ETHIO12.COM

“ዛሬ ኃያል ነን የሚሉ አገራት አገራችን ላይ ግራጫ ጦርነት እያካሄዱባት ነው”

የእንደራሴዎች ምክርቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ከጥያቄዎቹ የሚከተሉት ነበሩ፤

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በግፍ ሕይወታቸውን ላጡ፣ ለተገደሉ ንፁኃን ዜጎች የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ለምክር ቤቱ ገለፁ 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በግፍ ሕይወታቸውን ላጡ፣ ለተገደሉ ንፁኃን ዜጎች የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ጀምረዋል።

ዜጎች ባልሰሩት ወንጀል፣ በማይመለከታቸው ጉዳይ፣ በአገራቸው በቄያቸው ሕይወታቸውን ለማሻሻል ደፋ ቀና ሲሉ ባልተገባ መንገድ ሕይወታቸውን የሚቀጥፉ ገዳዮች፣ አጥፊ ስብስቦች ያደረሱባቸው ጥቃት በእጅጉ የሚያሳዝነን ከመሆኑም ባሻገር ሕይወታቸውን ለመታደግ ባለመቻላችን እንደ አገር፣ እንደ መንግስት እንደ ሕዝብ ጥልቅ ሀዘን ይሰማናል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የንፁሃን ደም በከንቱ የሚያፈሱ የሸኔም ሆነ ሌላው ኃይል ላይ በጀመርነው መልክ የመከላከል ስራችንን መቀጠል ከቻልን ይጠፋሉ ያሉት ጠቅላይ ሚነስትሩ እነዚህ ኃይሎች ምንም ዓላማ የሌላቸው መሆናቸውን ገልፀዋል።

በመንግስት እስካሁን በርካታ የህግ ማስከበር እርምጃዎች ተወስደዋል፤ እስካሁንም በሚፈጠሩ ችግሮች ሁሉ የጸጥታ ኃይሎች ሳይከፈላቸው የህይወት መስእዋትነትም ጭምር እንደሚከፍሉ አስታውሰዋል።

በደራሼ፣ ጊምቢ፣ጋምቤላ፣ ደምቢዶሎ እና በአምቦ አካባቢዎች የመንግስት ጸጥታ ኃይሎች በተመሳሳይ ህይወታቸውን ገብረዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዜጎቻቸውን ለመታደግ ህይወታቸውን ለሚከፍለው የጸጥታ ኃይሎች ምክር ቤቱ ክብር ሊሰጥ እንደሚገባም በአፅንኦት ተናግረዋል።

መንግስት አሸባሪ አይደለም፤ አሸባሪን የሚፋለም ኃይል ነው!!” 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እየሰጡ በሚገኘው ምላሽ “መንግስት አሸባሪ አይደለም፤ አሸባሪን የሚፋለም ኃይል ነው!!” ብለዋል።

የአሜሪካን ልምድ እንደ ምሳሌ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ስድስት ወራት ከ1 ሺህ በላይ አሜሪካውያን በሽብር ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አልቃይዳ ትይዩ ህንፃዎችን በአሜሪካ ሲያፈነዳ ሚስቱ ልጁ ወንድሙ የሞተበት አሜሪካዊ ከመንግስት ጎን ሆኜ አሸባሪን እንፋረዳለን ይላል፤  እኛ ጋር ደግሞ ይሄ መንግስት ይላል።  ይሄ ትክክል አይደለም። መንግስት አሸባሪ አይደለም፤ አሸባሪን የሚፋለም ሃይል ነው።” ብለዋል።

ጠቅላ ሚኒትሩ አሸባሪዎችን ከዘር ጋር ማያያዝ ችግር አለበት፤ በድምሩ ሸኔ እና ሌሎች የሽብር ቡድኖች የራሳቸው እግር የላቸውም ነገር ግን እግር የሚገጥምላቸው ሲያገኙ ጥፋት ይፈፅማሉ ነው ያሉት።

አሸባሪዎች የራሳቸው ማሰቢያ ጭንቅላት የላቸውም፤ ታስቦ ስራ ሲሰጣቸው ጥፋት ይፈፅማሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንፁሃን ዜጎችን በዚያ ሁኔታ መግደል የሽብር ባህሪ ነው፤ ኢትዮጵያ ለመበተን እና ለማፍረስ የሚፈልጉ ኃይሎች መሻትን በገሃድ የሚያሳይ ነገር ነው ብለዋል።

