በጦርነትና ከዳኝነት ውጪበአማራና በአፋር ከ749 በላይ ንጹሃን መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እና ሚሊሺያዎችም የትግራይ ኃይሎች እና የኦነግ-ሸኔ አባላት ወይም ደጋፊ ናቸው በሚል የጠረጠሯቸው ሰዎች ላይ ከዳኝነት ውጪ የሆኑ ግድያዎችን ፈጽመዋል፤ የአካል ጉዳትም አድርሰዋል።

BBC Amharic – የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በአማራ እና አፋር አካባቢዎች 749 በላይ ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን አስታወቀ።

ኢሰመኮ በአማራ እና አፋር ክልሎች የተፈጸሙ ናቸው ባላቸው የሰብዓዊ መብቶች እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ ጥሰቶች ላይ ያደረገውን ምርመራ ሪፖርት ይፋ አድርጓል። 

በዚህ ሪፖርት ላይ በጦርነት ምክንያት ቢያንስ 403 እንዲሁም ሕገ-ወጥ እና ከዳኝነት ውጪ በተፈጸመ ግድያ 346 ሲቪል ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ገልጿል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ለእነዚህ ግድያ ሁሉተም ተዋጊ ኃይሎችን ተጠያቂ ቢያደርግም፤ ትልቁን ድርሻ የሚይዙት ግን የትግራይ ኃይሎች ናቸው ብሏል። 

ምርመራ እንዴት ተካሄደ?

ኢሰመኮ ይህን ምርመራ ለማካሄድ በሦስት ክልሎች ማለትም በአማራ፣ ትግራይ እና አፋር 29 አባላት ያሉት የምርምራ ቡድን አሰማርቷል። 

ምርመራው ትኩረት ያደረገው ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ 2014 ዓ.ም. በአማራ እና አፋር ክልሎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሲሆን፤ በትግራይ ክልልም በአየር ጥቃቶች ምክንያት የደረሱ ጉዳቶችን እና የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን በተመለከተ መረጃ ሰብሰቧል። 

ኢሰመኮ መረጃውን ከተለያዩ አካላት ሰብበቧል። ለ427 ሰዎች ቃለ መጠይቆችን አድርጓል። 12 የቡድን ውይይቶችን አከናውኗል። ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ ደረጃ ከሚገኙ ባለሥልጣናት ጋር 136 ስብሰባዎችን አካሂዷል፤ የሰነድ ማስረጃዎችንም ተመልክቷል። 

ኮሚሽኑ ይፋ ያደረገው ሪፖርት ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች የተፈጸሙ ሁሉንም ጥሰቶችን የሚሸፍን ባይሆንም፤ የተፈጸሙ ዋና ዋና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ግን መካተታቸውን ገልጿል።

የምርምራው ግቶች

ጦርነቱ በአብዛኛው ሲቪል ሰዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በመካሄዱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሲቪል ሰዎች ሞተዋል፣ ለአካል እና ለሥነ ልቦና ጉዳት ተዳርገዋል፣ ፆታዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶችም ተፈጽመውባቸዋል ይላል ሪፖርቱ። 

በሰው ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ በግል ንብረቶች እና እንደ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት ባሉ የሕዝብ መገልገያ መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እና ዝርፊያ ማጋጠሙን ኢሰመኮ አውስቷል። 

እንደ ሪፖርቱ ከሆነ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች ሲቪሎችን እንደከለላ በመጠቀም በከተሞች ጦርነት በማካሄድ በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት፣ አካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት እንዲከሰት አድርገዋል።

ኮሚሽኑ በአፋር እና በአማራ ምርመራ ባደረገባቸው ሥፍራዎች ሆነ ተብለው የተፈጸሙ ሕገወጥ ግድያዎችን ሳይጨምር፤ በጦርነት 403 ሲቪል ሰዎች ለሞት እንዲሁም 309 ሰዎች ለቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል።

እንደ ምሳሌም ኮሚሽኑ የትግራይ ኃይሎች ሐምሌ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በአፋር ክልል ጋሊኮማ ቀበሌ በፈጸሙት ጥቃት 27 ሕፃናትን ጨምሮ 107 ሲቪል ሰዎችን ገድለዋል ብሏል። 

ከዚህ በተጨማሪም የትግራይ ኃይሎች የአማራ እና የአፋር ክልል ከተሞችን ከመቆጣጠራቸው አስቀድሞ ከተሞች ላይ በተኮሷቸው ከባድ መሳሪያዎች ሲቪል ሰዎች እንዲሞቱ እና እንዲቆስሉ አድርገዋል ይላል።

