Site icon ETHIO12.COM

መከላከያ ያለበቂ መረጃ የጠላትን አሳብ ለሚይራቡ ሚዲያዎች ማስጠንቀቂያ ሰጠ


ጠላት ባሰናዳው ፕሮፖጋንዳ ወጥመድ የተጠለፉ አሉታዊ መረጃዎች በማስተጋባት እና በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች የሰራዊታችንን እንቅስቃሴ በማሰራጨት ኃላፊነት የጎደላቸው አካላት እንዳሉም አይተናል፡፡ ይህ ድርጊት በሰራዊታችን የግዳጅ አፈፃፀም ላይ ምንም አወንታዊ ተፅኖ ሊኖረው አይችልም

የሰራዊቱን ምስጢር በመንዛት፣ የጠላትን አጀንዳ በማራገብ የሃገር ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉትን እንደ አስፈላጊነቱ የወንጀል ክስ በመመስረት ተጠያቂ ለማድረግ እንደምንገደድ በጥብቅ እናሳውቃለን

ከኢፌዴሪመከለከያህዝብግንኙነትየተሰጠመግለጫ.

የሠራዊታችንን ወቅታዊ ሁኔታ፣ ባልተረጋገጡ፣ ባልተገቡ መረጃዎችና አሉባልታዎች የመዘገብ ወይም የማራገብ አሉታዊ ሙከራዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ በጥብቅ ስለ ማሳሰብ የተሰጠ መግለጫ።

የህዝባችን ድጋፍ እና ተሳትፎ ጠንካራ መሆን፤ መከላከያ ሰራዊት የሀገር ሉዓላዊነትን ለመጠበቅ የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት ወሳኝ መሆኑን በፅናት ያምናል፡፡ በህዝባችን እና በሰራዊታችን የተገነባው መተማመንና መደጋገፍ በፅኑ መሰረት ላይ የቆመ በመሆኑ፣ ፈተናዎች በጋራ እያለፍን የሃገራችንን አንድነትና ሉዓላዊነት አስከብረን ቆይተናል፡፡ ወደፊትም ጠላቶቻችን የሚደግሱልንን ሴራ እና ወጥመድ አውቀን በማክሸፍ ለዕኩይ ዓላማቸው የማንበገር መሆናችንን በተግባር እያሳየን እንቀጥላለን፡፡ ይህ የጋራ ታሪካችንና ተስፋችን አይቀሬ ቢሆንም ለድላችን የምንከፍለው ዋጋ እንዲቀንስ ግን ጠንካራ ስራ ያስፈልገናል፡፡

ጠላቶቻችን ከሰሞኑ ግልፅ አደጋ ለመፍጠር አስበው በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ሰርጎ የገባው አልሸባብ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኃይሉ መደምሰሱ ይታወቃል፡፡ በሰሜኑ የሃገራችን ክፍልም አሸባሪው የህወሃት ቡድን የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ይገኛል፡፡ በተለይ የአሸባሪው ህወሓት አፈ ቀላጤዎች ሰሞነኛ ሰበካቸው የሰራዊታችን ስም ማጥፋት ስራዬ ብለው ተያይዘውተዋል፡፡ ተቀባይነት የሌላቸውን ሰበቦች በመደርደር መከላከያ ሰራዊታችንን በመወንጀል ዘመቻ መሰማራታቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡

ለዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጭምር እየለፈፉ ያሉት፤ “…የሰላም ድርድሩ ቴክኒካል ፈርሷል…፣ …መከላከያ ኃይሉን እያስጠጋ ነው…፣ …መከላከያ በከባድ መሳሪያ እየደበደበን ነው…፣ …ከላይ እስከታች የዕዝ ሰንሰለቱን ጠብቆ እየተፈፀመ ያለ ጥቃት ነው…” ወዘተ በማለት የቅድመ ግጭት ጩኸታቸውን በስሙልኝ ፕሮፖጋንዳቸው እያስተጋቡት ይገኛሉ፡፡

የሃገራችን ሚዲያዎች፣ የጠላትን ሴራ እና አጀንዳ በውል ተገንዝበው የሚሞግቱ የመኖራቸውን ያህል፣ አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ዘገባዎችና መረጃዎች ይህንኑ አፍራሽ ውንጀላ ባልተገባም መልኩ እየተቀባበሉት መሆኑን አስተውለናል፡፡

ያለበቂ መረጃ የጠላትን እንቅስቃሴ መዘገብ በራሱ የህዝባችንን የዕለት ከዕለት ኑሮ ያውካል። ጠላት በዚህ ገባ፣ በዚህ ወጣ ፤ የወገን ሠራዊት በዚህ ገባ፣ በዚህ ወጣ የሚለው ወሬ በፍፁም ዜና እና የዜና ትንታኔ ሊሆን አይችልም። ጦርነቱን እንዲዘግቡ ፍቃድ ከተሰጣቸው ውጭ በሀገር ህልውና ላይ የተቃጣን ጦርነት የሚያክል ነገር በማህበራዊ ሚዲያ ገቢ ማስገኛነት ተቆጥሮ ምንም የተረጋገጠ መረጃ ሳይኖር ወሬውን ማናፈስ የህዝባችንን መረጋጋት የሚነሳ ጉዳይ ነው ፤ የፀጥታ ሃይሎችን ተግባርንም ያውካል።

የሠራዊታችን ወቅታዊ ሁኔታ እና እንቅስቃሴ አስፈላጊ ሁኖ ሲገኝ ለህዝባችን ይፋ ስናደርግ እንደነበረው ወደፊትም በዚሁ አግባብ የሚከናወን ተግባር ሆኖ ሳለ፤ ሰራዊታችን ማንኛውንም ጥቃት ለመመከት በፅናትና በጥንቃቄ፤ ተዘጋጅቶ በተጠንቀቅ በቆመበት በአሁኑ ወቅት ጠላት ባሰናዳው ፕሮፖጋንዳ ወጥመድ የተጠለፉ አሉታዊ መረጃዎች በማስተጋባት እና በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች የሰራዊታችንን እንቅስቃሴ በማሰራጨት ኃላፊነት የጎደላቸው አካላት እንዳሉም አይተናል፡፡ ይህ ድርጊት በሰራዊታችን የግዳጅ አፈፃፀም ላይ ምንም አወንታዊ ተፅኖ ሊኖረው አይችልም።

በመሆኑም ይህን አሉታዊ ተግባር በማወቅም ሆነ ባለማወቅም የተዛባ፣ ተገቢና የማይመለከታቸውን ዘገባ የሚዘግቡ የማህበራዊ ሚዲያ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡

ይህንን ተግባር በግዴለሽነት ወይም በማንአለብኝነት የሚቀጥሉና የማይታረሙ ካሉ መከላከያ ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድ ከመሆኑም በላይ የሰራዊቱን ምስጢር በመንዛት፣ የጠላትን አጀንዳ በማራገብ የሃገር ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉትን እንደ አስፈላጊነቱ የወንጀል ክስ በመመስረት ተጠያቂ ለማድረግ እንደምንገደድ በጥብቅ እናሳውቃለን፡፡

የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

Exit mobile version