መንግስት ከዜጎች በተሻለ የሽብር መረጃን ቀድሞ እንደሚያገኝ ማሰብ ጠቃሚ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሳሽ እና ጠያቂ ብቻ ሳይሆን ኃላፊነት የሚወስድ እና የሚጠብቅ ዜጎችም ያስፈልጋሉ ነው ያሉት።

የፀጥታ ኃይሉ በየቀኑ ከአሸባሪ ጋር የህይወት መስዋዕትነት የሚከፍል ኃይል ነው፤ የህዝብ ስራ አሸባሪውን ከለየ በኋላ ከመንግስት ጎን ቆሞ ጥፋት እንዲቀንስ ማድረግ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያን ከጠላት ጋር ወደ ታች መጎተት ትርፉ ፀፀት እና መከራ ብቻ ነው!!”

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ኢትዮጵያን ከጠላት ጋር ወደ ታች መጎተት ትርፉ ፀፀት እና መከራ ብቻ መሆኑን ተናገሩ። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለፓርላማው እየሰጡ ባለው ማብራሪያ፣ “የኢትዮጵያ የዳገት ጉዞ ተጨማሪ ኃይል ስለሚፈልግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በትብብር ወደ ላይ እንዲገፋት፣ ካልቻለም ወደ ታች እንዳትንሸራተት ታኮ እንዲያስቀምጥላት አደራ ብለዋል።

ነገር ግን ጠላት እንድንከፋፈል ስለፈለገ ብቻ ሀገራችንን ወደ ታች መጎተት ትክክል አለመሆኑን ገልጸዋል። 

የመንን እንደ ምሳሌ ያነሡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “ሀገራቸውን ያፈረሱ ባንዳዎች ያተረፉት ነገር ፀፀት እና መከራ ብቻ ነው። ኢትዮጵያም ወደዚያ ብትሔድ ጠላቶች የመንን እንዳደረጉት ሁሉ “እዳው ገብስ ነው” ብለው ይሄዳሉ።” ብለዋል።

ማንም ሀገር ኢትዮጵያን ማሸነፍም ሆነ ማፍረስ አይችልም። መግደል ይችላል፣ ማጋደል ይችላል፣ በኢኮኖሚ ጫና ማዳከም ይችላል ነገር ግን ኢትዮጵያን ማፍረስ ሆነ ማዳከም እንደማይችልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ሁልግዜ ለሰላም ቅድሚያ ይሰጣል!!”

የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ሁልግዜ ቅድሚያ ለሰላም እንደሚሰጥ በአንክሮ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ለሰላምም ለጦርነትም የምንወስነው በብሔራዊ ጥቅማችን ጉዳይ ነው!! የኢትዮጵያ አንድነት፣ የኢትዮጵያ ጥቅም በሰላም መንገድ ማስጠበቅ ሲሳነን የሕይወት ዋጋ መስዋትነት እንከፍላለን። ከዛ በመለስ ተስፋ አለ ብለን ካሰብን ሁሌም ለሰላም በራችን ክፍት ነው።!!” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ እየሰጡ በሚገኘው ማብራሪያ “ኢትዮጵያ ላይ አሁን እየተካሄደ ያለው የግራጫ ጦርነት መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነጭ መዝገብ ላይ ወይም፤ ጥቁር መዝገብ ላይ የተቀመጠ ሳይሆን  የግራጫ ጦርነት ባህርይ ነው ያለው፤ የመረጃ ጦርነት ነው። በወለጋ አንድ ቀበሌ ውስጥ ሞት የሚካሄድ ከሆነ  ብዙ ዓለም ያለ የመረጃ ተዋናዮች ያውቁታል፤ ጫፍ ጫፍ ይላሉ ብለዋል።

ይህንን ተከትሎም “የዓለም ሚድያዎች ይዘግባሉ። እኛ ገና መረጃውን ሰምተን ወታደር ስንሯሯጥ  ከኛ በላይ መረጃውን የሚያሰፋ ሃይል አለ። ይህ መረጃ ሃይል በስንዴ ላይ በግሪን ሌጋሲ ላይ ኢትዮጵያ ብትሰራ፤ ስራም አላጣ እዛ አይገኝም!!” ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የህግ ማስከበርን በተመለከተም መንግስት ይህንን ለመከላከል ስትራቴጂ ነድፎ እየሰራ ነው። የመጀመርያው “መከላከል” ነው። 

