Site icon ETHIO12.COM

ኢትዮጵያ “ቁማሩ ይቁም” ስትል አሳሰበች፤ “የትህነግ ጉዳይ ሰለቸን”ዜጎች

ምዕራባውያን መልዕክተኞችና ዲፕሎማቶች መቀለ ደርሰው እንደተመለሱ ያወጡትን መግለጫ ተከትሎ ኢትዮጵያ “ቁማሩ ይቁም” ስትል የሰላም ንግግሩ ቅድሚያ እንዲሰጠው ማሳሰቧ ተሰማ። ትህነግ እርዳታ እያለ ወደ ግጭት ለማምራት ከሞከረ ግን መንግስት ከዚህ ቀደም ባልታየ መልኩ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል። ትህነግ በሚፈጥረው ሴራ መማረራቸውን የሚገልጹ ” አንድ ውሳኔ ላይ ይደረስ” ሲሉም እየተደመጡ ነው። እነዚህ ክፍሎች ምን አልባትም በይፋ እንቅስቃሴ ሊጀመሩ እንደሚችሉ ተሰምቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም እጁ የተዘረጋ መሆኑንና በተግባርም ለሰላም ሲል በርካታ ውሳኔዎችን አሳልፎ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑንን አስታውቆ ማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያ መስጠቱን የመረጃ ምንጮች ለኢትዮ12 ተናግረዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን በቲውተር ገጻቸው ቆንጥረው እንዳሰፈሩት ሳይሆን መንግስት የከረረ ማሳሰቢያ መስጠቱ ነው የተመለከተው።

የተቋረጠ አገልግሎት እንዲጀመር ወስኖ መስራትና ይህንን ማስተጋባት ከቶውንም አግባብ እንዳልሆነ ጠቅሳ ለአውሮፓና አሜሪካ ያስታወቀችው ኢትዮጵያ፣ “እየተወጋች፣ እየደማች፣ ሴራ እየተፈለፈለባትና ሽብር ስፖንሰር እየተደረገባት ይህንን ሁሉ ለሚያደርግ ድርጅት ቀለብ፣ ትራንስፖርትና፣ መድሃኔት የምትሰፍር ብቸኛዋ የዓለም አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት” ብላለች። የመረጃ ምንጮቹ እንዳሉት ” መንግስት ይህን ሁሉ የሚያደርገው ለትግራይ ህዝብ ብሎ ቢሆንም ትህነግ ህዝብን በጋሻነት ይዞ ቁማር እንዲጫወት መፍቀድ አግባብ አይደለም” ሲል “ቁማር” ያለውን ዘርዝሮ አቅርቧል።

የአሜሪካና የአውሮፓ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኞች እንዲሁም በኢትዮጵያ የካናዳና የጣሊያን አምባሳደሮችን ያካተተ ልዑክ ወደ ትግራይ መዲና መቀለ አምርተው ከትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር አመራሮች ጋር መነጋገራቸው ይታወሳል። ከጉዞ መልስ ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ ችግሩን ለመፍታት የፖለቲካ ውይይት እንደሚያስፈልግ፣ በነዳጅ፣ በጥሬ ገንዘብና በማዳበሪያ ላይ ተጥሎ ያለው ክልከላ መነሳትእንዳለበት፣ በክልሉ ተቋርጠው የሚገኙ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ዳግም እንዲጀመሩ ለባለሙያዎች ደኅንነት የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ለፌደራል ማድረሳቸውን አስታወው ነበር።

መንግስት እንደሚለው ትህነግ የአገር መከላከያ ሰራዊትን አርዶ፣ መሰረተ ልማት አውድሞና ባለሙያዎችን ገሎ ያቋረጠውን አገልግሎት ለማስጀመር ዕቅድ ቢኖርም ቅድሚያ የሰላም ንግግር መደረግ አለበት። ከአንዳንድ ገለለተኛ ወገኖች እንደሚሰማው ትህነግ በሰላም ንግግሩ እንደማያተርፍ ስለሚረዳ የተቋረጡ አገልግሎቶች ቀድመው እንዲጀመሩ ይወተውታል። ሲያብራሩም በድርድር መርህ መቀበል የሚኖረው መስጠት ካለ ብቻ በመሆኑ ዛሬ ላይ ትህነግ አንዳችም የሚሰጠው ነገር የለውም። ወደ ድርድር ሲመጣ ባዶ እጁን በመሆኑ ተሸናፊ ነው። ይህ ደግሞ የድርድር መርህ ነው።

