Site icon ETHIO12.COM

በአማራ ሕዝብ ላይ ተባብሶ የቀጠለውን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ አስመልክቶ ከአብን የተሰጠ መግለጫ

የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሞ እና አስፈጽሞ አንገትን ቀና አድርጎ መሄድ አይቻልም!

የተቀናጀ ፣ ተከታታይ እና ሥልታዊ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመፈጸም እና በማስፈጸም የአማራን ሕዝብ ማሸማቀቅ ፣ አንገቱን ማስደፋት እና ፖለቲካዊ ድል ማግኝት አይቻልም!

የዘር ፍጅት ፖለቲካ አራማጁ እና ሽብርተኛው የኦነግ ሸኔ ሰራዊት ፣ ከይፋዊ እና ህቡዕ አጋሮቹ ጋር በመተባበር በአማራ ሕዝብ ላይ እየፈጸሙ ያሉትን የዘር ማጥፋት ወንጀል አጠናክረው ቀጥለዋል። በብዙ ምዕራፍ በተከፈለው የተቀናጀ፣ ተከታታይ እና ሥልታዊ የዘር ማጥፋት ወንጀል ዕቅድ ቀጣይ ክፍል በሆነው ጭፍጨፋ ትናንት በቀን 27/10/2014 ዓ.ም በቄሌም ወለጋ ዞን በሃዋ ገላን ወረዳ መንደር 20 እና 21 ተብለው በሚታወቁ ልዩ ቦታዎች እስካሁን በታወቀ መረጃ ከ400 በላይ ህጻናት ፣ ሴቶች እና ሌሎች ሲቪሊያን የአማራ ተወላጆች ተጨፍጭፈው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል።

እራሱን “የኦሮሞ ነጻ አውጭ ሰራዊት” እያለ የሚጠራው እና የዘር ፍጅት ፖለቲካ አራማጁ እና ሽብርተኛው ኦነግ-ሸኔ ሰኔ 25 ቀን 2014 ዓ.ም /እ.ኤ.አ ሐምሌ 2 ቀን 2022 ዓ.ም/ ባወጣው መግለጫ ጭፍጨፋውን እንደሚፈጽም እና ለጭፍጨፋው ኅላፊነት እንደሚወስድ አስቀድሞ አረጋግጧል። የሽብር ቡድኑ ልሳን የሆነው እና መቀመጫውን በአሜሪካን ሀገር ያደረገው ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ /OMN/ የተባለ የዘር-ፍጅት አራማጅ ሚዲያ ድርጅት “የአማራ ሃይሎች በሁሉም አቅጣጫ ወደ ኦሮሚያ እየገቡ ነው ተባለ” ፣ “አሁን በኦሮሚያ ላይ የታወጀው ጦርነት ዋነኛ ባለቤት የአማራ መንግስት ነው ተባለ” ፣ “በኦሮሚያ ላይ የታወጀው ጦርነት በዩጎዝላቪያ ሰርቦች በኮሰቦ ላይ ከከፈቱት ጦርነት ጋር እንደሚመሳል ተናገሩ” የሚሉ እና የመሳሰሉ ሰፊ ፣ ተከታታይ እና የተቀናጀ ቅስቀሳ በመስራት እየተፈጸመ ላለው እና ለቀጠለው የዘር ጭፍጨፋ ወንጀል ሽፋን ሲሰጥ ቆይቷል። የሚዲያው መስራች እና ባለቤት የሆኑት ግለሰብ ደግሞ “ከደሙ ንፁህ ነኝ” እና “የለሁበትም” ለማለት እና ኅላፊነት የሚሰማው ወገን ‘ሆኖ – ሳይሆን – መስሎ – ለመቅረብ’ ባገኙት መድረክ ሁሉ መሃላ እየፈጸሙ ይገኛሉ።