ከዚህ አንጻር ተቋማትን በማጠናከር አደጋው ከመድረሱ በፊት ለመከላከል እየተሰራ ነው ሁለተኛው ” መከታተል” ነው። የክትትል አቅማችንን ለማሳደግ እየሰራን ነው። 

ሶስተኛው “መጠበቅ” ነው። የጥቃት ዋና ዋና ትኩረት የሆኑ ፕሮጀክቶች፣ ተቋማትን እንጠብቃለን የማንደርስባቸውን ደግሞ ህዝብ ተደራጅቶ እንዲጠብቃቸው እናደርጋለን።

አራተኛው “መዘጋጀት” ነው። በየቀኑ መዘጋጀት። ሰው ሞተ ስንባል ተጯጩህን የምንረሳ ሳይሆን ተጨማሪ ሞት እንዳይኖር በየቀኑ መዘጋጀት ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመከላከል እየሠራን ነው” 

መንግሥት አገር ማሻገርን በጽኑ ማመን ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ ከሆነ መስዋትነት የሚከፍል በመሆኑ በግርግር የሚፈርስ አለመሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገልጸዋል።

በዋናነት ቀድሞ መንግስት ዜጎችን የመከላከል፣ አሸባሪዎችን የመከታተል፣ ተቋማትን የመጠበቅ እና ለሚቀጥለው ፈተና እንደ አገር በመትጋት በየቀኑ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

በዚህም የመንግሥት መዋቅርን ከማጽዳት አንጻር ከ500 በላይ የሚሆኑ ግለሰቦች መንጥሮ ማውጣት መቻሉን ገልጸዋል።

ይሁንና መረጃ ደርሶን እነኚህ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው መረጃ በማሾለክ ለአሸባሪዎች ቀድመው በመስጠት የሚወሰደውን እርምጃ ያኮላሻሉ ብለዋል።

እየተካሄደ ያለው ጦርነት የተቀናጀ ሚዲያ ዘመቻ ወይም በግራጫ ጦርነት በአንድ ጊዜ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ይሰማሩብናል በማለት አብራርተዋል።

በታሪክ ባንዳዎች አገራችንን በተለያዩ ጊዚያት ሲያቆስሏት ኖረዋል፤ ዛሬም የሚታየው ይሄው ነው በአፍሪካም የተለያዩ አገራት ፈርሰዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በመሆኑም እነሱ ያተረፉትን ፀፀትና መከራ እንዳይመጣ በጽናት መታገል ይገባል ብለዋል።

ሰሞኑን እዚህም እዚያም ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ግድያ እና መጎሳቆል ከባድ ቢሆንም ፈተናውን ተሻግረን በትብብር እና በጋራ አገራችንን ለማሻገር መትጋት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ከምክር ቤቱ እና አገር ከሚወዱ ዜጎች የሚጠበቀው አገራችንን መደገፍ ወይም ቢያንስ እንዳትንሸራተት ታኮ ማድረግ እንጂ ጠላት እንድንከፋፈል የሚያደርገውን ነገር መደገፍ ተገቢ አይደለም ብለዋል።

የአሸባሪዎች ዓላማ አገር መምራት ሳይሆን አገር ማፍረስ በመሆኑ ልንታገላቸው ነው የሚገባውም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ኢትዮጵያ ለዓለም ያላት አስተዋፅኦ እና ለዕድገት ያላት ተስፋ፣ ዕድልም ፈተናም ሆነውባታል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ “ኢትዮጵያ ለዓለም ያላት አስተዋፅኦ እና ለዕድገት ያላት ተስፋ፣ ዕድልም ፈተናም ሆነውባታል” ሲሉ ተናገሩ። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል። 

“‘ኢትዮጵያ የሥልጣኔ መነሻ ከሆኑ ሀገራት አንዷ ናት’ በሚለው ላይ የጋራ መግባባት አለ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እኛ ለዚህ ጉዳይ ብዙም ትኩረት ባንሰጥም ሌሎች ግን ትልቅ ቦታ እንደሚሰጡት ገልጸዋል። 

ከ100 ሺህ የሚበልጡ የኢትዮጵያ ቅርሶች እና ጥንታዊ ጽሑፎች በተለያዩ የዓለም ሀገራት ላይብረሪዎች እንዳሉ ገልጸው፣ የተጻፈ ብቻም ሳይሆን በግልጽ የሚዳሰሱ እና የሚታዩ ቅርሶች አሉን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። 

