Site icon ETHIO12.COM

“በሕይወት የመኖር መብት እጅግ የከፋ አደጋ ውስጥ ወድቋል” ኢሰመኮ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከሰኔ 2013 አስከ ሰኔ 2014 ዓ.ም በሀገሪቱ በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዓመታዊ ሪፖርት ላይ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ.ር) አንዳሉት ባለፉት 12 ወራት በህይወት የመኖር መብት እጅግ በከፋ ሁኔታ ውስጥ እንዳለ ቀጥሏል ብለዋል። በዓመቱ የትግራይ ጦርነት ወደ አማራ ክልል መስፋፋቱን ተከትሎ ኾን ተብሎ በትግራይ ኀይሎች በተወሰዱ ርምጃዎች 346 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል በተለይ በወለጋ ዞኖች ከነሐሴ 2013 ዓ.ም ጀምሮ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ በተፈፀመ ጥቃት በአብዛኛው በአማራ ብሔር የገጠር እና የከተማ ነዋሪዎች ላይ ያነጣጠረ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት ሴቶችን ጨምሮ ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል ብለዋል።

ዶክተር ዳንኤል ወንጀሉ በሰብዓዊነት ካይ የተፈፀሙ ግፎች፣ የጦር ወንጀሎች እና ሌሎች ወንጀሎች አንደኾኑ ገልጸው ጉዳዩ የዘር ማጥፋት አንደኾነ ገና ጥናት ተደርጎ የሚረጋገጥ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡ ኮሚሽነሩ ጥቃቱ ግን ብሔር ተኮር መኾኑን አረጋግጠናል ብለዋል። ጥናት ለማድረግ አካባቢው ገና አመች ያልኾነ እና ከባድ ወታደራዊ አንቅስቃሴ ያለበት በመኾኑ ጥናቱ ይቆያል ነው ያሉት።

ከዘፈቀደ እስር እና ጠለፋ አንዲሁም አስገድዶ ከመሰወር ጋር በተገናኘ በዓመቱ በተለይ በሰሜኑ ጦርነት የተሳተፉ ሁሉም ኀይሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ በዘፈቀደ እስር ጠለፋ እና አስገድዶ መሰወር ፈጽመዋል ብለዋል። ይህም በሰበዓዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል ሲኾን ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል ሊኾን በሚችል መልኩ ተፈጽሟል ብለዋል።

በዓመቱ በአማራ ክልል ብቻ ሕግን እና ሰላምን ለማስከበር በሚል ምክንያት ከ10 ሽህ ሰዎች በላይ በኢመደበኛ ኀይሎች ታጣቂዎች አባል ናችሁ በሚል እና የተፎካከሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ጭምር ከፍርድ ቤት ትእዛዝ ውጭ ታስረዋል ነው ያሉት።

ከአመለካከት እና ሃሳብን በነጻነት ከመግለጽ መብት ጋር በተገናኘ በተለያዩ ወቅቶች 39 የሚዲያ ሰራተኞች ተይዘው ከቀናት እሰከ ወራት በእስር እንዲቆዩ መደረጋቸውን አስረድተዋል። በትግራይ ክልል ይህ ሪፖርት ይፋ አስከተደረገበት ጊዜ ድረስ 15 የሚዲያ ሰራተኞች በክልሉ ባለስልጣናት ትእዛዝ እንደታሰሩም አስረድተዋል።

በእስር ላይ ያሉ እና የተያዙ ሰዎችን መብቶች በተመለከተ ፖሊስ ጊዜውን ጠብቆ ለፍርድ ቤት አለማቅረብ፣ የዋስ መብት የተፈቀደላቸውን ተጠርጣሪዎችን ከእስር አለመልቀቅ፣ በታሳሪዎች ላይ ያለአግባብ አያያዝ፣ ለኮሚሽኑ ባለሙያዎች በቂ መረጃ አለመስጠት እና ተባባሪ አለመኾን። የፍርድ ቤት ትእዛዝን አለማክበር እና ሌሎችም ተፈጽመዋል ነው ያሉት።

በግጭት እና የፈጥሯዊ አደጋ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከቀያቸው እና ከመደበኛ መኖሪያው መፈናቀላቸውንም ጠቅሰዋል። በዚህም በተጠለሉበት ቦታ በከፍተኛ ችግር ውስጥ አንደሚኖሩ ጠቅሰው መሰረታዊ ፍላጎቶች ማቅረብ ላይም ከፍተኛ ችግር መኖሩን አመላክተዋል። ተበዳዮችን ከመካስ እና አጥፊዎችን ተጠያቂ ከማድግ አንጻርም ብዙ ሥራ እንደሚቀርም አብራርተዋል።

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን (አሚኮ)

Exit mobile version