ETHIO12.COM

ሀገር ጠል [ የትህነግ ታጣቂዎች] ከአልሸባብ ሃይሎች ጋር ተይዘዋል

የተለያዬ ሀገር ዜግነት ያላቸው ግለሠቦች የአልሸባብን የሽብር ቡድን ሲያሠለጥኑ መቆየታቸውንና “ሀገር ጠል” የተባሉ [የትህነግ አባላት] ኢትዮጵያዊያኖች ከሽብር ቡድኑ አባላት አብረው መገኘታቸውን የኮማንድ ፖስቱ አስተባባሪ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው በይፋ ተናገሩ።

ይህ የተገለጸው የአልሸባብ ኃይል ያሠበው የሽብር ሴራ በመከላከያ ሰራዊትና በሱማሌ ክልል ልዩ ሃይል አባላት መክሸፉን አስመልክቶ መኮንኑ ለመከላከያ ሰራዊት መገናኛ ገለጻ በሰጡበት ወቅት ነው። በመግለጫቸው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ነኝ የሚለውን ትህነግ በስም ባይገልጹትንም ” አገር ጠል” ሲሉ ፈርጀዋቸው መያዛቸውን አመልክተዋል።

በመከላከያ ህብረት ዘመቻ ዋና መምሪያ የኃይል ሥምሪት መምሪያ ኃላፊ እና የቀጠናው ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው እንዳሉት በሶስት አቅጣጫ የሽብር ተግባር ለመፈፀም አስቦ የተንቀሳቀሰው አልሸባብ በመከላከያ ሠራዊታችን እና በሱማሌ ልዩ ሃይል ተደምስሷል። በርካታ ቁጥር ያለው ኃይልም ተማርኳል፡፡

የሽብር ቡድኑ ኤልከሬ በተባለው ቦታ ቀደም ብሎ ቀብሮት የነበረውን ትጥቅ እና ስንቅ በህብረተሠቡ ጥቆማ በፀጥታ ኃይላችን ተይዟል፡፡ ሠርጎ ለመግባት የሞከረውን የአልሸባብ ኃይል ከኋላ በመቁረጥ በየትኛውም አቅጣጫ መውጣት እንዳይችል አድርጎ የደመሰሰው የፀጥታ ኃይላችን አሁን ላይ ቀጠናውን በማፅዳት እና የተንጠባጠበውን አሸባሪ እየለቀመ መሆኑንም ጀኔራል መኮነኑ ተናግረዋል፡፡

በጠረፍ አካባቢ ለወራት ሠው ሲያሠባስብ እና ሲያሠለጥን የቆየው አሸባሪው ኃይል ኢትዮጵያዊያን የውስጥ ችግር አለባቸው በሚል የተሳሳተ አመለካከት ሰርጎ ለመግባት መሞከሩን እና ከቻለ ከሸኔ ሃይል ጋር በመገናኘት ጥምረት ፈጥሮ ቀጠናውን ሠላም ለማሳጣት አስቦ መንቀሳቀሱን ሜጄር ጄኔራል ተስፋዬ ገልፀዋል፡፡

የተለያዬ ሀገር ዜግነት ያላቸው ግለሠቦች የሽብር ቡድኑን ሲያሠለጥኑ መቆየታቸውን እና ሀገር ጠል የሆኑ ኢትዮጵያዊያኖች ከሽብር ቡድኑ አባላት ጋር መገኘታቸውንም የኮማንድ ፖስቱ አስተባባሪ ተናግረዋል፡፡

ከፍተኛ ሀገራዊ ስሜት በተንፀባረቀበት እና ፍፁም የበላይነት በታየበት ድል የፀጥታ ሃይሎቻችን ሳይኩራሩ ባለመዘናጋት እና ክፍተት ባለመፍጠር ጥንቃቄ በተሞላበት አግባብ ሁሌም ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው ሜጄር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው አሳስበዋል፡፡

በተያያዘ ኢትዮጵያን በጦርነት የማተራመስ ተልዕኮ ተሠጥቷቸው ለሽብር ተግባር የተሠማሩ መሆናቸውን የተማረኩ የአልሸባብ አባላት ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ በሶስት አቅጣጫ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ሰርጎ በመግባት ሽብር ለመፈፀም ካሠበው የአልሸባብ ሃይል መካከል አብዛኛው ተደምስሷል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሃይልም በመከላከያ ሠራዊታችን እና በሱማሌ ክልል ልዩ ሃይል ተማርኳል፡፡

ይህ የሽብር ኃይል ያቀደው እንደምንም እየተዋጋ አልፎ ከኦነግ ሸኔ ጋር በመገናኘት እና የሽብር አድማሱን በማስፋት ኢትዮጵያ ውስጥ የሠላም እጦት እንዲፈጥር ተልዕኮ ተሠጥቶት የነበረ ሃይል ነው፡፡

የአልሸባብ አመራሮች በኢትዮጵያ ላይ በተለያዬ አቅጣጫ ዘመቻ ከፍተን የግዛት አድማሳችንን እናሠፋለን ኢትዮጵያዊያን በውስጥ ችግር ፈተና ውስጥ ስላሉ የሚመክተን ሃይል የለም በሚል የተሳሳተ ፕሮፖጋንዳ ወደ ጦርነት ያስገቧቸው መሆኑንም ምርኮኞቹ ተናግረዋል፡፡

አልሸባብ የሶማሊያን ህዝብ እየዘረፈ እና አስገድዶ እየቀማ የሚኖር ሃይል መሆኑን የጠቆሙት ምርኮኞቹ በተለያዬ ስራ የተሠማሩ ሠዎችን እያሠገደደ እና እያታለለ ወደ ጫካ በመውሠድ የሽብር ቡድኑ አባል እንዳደረጋቸውም ገልፀዋል፡፡

የተለያዬ ሀገር ዜግነት ባላቸው አሰልጣኞች የጥፋት መሠረታዊ አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ስልጠና መውሠዳቸውን እና በአመራሮቻቸው ትዕዛዝ ለውጊያ ወደ ኢትዮጵያ ደንበር መሠማራታቸውን እና ሲዋጉም በኢትዮጵያ የፀጥታ ሃይል መማረካቸውን ገልፀዋል፡፡

ይህ አለም አቀፍ አሸባሪ ቡድን ለጥፋት ሊጠቀምባቸው የነበሩ ፈንጅዎች እና የተለያዩ ወታደራዊ ቁሶችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የመከላከያ ፌስ ቡክ ላይ የቀረበው ዜና ያስረዳል።

Exit mobile version