Site icon ETHIO12.COM

“ሳይንሳዊ ትንታኔዎችን የተከተለ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ለመቀበል የገንዘብ ሚኒስቴር ዝግጁ ነው”

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ትኩረቱን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ በማተኮር 19ኛውን አለም አቀፍ ኮንፈረንሱን እያካሄደ ነው።

ሳይንሳዊ ትንታኔዎችን የተከተለ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ለመቀበል የገንዘብ ሚኒስቴር ዝግጁ ነው ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በዚህ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር አስታውቀዋል።

የልማት ግቦችን ለማሳካት የእዳ ጫናዎችን ለመቀነስ የብድር ሽግሽግ በማድረግ እየተሰራ ነው። ይህም የፊሲካል አቅም ያሳድጋል ብለዋል ሚኒስትሩ።

አቶ አህመድ እንደተናገሩትም፤ እንደ አገር ድርቅ፣ ኮሮና፣ ጦርነት፣ የሩሲያና ዩክሬን ግጭት በኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ጫና አሳድሯል። ይህን ጫና ለመቅረፍ የሚያስችል ማስረጃና መረጃ ላይ የተመሰረቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎች ያስፈልጋሉ።

ማህበሩ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችሉ የፖሊሲ ግብአቶችን የሚያቀርብ ከሆነ የገንዘብ ሚኒስቴር ለመቀበል ዝግጁ ነው፤ ድጋፍም ያደጋል ነው ያሉት ሚንስትሩ።

የብሄራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ በበኩላቸው የፋይናንስ ዘርፍ ለአገር ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢንቨስትመንት፣ የግብርና፣ የአምራች ዘርፉ፣ በሚገባ እንዲያመርት ማድረግ ያስፈልጋል፤ ለዚህ ደግሞ የባንኮች ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ለማ ጉዲሳ፣ ማህበሩ ለኢኮኖሚ ፖሊሲ መሻሻል አስፈላጊና በጥናት የተመሰረቱ ግብአቶችን እያቀረበ ነው ብለዋል።

ማህበሩ ትኩረቱን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ በማተኮር 19ኛውን አለም አቀፍ ኮንፈረንሱን በግብርናው ኢንዱስትሪ የስራ እድል ፈጠራ፣ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን በኢትዮጵያ፣ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፉን ማሳደግ፣ የግሉ ዘርፍ እድገት በኢትዮጵያና ተጽእኖን የተመለከቱና የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሻሻል ያሉ እድሎችና ማነቆዎች የሚዳስሱ ጥናቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተገልጿል።

በኮንፈረንሱ የማህበሩ አባላትና የዘርፉ ምሁራን ታድመዋል።

በሞገስ ተስፋ – (ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version