Site icon ETHIO12.COM

«በጋራ መኖሪያ ቤቶች የዕጣ አወጣጥ የተጠረጠሩ ባለሙያዎችና አመራር በቁጥጥር ሥር ሆነው ምርመራ እየተደረገ ይገኛል»

ላልቆጠቡ ሰዎች የቤት እጣ መውጣትን ጨምሮ የተለያዩ የተዓማኒነት ጉድለቶች በመገኘቱ ጉዳዩን እያጣራ መሆኑን አስተዳደሩ አስታወቀ


ሀምሌ 01 ቀን 2014 የወጣው የ 20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ላይ ላልቆጠቡ ሰዎች እጣ መውጣትን ጨምሮ የተለያዩ የተዓማኒነት ጉድለቶች በመገኘቱ ጉዳዩን እያጣራ መሆኑን አስተዳደሩ አስታወቀ።

በዚህ ዙሪያ አስተዳደሩ ማምሻውን መግለጫ አውጥቷል።

አስተዳድሩ.ማምሻውን ያወጣው መረጃ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፤

ሀምሌ 01/ 2014 የወጣውን የ 20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ይመለከታል::

በከተማችን አዲስ አበባ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል አንዱ የቤት አቅርቦት እጥረት ሲሆን ይህንኑ ደረጃ በደረጃ ለማቃለል አስተዳደሩ የተለያዩ አማራጮችን ነድፎ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

የዚህ ሂደት አካል የሆነው የነባሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ያሉበትን ወስብስብ ችግር ለይቶ በመፍታት ተመዝጋቢዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ እና የቤት እጥረት ጫና ለመቀነስ የተደረገው ሰፊ ጥረት ተጠቃሽ ነው፡፡
በዚህ ሂደት በግንባታ ላይ የነበሩ 20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መካከል 25,491 ያህሉ በቅርቡ ለባለ እድለኞች የዕጣ አወጣጥ ስነ-ስርዓት መካሄዱ ይታወቃል፡፡

ይህ የቤት ማሰስተላለፍ ስራ እንደ ከዚህ በፊቱ በቆጣቢወች መካከል አድሎና ብልሹ አሰራር እንዳይኖር ለማድረግ ግልፅነት በሚያሰፍን አግባብ ለማስተላለፍ ሲባል በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስራ በመስራት ሂደቱን ግልጽና አሳታፊ ለማድረግ የተደረገው ተነሳሽነትና ጥረት እንዲሁም የባልሙያዎችን ሙያዊ ነፃነት አክብረን አስፈላጊውን ሂደት ተከትለን ተዓማኒነቱን እንዲያረጋግጡልን አድርገን ነበር:: በዚህ ሂደት በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ አዲስ ሶፍትዌር እንዲበለፅግ እና ስለሶፍትዌሩ ታአማኒነት የኢኖቬንና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር እንዲያረጋግጥልንም ተደርጓል::

በቀጣይም ከሁለት ጊዜ በላይ ታዛቢወች እና ባለሙያወች ፊት ቀርቦ እንዲያረጋግጡልን ተደርጎ ማረጋገጫ ሰጥተዋል::
ይህ ሁሉ ሂደት ከእለት ጉርሱ የቆጠበዉን እና በከፍተኛ ጉጉት የሚጠባበቀውን ሕዝብ በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ ቀና ሃሳብ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል::

ይሁን እንጂ ከዕጣ አወጣጥ ስነ-ስርዓት በኋላ የተለያዩ ጥቆማዎች በመቅረባቸው የኦዲት ሥራ ስንጀምር በባንክ የተላከውና ለእጣ እንዲውል ወደ ኮምፒዩተር የተጫነው ዳታ ልዩነቶች ተግኝተዋል::

በመሆኑም በእስካሁኑ የማጠራት ስራ ላልቆጠቡ ሰዎች እጣ መውጣትን ጨምሮ የተለያዩ የተዓማኒነት ጉድለቶች ታይተዋል፡፡

ከዚህ በመነሳትም የቤት ማስተላለፉን ሂደት ግልፅነት ለማስፈን ሲባል እና ውጤቱን የሚያዛባ ተግባር ሲያጋጥም መልሰን ኦዲት እንዲደረግ በገባነው ቃል መሰረት የተፈጠረውን ችግር ከጉዳዩ ገለልተኛ በሆኑ በሚመለከታቸው ተቋማት የማጣራት ስራ በመከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን በጉዳዩ የተጠረጠሩ ባለሙያዎች እና አመራር በቁጥጥር ሥር ሆነው ምርመራ እየተደረገ ይገኛል::

ስለሆነም ሂደቱን በአጭር ጊዜ አጠናቀን ለቤት ተመዝጋቢዎችና ለመላው የከተማችን ነዋሪ የምናሳውቅ መሆኑን ስንገለጽ ተመዝጋቢዎች እንደተለመደው በከፍተኛ ትዕግስት እንድትጠባበቁ እናሳውቃለን፡፡

ለተፈጠረው ስህተት የከተማ አስተዳደሩ በዚህ አጋጣሚ ይቅርታ ይጠይቃል።

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር
ሐምሌ 4/2014 ዓ/ም

Exit mobile version