በአማራ ሕዝብ ላይ የተደገሰው ሰፊ ፣ ተከታታይ እና ሥልታዊ የዘር ማጥፋት ወንጀል በአጋጣሚ እና በደም ፍላት የተፈጸመ እና እየተፈጸመ ያለ ድንገተኛ ክስተት አይደለም። እቅዱ በርካታ አስርት ዓመታት ያስቆጠረ እድሜ ያለው እና በተለያየ ቦታ እና ጊዜ ሰርቶ-ማሳያዎች ሲከወኑበት የቆየ “ግዙፍ ፕሮጀክት” ነው። ከምስረታው ጀምሮ የዘር ፍጅት ወንጀልን የፖለቲካ ግብ ማስፈጸሚያ መሳሪያ አድርጎ የቀረጸው የዘር ፍጅት ፖለቲካ አራማጁ እና አሸባሪው ትሕነግ-ወያኔ የዕቅዱ ደራሲ እና ጀማሪ ሲሆን ፣ ዕቅዱን በተሟላ ሁኔታ ለማስፈጸም የሚያስችል የሕ ማዕቀፍ ፣ የአስተዳደር መዋቅር እና አስቻይ-ትርክት በሀገራችን ላይ ተክሏል። ዕቅዱን እንደራሳቸው አድርገው የተቀበሉት ፣ የዕቅዱ ፈጻሚዎች እና አስፈፃሚዎች የሆኑት የትሕነግ-ወያኔ ይፋዊ የ”ትግል” አጋር ኦነግ-ሸኔ ፣ በህቡዕ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ እና በ”ሰላማዊ” ተቃውሞ ሽፋን ስልታዊ ድጋፍ የሚሰጧቸው “ጉምቱ ፖለቲከኞች” እና ተባባሪዎቻቸው የ”ግዙፉ ፕሮጀክት” ባለቤት ፣ ቀጥተኛ እና ንቁ ተሳታፊዎች ናቸው።

የፌዴራል እና የክልል መንግስታት በአማራ ሕዝብ ላይ ሲፈጸም የቆየውን እና እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በመካድ ፣ በመሸፋፈን ፣ በማቃለል እና ወንጀሉን በስሙ ባለመጥራት ፤ በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ለማስቆም ፣ ለመከላከል እና ቀጣይነቱን ለመግታት የሚያስችል የፖሊሲ ፣ የስትራቴጅ እና ተግባራዊ እርምጃዎች ለመውሰድ ፈቃደኛ ባለመሆን እና ዳተኛ በመሆን ፤ በዘር ማጥፋት ወንጀሉ በይፋ እና በህቡዕ ተሳትፎ እያደጉ ያሉ ወንጀለኞች በሕግ አግባብ እንዳይጠየቁ በማድረግ ፤ ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ሲኦል ይዘው ለመውረድ እና ኢትዮጵያን ለመበተን ምለው የተገዘቱ ቡድኖች በአማራ ሕዝብ ላይ እየፈጸሙት ላለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተባባሪ ሁነዋል።

በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ላለው ለዘር ጭፍጨፋ ወንጀል የምዕራባውያን “ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች” እና ተቋማት ጀሮ ዳባስ ልበስ ብለዋል። አንዳንድ የምዕራባውያን ባለስልጣናት ደግሞ የዘር ጭፍጨፋ ወንጀሉን በኢትዮጵያ እንዲጸና እና እንዲተከል ለሚፈልጉት የፖለቲካ ሥርአት ምስረታ አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥር መልካም አጋጣሚ አድርገው በመቁጠር ፣ የዘር ጭፍጨፋ ወንጀሉን በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እና ነፍጥ ባነገቡ አሸባሪዎች መካከል በሚደረገው ግብግብ ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ ውጤት ተደርጎ እንዲቆጠር እና መደራደሪያ እንዲሆን ለማድረግ እየሰሩ ይገኛሉ። በውጤቱም የዘር ጭፍጨፋውን እየፈጸሙ ያሉት ሽብርተኛ ቡድኖች በጦር ግንባር ማሳካት ያልቻሉትን ጠንካራ የመደራደር አቅም ፣ የዘር ጭፍጨፋውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ እና የመደራደር አቅማቸውን የማሳደጊያ መሳሪያ አድርገው እንዲጠቀሙበት እየሰሩበት ይገኛሉ።
በየትኛውም ዓለም-አቀፍ ሕግ የዘር ጭፍጨፋ ወንጀል በሁለት ተፋላሚ ወገኖች ግጭት ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ ውጤት ተደርጎ የማይቆጠር እና ይቅርታ የማያሰጥ ወንጀል ቢሆንም ፣ በአንዳንድ ምዕራባውያን መንግስታት እና ባለስልጣናት ወንጀሉን በስሙ ላለመጥራት ብቻ ሳይሆን ድጋፍ የሚያደርጉላቸው የሽብር ቡድኖች መደራደሪያ እንዲያደርጉት እየሄዱበት ያለው እርቀት በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ወንጀል በቀላሉ መቋጫ እንዳያገኝ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል። የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሆኑት እንደ ግብጽ ያሉ ሀገራት ደግሞ ሁኔታው ሰርግ እና ምላሽ ሁኖላቸው ከሽብር ቡድኖቹ ጋር እጅ እና ጓንት ሁነው ጭፍጨፋው እንዲጧጧፍ ሌት ተቀን እየሰሩበት ይገኛሉ።

በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ወንጀል እና የተደቀነው ግልጽ እና ተጨባጭ የኅልውና አደጋ እጅግ በጣም ስር የሰደደ ፣ ውስብስብ እና በርካታ የውስጥ እና የውጭ ተዋናዮች የሚሳተፉበት ብቻ ሳይሆን ፣ የዘር ማጥፋት ወንጀሉ የፖለቲካ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ መሳሪያ ሆኖ የተቀረጸ በመሆኑ ትግላችንን መራራ ፣ ረጅም እና ከፍተኛ መስዋእትነት የሚጠይቅ አድርጎታል። ከፍተኛ የሆነ ሃብት እና የሰው ኅይል ተመድቦ በእቅድ የሚመራው “ግዙፍ ፕሮጀክት” ማስፈጸሚያ የሆነው የዘር ጭፍጨፋ ወንጀል የመጨረሻው ግብ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የመበተን ፣ መላ ኢትዮጵያውያንን በቋንቋ እና በሃይማኖት ከፋፍሎ በማያቋርጥ የግጭት አዙሪት መክተት ፣ የአማራን ሕዝብ እንደ ፖለቲካ ማኅበረሰብ እንዳይቀጥል እና እንደ ፍልስጤም ሕዝብ ሀገር አልባ፣ በገዛ ሀገሩ ስደተኛ እና ተቅበዝባዥ ሕዝብ የማድረግ ግብ ያለው ነው። በመሆኑም እያንዳንዱ እርምጃችን እና እንቅስቃሴያችን ትዕግስት የተሞላበት ፣ ብዙ ማስተዋል የሚጠይቅ ፣ አውቀንም ሆነ ሳናውቅ በጠላት የኅይል አሰላለፍ ውስጥ እንዳንገባ እና በጠላቶቻችን ዕቅድ ውስጥ እንዳንወቅድ ብርቱ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ሁኗል።

ጠላቶቻችን ማወቅ ያለባቸው የተቀናጀ ፣ ተከታታይ እና ሥልታዊ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመፈጸም እና በማስፈጸም የአማራን ሕዝብ ማሸማቀቅ ፣ አንገቱን ማስደፋት እና በአማራ ሕዝብ ላይ ፖለቲካዊ ድል ማግኝት እንደማይቻል ነው። ይህ በተደጋጋሚ ተሞክሮ የከሸፈ ነውረኛ እና አሳፋሪ የፈሪዎች ዱላ ነው፡፡ የአማራ ሕዝብም ሆነ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለሽህ ዓመታት የዘለቀውን ኅልውናቸውን አረጋግጠው የኖሩት ፣ በርካታ መሰል እና ተደጋጋሚ አስከፊ የታሪክ እጥፋቶችን በድል ተሻግረው ነው። ዛሬም የአማራ ሕዝብ የተደቀነበትን ግልጽ እና ተጨባጭ የኅልውና አደጋ ፣ የሀገራችን ሕዝቦች የተደገሰላቸውን የእርስ በእርስ እልቂትና የቀውስ አዙሪት እና ሀገራችን ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን የመበተን ስጋት በድል አድራጊነት እንደምንሻገረው ፓርቲያችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፣ የአማራ ሕዝብ እና መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ምንም ጥርጥር የለንም። ነገር ግን የአማራ ሕዝብ የተደቀነበትን ግልጽ እና ተጨባጭ የኅልውና አደጋ ፣ የሀገራችን ሕዝቦች የተደገሰላቸውን የእርስ በእርስ እልቂትና የቀውስ አዙሪት እና ሀገራችን ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን የመበተን ስጋት መከላከል የሚቻለው እና በድል አድራጊነት መሻገር የምንችለው የአማራ ሕዝብ ፣ መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እና መንግስት ጠላቶቻችን ካላቸው ዝግጅት በላቀ ደረጃ መዘጋጀት ከቻልን እና በብዙ እርምጃ ቀድመን ከተገኘን ብቻ ነው። ስለሆነም ፦