እነዚህ ክፍሎች ሌላው የሚያነሱት የወልቃይት ጉዳይን ነው። ወልቃይትን በሃይል እንደሚያስመልስ ትህነግ ደጋግሞ ለደጋፊዎቹና ለወዳጆቹ እያስታወቀ ሁለት ዓመት ቢቆይም በተግባር የሆነ ነገር የለም። በተደጋጋሚ ተሞክሮ አለመሳካቱን የአካባቢው ነዋሪዎችና የአማራ ክልል ይፋ አድርገዋል። መንግስትም ሰፊ ቁጥር ያለው ሜካናይዝድ ሃይል በአካባቢው አስፍሮ እየጠበቀ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በወልቃይት ጠገዴ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት እጅግ ዘግናኝ ግፍ መፈጸሙን የሚይረጋግጡ መረጃዎች መገኘታቸው የትህነግን አመርሮችና ካድሬዎች በዓለም ዓቀፍ ህግ መሰረት ለመጠየቅ ዝግጅቱ መጠናቀቁ ትህነግ ወልቃይትን እንዲረሳ ሳያደርገው እንደማይቀርም እየተነገረ ነው። ነጮቹም ይህንኑ ተረድተዋል የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ነው። ይህ ሁሉ ሆኖ የሱዳን ትህነግ ላይ ፊት ማዞርም ሌላው ምክንያት እንደሆነም እየተገለጸ ነው። የአማራ ክልልም ውስጡን እያጠራ ከቀድሞው ጋር ሲነጻጸር እጅግ ሰፊ የሚባል ሃይል መገንባቱም ይጠቀሳል።

ከላይ የተጠቀሱ ጥቂት ማሳያዎች እንዳሉ ሆነው አቶ ጌታቸው ረዳ ሰሞኑንን “የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ በጥንቃቄ ካልተያዘ ኢትዮጵያ ልትበታተን ትችላለች” ሲሉ ተደምጠዋል። ይህን ሲሉ ወልቃይት ወደ ትግራይ ካልተካተተች ኢትዮጵያ ትበታተናለች ለማለት ፈልገው ስለመሆኑ ግን አልብራሩም። ይህን ንግግራቸውን የሰሙ ” ትህነግ ኢትዮጵያን ሊበትን የሚችልበት አቅም ላሽቋል። አገሪቱ ባዶ በነበረችበት ወቅት ያልተሳካ ዕቅድ ዛሬ የክልል ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ሳይጨምር ሁለት ሚሊዮን ጦር ተገንብቷል” ሲሉ ሃሳቡን “ቅዠት” ይሉታል።

በውጭ አገር ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ጋር በዙም በተደረገ ውይይት ስለመገንጠል ተነስቶ “We will cross the bridge when we come to it” የሚል ምላሽ የሰጡት አቶ ጌታቸው “ወልቃይት ጠገዴን መልሰን እጃችን ውስጥ ካስገባን በኋላ ስለ ነፃ ሃገረ ትግራይ እናወራለን” ማለታቸው ወልቃይት ወደ ትግራይ እስካልገባች ትግራይ ያው ትግራይ ሆና እንደምትቀጥል አመላካች ሆኗል።

አቶ ሬድዋን አለሳልሰው ያቀረቡት ቅሬታ ላይ መንግስት ትህነግ ትንኮሳ ከጀመረ ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወስድ በግልጽ ማስገንዘቡና ማስተንቀቁ፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ ዜጎችን መውረርና ንብረታቸውን መዝረፍ ከቶውንም እንደማይታሰብ፣ መንግስት ሰላማዊ ዜጎችን ለመጠበቅ ሲል ማናቸውንም እርምጃዎች በትህነግ ላይ ሊወስድ እንደሚችል ለዚህም ሙሉ ዝግጅት አድርጎ በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኝ ይፋ ማድረጉን ዜናውን የገለጹልን አስረድተዋል። ይህንን በመረዳት ይህ የሽብር ቡድን ወደ ሰላም እንዲመጣና አገሪቱ ውስጥ ህግ በሚፈቅድለት አግባብ ለክ እንደሌሎች ክልሎች ድርሻውን እየወሰደ እንዲኖር ጫና እንዲደረግበትም ጥያቄ ቀርቧል።

ይህ በንዲህ እያለ በአዲስ አበባ ” የትህነግ ጉዳይ እልባት ይሰጠው” የሚሉ ወገኖች መበራከታቸው ተሰምቷል። መለያየትም ከሆነ ልክ ኤርትራ ስትገነጠል እንደሆነው ሳይሆን በጥብቅ ውሳኔ መለያየት እንደሚሻል የሚናገሩ በቅርቡ መንግስትን ለመጠየቅ መዘጋጀታቸው ታውቋል።