የትግራይ ኃይሎች በአማራ ክልል የአርሶ አደሮችን መኖሪያ ቤት እንደ ምሽግ አድርገው በመዋጋታቸው በአገር መከላከያ ሠራዊት በተተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች 6 ሲቪሎች ስለመገደላቸው፤ እንዲሁም የትግራይ ኃይሎች ቀብረዋቸው አልያም ሜዳ ላይ ጥለዋቸው በሄዱ ፈንጂዎች ምክንያት 5 ሕጻናት መሞታቸውን ገልጿል። 

የፌደራሉ መንግሥትም በአማራ ክልል በፈጸማቸው የድሮን ጥቃቶች በወልዲያ ከተማ ብቻ 6 ሲቪሎች መገደላቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።

ሕገ ወጥ እና ከዳኝነት ውጪ የተፈጸመ ግድያ 

ኢሰመኮ ምርመራ ባደረገባቸው የአማራ እና የአፋር ክልል አካባቢዎች በዋነኝነት በትግራይ ኃይሎች ቢያንስ 346 ሲቪል ሰዎች በሕገ ወጥ መንገድ ተገድለዋል ብሏል። 

የትግራይ ኃይሎች እነዚህን ሰዎች የገደሏቸው፤ ‘ለመንግሥት ኃይሎች ሰላይ ናችሁ፣ የጦር መሳሪያ አምጡ፣ መከላከያ፣ የልዩ ኃይል ወይም የፋኖን ታጣቂዎችን አግዛችኋል፣ የእነዚሁ አባላት የሆኑ ሰዎች ቤተሰብ ናችሁ’ በሚሉ ምክንያቶች በበቀል እርምጃ ነው” ብሏል።

በተመሳሳይ እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው እና መንግሥት ኦነግ-ሸኔ የሚለው ታጣቂ ቡድን በተቆጣጠሯቸው ስፍራዎች በነበሩ የመንግሥት አስተዳደር ኃላፊዎች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ እንዲሁም መንግሥትን ይደግፋሉ ባሏቸው ሲቪል ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ግድያን መፈጽሙን ኢሰመኮ በሪፖርቱ አመልክቷል። 

በሌላ በኩል የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እና ሚሊሺያዎችም የትግራይ ኃይሎች እና የኦነግ-ሸኔ አባላት ወይም ደጋፊ ናቸው በሚል የጠረጠሯቸው ሰዎች ላይ ከዳኝነት ውጪ የሆኑ ግድያዎችን ፈጽመዋል፤ የአካል ጉዳትም አድርሰዋል።

እንደ ሪፖርቱ ከሆነ የትግራይ ኃይሎች በአማራ ሰሜን ወሎ ዞን ከነሐሴ 24 እስከ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ቢያንስ 47 ሲቪሎችን፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ኅዳር 23/2014 ዓ.ም. ደግሞ 40 ሲቪል ሰዎችን ገድለዋል።

በሌላ በኩል የመከላከያ ሠራዊት ወታደሮች በታኅሣሥ ወር 2014 ዓ.ም. በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ቁጥራቸው ወደ 30 የሚጠጉ ሰዎችን በጅምላ በጥይት ደብድበው ገድለዋል ብሏል ሪፖርቱ።

የዘፈቀደ እስር፣ ጠለፋ እና አስገድዶ አስገድዶ መሰወር

የጦርነቱ ተሳታፊ ኃይሎች ዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶችን እና የሰብአዊነት ሕጎችን ድንጋጌ በሚጥስ መልኩ የዘፈቀደ እስር፣ ጠለፋ እና አስገድዶ መሰወር መፈጸማቸውን ሪፖርቱ ጠቅሷል። 

የትግራይ ኃይሎች በአፋርና አማራ ክልሎች የሚገኙ ቦታዎችን ተቆጣጥረው በቆዩበት ጊዜ መጠነ ሰፊ፣ ጭካኔ የተሞላበትና እና ስልታዊ የሆነ በተናጠል እና በቡድን የተፈጸመ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት በሴቶች፣ በሕፃናት ሴቶችና አረጋዊያን ሴቶች ላይ መፈጸማቸውንም ሪፖርቱ አመልክቷል። 

በደረሰባቸው ፆታዊ ጥቃቶች ከፍተኛ አካላዊ እና ሥነ-አእምሯዊ ጉዳቶች የደረሰባቸው እንዳሉት ሁሉ- እራሳቸውን ያጠፉ ሴቶች ስለመኖራቸው ኢሰመኮ በሪፖርቱ ጠቅሷል።

የጭካኔ፣ ኢሰብአዊና አዋራጅ አያያዝና ቅጣት

ኢሰመኮ የትግራይ ኃይሎች በቁጥጥራቸው ስር ገብተው በነበሩ የአፋር እና አማራ ክልል አካባቢዎች ነዋሪዎችን ገንዘብ አምጡ፣ መረጃ አምጡ፣ የደበቃችሁትን መሳሪያ አውጡ፣ በሚሉና የመሳሰሉ ምክንያቶች በሲቪል ሰዎች ላይ በጭካኔ የመደብደብ፣ የማዋረድ እና የማሰቃየት ተግባር መፈጻማቸውን ገልጿል። 

እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን ደግሞ በአማራ ክልል ከሚሴ ከተማ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት መፈጸሙን የመብት ድርጅቱ ገልጿል።

ተፈናቃዮች እና የእርዳታ አቅርቦት

በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት ወደ አጎራባች ክልሎች መስፋፋቱን ተከትሎ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለው ለከፍተኛ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎች ጉዳቶች ተደርገዋል ይላል ሪፖርቱ።

ተፈናቃዮች መሠረታዊ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶች ያልተሟላላቸው በመሆኑ ችግሩን የከፋ አድርጎታል ይላል። 

ኢሰመኮ በጦርነቱ ምክንያት የሰብዓዊ እርዳታ ፈላጊ ሰዎች ቁጥር ከ8 ሚሊዮን በላይ መሆኑን ያስታወሰ ሲሆን፤ በተለይ በትግራይ ክልል የሚደርሰው ሰብአዊ እርዳታ ላይ በፌደራል መንግሥት እና በክልል መንግሥታት የሚደረጉ አስተዳደራዊና ቢሮክራሲያዊ ሂደቶች አስፈላጊው እርዳታ በሚፈለገው መጠንና ፍጥነት እንዳይደርስ እንቅፋት ሆኗል ብሏል።

በመጨረሻም ኮሚሽኑ የጦርነቱ ተሳታፊዎች በአባሎቻቸው ለተፈጸሙ ጥሰቶች ኃላፊነት በመውሰድና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም በማድረግ ለጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ጠይቋል።

ከዚህ በተጨማሪም ፆታዊ ጥቃት የፈጸሙትን ጨምሮ የሰብአዊ መብት እንዲሁም የሰብአዊነት ሕጎች ጥሰት የፈጸሙ እና ያስፈጸሙ ሰዎችና ቡድኖች ሁሉ ተጠያቂ ለማድረግ ገለልተኛ፣ ተአማኒ እና የሰብአዊ መብቶች ደረጃውን የሚያሟላ የወንጀል ምርመራ እና የክስ ሂደት በአስቸኳይ እንዲጀመር ጨምሮ ጠይቋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸማቸውን ዓለም አቀፍ የመብት ድርጅቶች ባወጧቸው ሪፖርቶች ማመልከታቸው ይታወሳል። 

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው በዚህ ሪፖርት ላይ ከተጠቀሱት ወገኖች መካከል አስካሁን ምላሽ የሰጠ የለም።

Related posts:

«ሕወሓት ጦርነትን እንደ አምልኮ የሚቆጥር ቡድን ነው» – ፕሮፌሰር ሀረገወይን አሰፋ
«በሕገወጦች ላይ ያለ ምኅረት እርምጃ መውሰድ አለብን፤ ይህ የመንግሥት ተግባር ነው» የአማራ ክልል
125 አዳዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆኑ
«በአገሩ መከላከያ ላይ አፉን የሚከፍት ሕዝብ የለም፤ መንግስትም አይታገስም» ክብር ለመከላከያ ሰራዊት!!
በኢትዮጵያና ቱርክ መካከል የተደረገውን የወታደራዊ ማዕቀፍ ስምምነት ምክር ቤቱ አጸደቀ
የሞት ፍርደኛው የ25 ዓመታት ሰቆቃ! ከመሬት በታች የታፈኑት አባት
«ኢትዮዽያን ማስቀጠል ከሚፈልጉት ጎን በመሆናችን የሚከፋ ከአለ እርሱ መፍረሷን የሚናፍቅ ብቻ ነው!»
ደብዳቤ ለኢትዮጵያ - ከቢልለኔ ስዩም
የዓለም ባንክ የ300 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ፈረመ
"እናቴ ፍጹም እስር ቤት እንድትገባ አልፈግም" ብሎ እግሩን ያጣው ወጣት ምስክርነት ለሮይተርስ
"አልዘምትም" ወይም "ከጠላት ጎን እሰለፋለሁ" ማለት ሲቻል ማውሰብሰብና ማድበስበስ አይገባም!
አብዱላሂ ፋርማጆ ለአዲሱን ፕሬዝዳንት «ሁሉም ወገኖቼ እንዲደግፉህና እንዲጸልዩልህም እጠይቃለሁ»
መንግስ የጸጥታ ሃይሎች ለየትኛውም ዓይነት ትንኮሳ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ማድረጉን አስታወቀ
በትግራይ 5.2 ሚሊዮን ሕዝብ ዕርዳታ እየደረሰ ነው፤ ከሺህ በላይ የጭነት መኪኖች ታግተዋል፤ 76 ቢሊዮን ብር ወደ ትግራይ ተልኳል
የደህንነት ጥናት አዲሱ ምዕራፍ - ጂኦስፓሻል ኢንተለጀንስ

Leave a Reply