  1. መላው የአማራ ሕዝብ ፣ የአማራ ወጣቶች እና አደረጃጀቶች በሙሉ የተቃጣብንን ግልጽ እና ተጨባጭ የኅልውና አደጋን መመከት የሚቻለው ከግብታዊነት እና ስሜታዊነት በራቀ መልኩ በፍጹም ጥንቃቄ እና ትዕግስት በምንወስዳቸው እርምጃዎች እና ውሳኔዎች ብቻ መሆኑን በመረዳት ፣ ለአመጽ ፣ ብጥብጥ እና የበቀል እርምጃ ጥሪ ከሚያደርጉ አካላት እንድትጠበቁ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፤
  2. ለመላው የኦሮሞ ሕዝብ ፣ ለኦሮሞ ወጣቶች እና ሀገር ወዳድ የኦሮሞ ፖለቲከኞች በሙሉ በታላቁ የኦሮሞ ህዝብ ስም የሚነግደው ፣ የዘር ፍጅት ፖለቲካ አራማጁ እና አሸባሪው የኦነግ-ሸኔ ቡድን የሚፈጽመው የዘር ጭፍጨፋ በንጹሃን አማሮች ላይ እያደረሰ ካለው ጉዳት ባልተናነሰ ፣ በኦሮሞ ሕዝብ ዘላቂ ጥቅም ላይ የደቀነውን አደጋ በመረዳት ቡድኑን እንድታወግዙ እና እየተጠቃ ካለው የአማራ ሕዝብ ጎን እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፤
  3. በተደጋጋሚ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈጸመባቸው የሚገኙት የምስራቅ ፣ የምዕራብ እና የቄሌም ወለጋ ዞኖች የሲቪል እና የፖሊስ አስተዳደር አባላት በሕግ እንዲጠየቁ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት አካባቢዎቹ ከፌዴራሉ መንግስት በሚመደቡ የሲቪል እና የጸጥታ አስተዳደር አካላት እንዲተዳደሩ እና አካባቢዎቹን የማስተዳደር ስልጣን ላልተወሰነ ጊዜ ሙሉ በሙሉ በፌዴራል መንግስት ስር እንዲውል እንዲያደርግ፤
  4. የፌዴራል እና የክልል መንግስታት የሀገር ኅልውና እና አንድነት ለማጽናት በጦር ግንባር ሽብርተኞችን ማሸነፍ ብቻውን በቂ አለመሆኑን በመረዳት እና በአሸባሪዎች እና ተባባሪዎቻቸው እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ በአንድ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት ብቻ ሳይሆን ፣ የሀገራችን ኢትዮጵያ እና መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ደኅንነት አደጋ ላይ የጣለ ግዙፍ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት መሆኑን ግንዛቤ በመያዝ ፣ እየተፈጸመ ያለው የዘር ጭፍጨፋ ወንጀል እንዲቆም ፣ ወንጀለኞቹ እንዲጠየቁ እና ጭፍጨፋው ቀጣይነት እንዳይኖረው ቁርጠኛ የፖለቲካ አቋም እንድትይዙ እና ተጨባጭ እርምጃዎችን እንድትወስዱ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፤
  5. ከዚህ ቀደም ፓርቲያችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በተደጋጋሚ ባቀረብነው የመፍትሄ ሃሳቦች እና ጥሪ መሰረት ፥

5.1. የፌዴራሉ እና የክልል መንግስታት ለጥቃት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች በቂ የስጋት ትንተና እንዲሰሩ እና ቀጣይ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችል በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ፤

5.2. መንግስት ለጥቃት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑ ዜጎችን በማደራጀት ፣ በማስታጠቅ እና አመራር በመስጠት ከመሰል ጥቃቶች ራሳቸውን የሚከላከሉበትን አስቻይ ሁኔታ እንዲፈጥር፤

5.3. ጥቃቱ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች ከሕይወት የተረፉ ነዋሪዎች አሁንም በከፍተኛ ስጋት ውስጥ የሚገኙ ስለሆነ አፋጣኝ ሕይወት አድን ድጋፍ እንዲደረግላቸው እና ለተጎጅዎች እና ቤተሰቦቻቸው አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርሳቸው፤