“ይህ ታሪክ ለእኛ ረከሰ እንጂ ለሌሎች አልረከሰም፤ ይህቺ ታሪካዊት ሀገር መዳከም አለባት የሚሉ ኃይሎች በርካታ ናቸው” ሲሉም ተናግረዋል። 

በሌላ በኩል ሀገራችን በተፈጥሯዊ ሀብት የታደለች ከመሆኑም ባሻገር በቅኝ ግዛት ያልተገዛች በመሆኗ ቅኝ በተገዙት ሀገራት ልክ አልተበዘበዘችም። 

በዚህም ምክንያት ዛሬ ‘ኃያል ነን’ የሚሉ ሀገራት ኢትዮጵያ ላይ ትኩረት በማድረግ ‘ግራጫ ጦርነት’ እያካሄዱባት ነው ብለዋል። 

ግራጫ ጦርነቱም በሚዲያ /በመረጃ/፣ በዲፕሎማሲ፣ በሳይበር እና በተልእኮ ጦርነት የተቀነባበረ እንደሆነ ዘርዝረዋል። 

የሚዲያዎቹን የሴራ ሥራ በተመለከተ ሲናገሩ፣ በኢትዮጵያ አንድ ቦታ ላይ ችግር የሚከሰት ከሆነ ሚዲያዎቹ በዚያ ጉዳይ ላይ አሉባልታዎችን ያራግባሉ፤ ችግሩ ሲፈጠርም ከሁሉም ቀድመው ስለችግሩ ይተነትናሉ ብለዋል። 

ጠላቶች የተልእኮ ጦርነትን ኢትዮጵያ ላይ የሚያካሂዱት ደግሞ እንደ ሸኔ ያሉ ‘እግር አልባ’ ሲሉ የገለጿቸውን ተላላኪዎችን በመጠቀም ነው። 

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ የጠላቶች ሴራ ኦሮሞ እና አማራን፣ አፋር እና ሶማሌን፣ ሲዳማ እና ወላይታን፣ ቤኒሻንጉልን ከኦሮሞ እና ከአማራ በማባላት እንዲሁም አማራን እርስ በርሱ፣ ኦሮሞንም እርስ በርሱ በማባላት ኢትዮጵያ ሰላም እንዳታገኝ ሌት ተቀን ይሠራሉ። 

ከዚያም ባለፈ ሙስሊሙን እና ክርስቲያኑን ማባላት ወይም ሙስሊሙ እርስ በርሱ እንዲባላ ማድረግ የሴራቸው አካል ነው። 

ይሁን እንጂ በዲፕሎማሲም፣ በሴራም፣ በሚላላኩ ጀሌዎች እና ባንዳዎች ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ኢትዮጵያን ማፍረስ አልቻሉም ብለዋል። 

የመጨረሻው ምርጫቸው በሰላም አስከባሪ ስም ኢትዮጵያን ለማፍረስ መሞከር እንደሆነም ተናግረዋል። 

ነገር ግን የትኞቹም ኃይሎች መግደል እና ማጋደል ይችላሉ፣ የኢኮኖሚ ጫና ሊያደርጉ ይችላሉ፤ በፈለጉት በኩል ቢሞክሩም ኢትዮጵያን ማፍረስ አይቻልም ሲሉ አረጋግጠዋል። 

ኢትዮጵያ ባለፉት 11 ወራት 309 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አግኝታለች

ኢትዮጵያ ባለፉት 11 ወራት ለማስገባት ከታቀደው 330 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከ309 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አግኝታለች፤ በዚህም ከእቅዱ 93 በመቶ ገቢ ለመሰብሰብ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእረፍት መልስ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን አስመልክተው ለምክር ቤቱ እየሰጡ በሚገኘው ማብራሪያ ዘንድሮ የተሰበሰበው ገንዘብ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ50 ቢሊዮን ብር ጭማሪ እንዳለው አስታውቀዋል። 

በዚህም የተገኘው ገቢ የ19.4 በመቶ እድገት ማምጣቱን እና ለተገኘው ውጤት በገቢ መስሪያ ቤት ያሉ አመራር እና ሠራተኞች ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል። 

ወጪን በተመለከተም አገሪቱ ባለፉት 11 ወራት ከ500 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን አሁንም በገቢ እና ወጪ በኩል አለመመጣጠን እንደሚታይ ጠቁመው ወጪን ያበዛው ዋናው ጉዳይ ያለብን እዳ እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