ለአዲስ አበባ ዘጋቢያችን መረጃውን የሰጡ እንዳሉት የአዲስ አበባ ሕዝብ ሰላም ይፈልጋል። “የትግራይ ህዝብ ፍልጎት መገንጠል ከሆነ መንግስት ሊያመቻችላቸው ይገባል” ብለዋል። የትግራይ ህዝብም ሰላም እንደሚያስፈልገው ያመለከቱት ክፍሎች፣ ጥያቄው የህዝብ ከሆነ መደባበቅና ሁለት ቦታ መጫወቱ ጊዜው ያለፈበት በመሆኑ አንዱን መርጦ መገላገል እንደሚሻል አመልክተዋል።

” የሚናህን ለይ” እንቅስቃቅሴ አካል መሆናቸውን የሚናገሩት ወገኖች “ዛሬ ሁሉም የአገሩ ሰላይ ነው። ነገሮች እንደ 1983 አይደሉም” ካሉ በሁዋላ ” አብሮ መኖርና በመተማመን መዝለቅ ካልተቻለ አንዱ ለአንዱ ጠላት ሆኖ መቀጠል አይቻልም። የትግራይ ሕዝብ ፍላጎቱ ሊፈጸምለት ይገባል። መንግስትም ይህንን መግፋት አለበት። በንግግሩ ላይ ቅድሚያ የትግራይ ህዝብ ውሳኔ እንዲቀድም ኢትዮጵያዊያን ግፊት ልናደርግ ይገባል” ብለዋል። ይህን አቋማቸውን በህዝብ ለማስደገፍ በይፋ መንቀሳቀስ እንደሚጀምሩም አመልክተዋል።

የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ትህነግ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ” ታላቂቷን ትግራይ እገነባለሁ” እያለ ቢቆይም ተግባራዊ አላደረገውም የሚሉትን የነጻ አገርነት ጉዳይ በአሜሪካን የህወሓት ተወካይ ሆኖ የሚሰሩት ፍስሃ አስገዶም በቅርቡ በሰጡት የትግርኛ ቃለመጠይቅ ላይ “ነጮቹ “ሪፈረንደም ማድረግ ከፈለጋችሁ በመጀመሪያ ‘ኢትዮጵያ ትረጋጋ’ ይሉናል።እኛም ይህን ሃሳብ አንቃወመውም። እኛ ወደ ፍቺ የምንሄድ ከሆነ ኢትዮጵያ በተረጋጋችበት ሰዓት ብንፋታ ነው የሚሻለው።መታወቅ ያለበት ነገር ግን ጄኖሳይድ ከፈፀመብህ አካል ጋር አብሮ መቀጠል አይቻልም።በአለም ታሪክ እንዲህ ሆኖ አያውቅም።ወይ እሱ ማሸነፍ አለበት ወይ አንተ አሸንፈህ መውጣት አለብህ።እሱ አሸናፊ ከሆነ ልክ እንደ አርመናውያንና እንደ ኩርዶች ያጠፋሃል።አንተ አሸናፊ ከሆንክ ደግሞ ልክ እንደእስራኤል አገር ትመሰርታለህ።እኛ ከድርድሩ በፊት ካስቀመጥናቸው ቅደመ ሁኔታዎች መካከል ሪፈረንደም ወሳኙ ነጥብ ነው።ሪፈረንደም ስንል ‘ህዝበ ውሳኔ’ ማለታችን እንደሆነ ማስረዳት አለብን።ተገንጥለን አገር ስለመሆን ማውራት የለብንም።ነጮቹም ቢሆኑ ይሄንን አይወዱልንም።” ፍላጎታችሁ ለመገንጠል ነበር እንዴ ወደ ድርድሩ የመጣችሁት?” ሊሉን ይችላሉ።ተደራዳሪዎቻችንም ቢሆን በዚህ ድምዳሜ ወደ ድርድሩ ከመጡ ውጤቱ ጥሩ አይመጣም” ማለታቸውን የአስፋው አብርሃ ትርጉም ያስረዳል።

ለዚህ ይመስላል በአዲስ አበባ የተጀመረው እንቅስቃሴ “ወደማይቀረው ውሳኔ እናምራ። እኛም እናግዛቸውና አብረን እንረፍ” የሚሉት። ይህ እንቅስቃሴ መቼና እንዴት ይፋ እንደሚሆን በቀጣይ ጠይቀን ለማሳወቅ እንሞክራለን።

Exit mobile version