5.4. የዘር ፍጅት ወንጀልን የፖለቲካ ግብ ማራመጃ መሳሪያ ካደረጉት የሽብር ቡድኖች እና ተባባሪዎቻቸው አቋም ባልተናነሰ ፣ ችግሩ መዋቅራዊ እና ሥርአት ሰራሽ ገጽታ ያለው መሆኑን በመረዳት መንግስት እና መላ ኢትዮጵያውያን ጥቃቱን በዘላቂነት ለማስቆም የሚያስችል መዋቅራዊ እና ሥርአት ሰራሽ ሽግግር እንዲደረግ እና ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ዋስትና የሚሰጥ ሥርአት እና ሀገር ለመገንባት እንዲረባረቡ፤

5.5. የመንግስት ባለስልጣናት እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥቃቱን በይፋ ማውገዝ መጀመራቸው የሚበረታታ ሆኖ ፣ ወንጀሉን በስሙ እንዲጠሩ እና ከማውገዝ ባለፈ ተጨባጭ እርምጃዎች እንዲወስዱ ጥሪያችንን እያሰተላለፍን ፤ በተለይም የፌዴራሉ መንግስት እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተከታታይ እና በመደበኛ ሁኔታ እየተፈጸመ ያለው የዘር ፍጅት እና የዘር ማጥፋት ወንጀል ተጨባጭ ፣ ግልጽ እና ተገማች አደጋ (Clear and Present Danger) በመሆኑ ፣ የችግሩ ምንጭ የሆኑ የህግ ፣ የመዋቅር እና የሥርአት-አቀፍ ችግሮች እስኪፈቱ ድረስ እና ችግሩ ወደለየለት እና አጠቃላይ የዘር ፍጅት (Full-Scale Genocide) ከመድረሱ በፊት አደጋውን መከላከል የሚቻለው የዘር ማጥፋት እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መከላከል የሚያስችል ብሔራዊ ፖሊሲ ፣ ስትራቴጅ ፣ ሕግ እና አሰራር (National Mechanism for the Prevention of Genocide and other Atrocity Crimes) ስራ ላይ በማዋል በመሆኑ ፣ የፌዴራሉ መንግስት እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፖሊሲውን እና አሰራሩን ስራ ላይ በማዋል ግዙፍ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት የሆነውን የዘር ፍጅት ወንጀል እንዲከላከሉ ፣ እንዲያስቆሙ እና ወንጀለኞቹን ለሕግ እንዲያቀርቡ፤

5.6. አንዳድ የውጭ ሀገር መንግስታት ባለስልጣናት እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል አስመልክቶ በሚያራምዱት አቋም በመንግስት እና በሽብር ቡድኖቹ መካከል እየተደረገ ያለው ወታደራዊ ግጭት ውጤት አድርጎ በማቅረብ ወንጀሉን የድርድሩ አካል ለማድረግ እየተኬደበት ያለው ርቀት ፣ ከዓለም ዓቀፍ ሕግ ያፈነገጠ አቋም ብቻ ሳይሆን ፣ ፍፁም ኢሰብዓዊ፣ ኢሞራላዊ እና ለዘር ፍጅቱ እየተሰጠ ያለ ሥልታዊ ድጋፍ ሆኖ የሚቆጠር መሆኑን ግንዛቤ እንድትወስዱ እያሳሰብን ፣ እየተፈጸመ ያለውን ወንጀል በስሙ “የዘር ማጥፋት ወንጀል” ብላችሁ እንድትጠሩ ፤ የዘር ማጥፋት ወንጀሉን እየፈጸሙ ያሉትን ይፋዊ የ”ትግል” አጋሮቹን ኦነግ-ሸኔ እና ትሕነግ-ወያኔን በዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጻሚነት እንድትፈርጁ ፣ በየሀገሮቻችሁ ተቀምጠው የዘር ፍጅት ቅስቀሳ የሚያደርጉ ሚዲያዎች እና ግለሰቦች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንድትወስዱ፤

ጥሪያችንን እያስተላለፍን በተፈጸመው ጭፍጨፋ ሕይወታቸው ላለፉ ወገኖቻችን ነብሳቸው እንዲማር ፣ ለጥቃቱ ሰላባ ቤተሰቦች ፣ ለመላው የአማራ ሕዝብ እና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውን በሙሉ መጽናናትን እንመኛለን፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
አዲስ አበባ፣ ሸዋ
ሰኔ 28 ቀን 2014 ዓ.ም

Exit mobile version