ባለፈው አመት ብቻ 100 ቢሊዮን ብር እዳ መከፈሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

ሌላው ከፍተኛ ውጤት የተገኘው በኤክስፖርት እንደሆነ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለዚህም ውጤት በአጠቃላይ በኢኮኖሚው ሴክተር ተሳታፊ የነበሩ ተዋናዮች ምስጋና እንደሚገባቸው አስታውቀዋል።

በኤክስፖርት የተገኘው እምርታ በጣም ግዙፍ እንደሆነ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከሴክተሩ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት መቻሉን ነው የገለፁት።

ፈተናን ለፖለቲካ አጀንዳ ማዋል ትክክል አይደለም”  

ለተማሪዎች የሚሰጥ ፈተና ተማሪዎችን ለመመዘን የሚውል ቢሆንም ይህን ለፖለቲካ አጀንዳ  ማዋል ትክክል አለመሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ16ኛ መደበኛ ጉባዔው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር አካሂዷል።  

የፈተና ዝግጅት ሂደት ላይ የአውቶሚሽን ስርዓት ለመዘርጋት ከቻይና መንግስት ጋር በመተባበር ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

የፈተና አሰጣጥ ሂደቱን ሙሉ ለሙሉ አውቶሜት ለማድረግ እየተሰራ ቢሆንም በኢትዮጵያ የተፈታኞች ብዛት እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር ተጨማሪ ኮምፒውተሮች አስፈልገዋል ብለዋል።

ኮምፒውተር በማቅረብ በጋራ የሚሰራው ድርጅት ከኮሮናቫይረስ መምጣት ጋር ተያይዞ ምርቶቹን በማቆሙ ለሁለት አመት ለሚጠጋ ጊዜ የአውቶሚሽን ስርዓት ለመዘርጋት የሚደረገው ጥረት መዘግየቱን ተናግረዋል።

አሁን ላይ የአውቶሜሽን ስርዓቱን በመጠቀም ፈተናዎች  ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ ቢሆንም ይህን ማሳካት ካልተቻለ እንኳን የነበሩ አሰራሮችን በማሻሻል ሌብነት የሚቀንስበት መንገድ እንደሚፈጠር ገልፀዋል። 

የስራ ዕድል ፈጠራን በተመለከተ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት በሚኒስቴር መስሪያ ቤት ደረጃ በዚህ ዘርፍ ላይ የሚሰራ ተቋም ከማቋቋም ጀምሮ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

በተለይም በስራ ስምሪት፣ በቋሚነት የስራ እድል ከመፍጠር እና  ከሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች አንፃር ሪፎርም ሲሰራ መቆየቱንም ነው የገለፁት።

በሪፎረሙ መሰረት ሰራተኛውን ወደ ስራ ለማሰማራት በሚደረገው ጥረት ከምልመላ እስከ ስምሪት 28 የሚጠጋ ሂደት መኖሩን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ይህን በመፈተሽ ወደ 14 በማውረድ ከግማሽ በላይ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።

የዛሬ አመት ከነበረው የስራ እድል ፈጠራ በተሻለ አሁን ላይ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ሁለት ሚሊዮን በላይ  ዜጎች ሁሉም በቋሚነት የተመዘገቡ መሆናቸው ትልቅ እድገት የታየበት ነው ብለዋል። 

የኑሮ ውድነትን በተመለከተ የዋጋ ግሽበት በኢትዮጵያ ለሁለት አስርት አመታት እየጨመረ የመጣ ጉዳይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአለም አቀፍ ደረጃ በየጊዜው የሚከሰቱ ቀውሶች ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ እቃዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እንዲፈጠር አድርጓል ብለዋል።

የበጀት ጉድለት በሚፈጠርበት ጊዜ ጉድለቱን ለመሙላት ከብሄራዊ ባንክ ብቻ ብድር የሚቀርብ ከሆነ የዋጋ ግሽበቱ ሊባባስ ከመቻሉ አንጻር ከብሄራዊ ባንክ የሚወሰድ ብድር ን በእጅጉ መቀነስ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። 

መንግሰት የበጀት ጉድለት ሲከሰት ጉድለቱን ለማሟላት ጥረት የሚያደረግው ከግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህን በማጠናከር በዋጋ ግሽበት የሚፈጠረውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ ይሰራል ብለዋል። (ኢፕድ እና ኢቢሲ)

(ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ)

Exit mobile version