪፖርተር ዜና እንዲስተካከልና ጉዳዩ የተለመደ የአርብቶ አደሮች የግጦሽ መሬት ግጭትና ዝርፊያ እንደሆነ ተመልክቷል።

“የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የወርቅ ማውጫ አካባቢን መቆጣጠራቸው ተሰማ” ሲል የሪፖርተሩ ዘጋቢ አማኑኤል ይልቃል “ታጣቂዎቹ የወርቅ ማውጫውን ከተቆጣጠሩ አንድ ወር ገደማ እንደሆናቸውና ወርቅ በማውጣት ሥራ እንደተሰማሩ፣ የክልሉ የሰላምና አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል፡፡ በዚህም ምክንያት ክልሉ በባህላዊ መንገድ ሲያከናውን የነበረውን ወርቅ የማውጣት ሥራ እንዳቋረጠም የቢሮው ዋና ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ለሪፖርተር ተናግረዋል” ሲል ጽፏል።

በተመሳሳይ አዲስ ዘመን የጠቀሳቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ሪፖርተር በሰኔ 19/2014 እትሙ የደቡብ ሱዳን የታጠቁ ሀይሎች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ወረራ ፈፅሟል ብሎ ያወጣው ዘገባ ስህተት እንደሆና የደቡብ ሱዳን የታጠቁ ሀይሎች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የፈፀሙት ወረራ እንደሌለ አለመኖሩን በመጥቀስ ሪፖርተርን ከሰዋል። ዜናው አውዱን የሳተና የተሳሳተ በመሆኑ ማስተካከያ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። ይህ እስከታተመ ድረስ ሪፖርተር ማስተካከያ ወይም ለክሱ መልስ አልሰጠም።

የሪፖርተር የፊት ዜና ምስልና ርዕስ

አቶ አንድነት አሸናፊ በመግለጫቸው ክልሉ እንደወትሮዉ በሁሉም አቅጣጫ ሰላም እንደሆነ ጠቅሰዉ፣በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምዕራብ ኦሞ ዞን ሱርማ ወረዳ ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያዋስን አካባቢ በመሆኑና በሁለቱም አካባቢዎች ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎች አርብቶ አደር ስለሆኑ በግጦሽ ሳርና በውሃ ምክንያት አልፎ አልፎ ግጭትና ዝርፍያ ይፈፀማሉ ብለዋል።

አሁንም በአካባቢው የተስተዋለው በአርብቶ አደሮች የአኗኗር ባህሪይ የተከሰተ ግጭትና አለመግባባት መሆኑን ገልጸዉ ፣የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እንደ ክልል ከመደራጀት በፊትም የነበረ እንደሆነ አቶ አንድነት አብራርተዋል። አክለውም በርወረራ ደረጃ የሚገልጽ እንዳልሆነ አመልክተዋል።

“አሁን ያለውን የሀገርቱን ወቅታዊ ሁኔታ በማሳበብ የሪፖርተር ጋዜጣ በሰኔ 19/2014 እትም ያወጣው ዘገባ ከነባራዊ ሁኔታና ከአውድ ያፈነገጠ ነው” ሲሉ ሃላፊው ተናግረዋል። “የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በመንተራስ” ሲሉ ሪፖርተር ሆን ብሎ ዜና ማዛባቱን ያመለከቱት ሃላፊው ዜናው ሆን ተብሎ የተዛባበትን ሚስጢር አላብራሩም።

የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው ባለስልጣን ” ከደቡብ ሱዳን ጋር ባለን ወሳኝ ህብረት ላይ ያነጣጠረ ዜና በመሆኑ ከህግና ከአገር ጥቅም አንጻር ዜናውና የዜናው እንደምታ ይመረመራል” ሲሉ ተናግረዋል። ዝርዝር መረጃ ከመስጠትም ተቆጥበዋል።

በድንበር አካባቢ የሚፈጠረውን ግጭትና አለመግባባትን የፌዴራልና የክልል መንግስት ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር በውይይት ለመፍታት እንደ ከዚህ በፊቱ ሰፊ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ያስታወቁት አቶ አንድነት፣ የህዝቡን ደህንነትና ሰላም ማስጠበቅ የክልሉ መንግስት ቀዳሚ ተግባር ስለሆነ የክልሉን ህዝብና የፀጥታ ሀይሉን በማስተባበር በትኩረት እየሰራ መሆኑን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ከተናገሩት ለማወቅ ተችሏል።

በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች በአንፃራዊነት የተረጋጋ ሰላም እንዳለ የገለፁት አቶ አንድነት ፣ሰላም ለሁሉም ስለሚተርፍ ሁሉም የክልሉ ህዝብ ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአከባቢውን ሰላም እንዲያስጠብቅና ለፅንፈኛ ሀይሎች አጀንዳ ጆሮ መስጠት እንደሌለበት ማሳሰባቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አመልክቷል።

ሪፖርተር የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ወረራ ማካሄዳቸውን ጠቅሶ ያሰራጨውን ዜና የተለያዩ የዩቲዩብ ዜና አቅራቢዎች እንዳለ በመውሰድ አሰራጭተውታል። አንዳንዶች ሰሞኑንን በወለጋ ከተፈጸመው ጭፍጨፋ ጋር በማያያዝ መንግስትን ዘልፈዋል። አገር ሲወረር ዝምታን የሚመርጥ ልፍስፍስ መንግስት እንደሆነ በመግለጽ ህዝብ እንዲቆጣ እንደ ተጨማሪ ግብአት የተጠቀሙበት አሉ።

ሪፖርተር በስፋት የዘገበው ዜና ” አውዱ የሳተ ነው” ሲሉ በአዲስ ዘመን ማስተባበያ የሰጡትን ሃላፊ ገልጾ በመሆኑ ምን አልባትም የሃላፊውን የድምጽ ማስረጃ ማቅረብ ግድ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል። ዜናውን እየመረመረ ያለው ክፍል ሪፖርተር የጠቃሳቸውን ሃላፊም እንደሚያጠናቸው ለማወቅ ተችሏል።

በኢትዮጵያ በተለይም የኦን ላይን ሚዲያዎች ዜና ማረም፣ ይቅርታ መጠየቅና ማስተካከያ ማድረግ አልለመዱም። ከዚህ ቀደም ዋዜማ አባይ መሸጡንና ኢትዮጵያ ግብጽ ላቀረበችው ሰነድ እውቅና ሰጥታ መፈረሟን ቢጽፍም ማስተባበያ ሳይዘጥ ማለፉ ይጠቀሳል። “አክቲቪስ ነን” የሚሉትና የዩቲዩብ ገበያተኞችም እጅግ በርካታ ስህተት ቢሰሩም ይቅርታ ሲጠየቁ ተሰምቶ አያውቅም።

Exit mobile version