Site icon ETHIO12.COM

ትህነግ ማንነቱን ለዓለም አጋልጧል፤ በጦር ወንጅልነት ሊጠየቅ ይገባል

“ሽብርተኝነት በምእራቡም ሆነ በተቀረው ዓለም ተቀባይነት እንደሌለው ሁሉ በኢትዮጵያም ፍጹም ቦታ የለውም!

ለትግራይ ሕዝብ ምግብ እና የግብርና ግብዓቶችን ለማከፋፈል ወደ ክልሉ በገባው ነዳጅ ዝርፊያ የፈጸመው የሽብር ቡድኑ ሕወሓት በትግራይ ሕዝብ የሚነግድ ኢሰብዓዊ ቡድን መሆኑን የሚያረጋግጥ ብቻ ሳይሆን ግልጽ የጦር ወንጀል እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ህግጋቶችን የጣሰ ድርጊት ነው ብሏል መግለጫው፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

በመቀሌ የህወሓት የሽብር ቡድን የአለም የምግብ ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ማከማቻ መጋዘን ውስጥ በነበረ 12 የነዳጅ ታንከርና ውስጡ የነበረውን 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ ላይ የተፈጸመውን ዝርፊያ መንግስት በፅኑ ያወግዛል። ዘረፋው የተፈጸመው የሽብር ቡድኑ ለዳግም ጥቃት እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት ነው።

ለትግራይ ህዝብ እጅግ አንገብጋቢ የሆኑትን የምግብና የግብርና ግብአቶች ለማከፋፈል ወደ ክልሉ በገባው ነዳጅ ላይ ዝርፊያ የፈጸመው የሽብር ቡድኑ ህወሓት በትግራይ ህዝብ የሚነግድ ኢሰብአዊ ቡድን መሆኑን በተጨባጭ የሚያረጋግጥ ብቻ ሳይሆን ግልጽ የጦር ወንጀልና ዓለምአቀፍ የሰብዓዊነት ህግጋቶችንም የጣሰ ድርጊት ነው።

ትናንት በሽብር ቡድኑ የተፈጸመው የሰብአዊ እርዳታ ዝርፊያ በዓለም የምግብ ፕሮግራምና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጉዳዮች ቢሮም ተረጋግጧል።

ለትግራይ ህዝብ የገባ የሰብዓዊ የነዳጅና የምግብ እርዳታ ላይ ህወሓት ትናንት የፈጸመው ዝርፊያ ዳግም በቆቦና አካባቢው ላይ ለከፈተው ጥቃት ማስፈጸሚያ ሊጠቀምበት እንደሆነም ታውቋል። አለም አቀፎቹ ተቋማት እንዳረጋገጡት የህወሓት የሽብር ቡድን በመቀሌ ከፈጸመው ዝርፊያ ባሻገር ድርጊቱን ለማስቆም የሞከሩ የሰብአዊ እርዳታ ባለሙያዎችንም አስሯል።

እንደሚታወቀው መንግስት ወደ ትግራይ ክልል አስፈላጊው ሰብአዊ ድጋፍ በአግባቡ እንዲደርስ ለማድረግ የተናጠል ተኩስ አቁም ከማድረግ ባሻገር ያልተቋረጠ የሰብዓዊ ድጋፍ በየብስም በአየርም እንዲቀርብ ሲያደርግ ቆይቷል።

በተጨማሪም መንግስት ባለፉት ወራት ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሄን ለመስጠት እንዲሁም መተማመንን ለመፍጠር እንዲቻል የሰብዓዊ ድጋፍና መሰረታዊ አገልግሎትን ለማስጀመር የሚያስችሉ ዝግጅቶችን ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል። ሆኖም መንግስት ለሰላም የወሰዳቸው እርምጃዎች በሙሉ በህወሓት የሽብር ቡድን በኩል ተቀባይነትን አላገኙም።

ከዚህም አልፎ ከቀናት በፊት የህወሓት የሽብር ቡድን አባልና ደጋፊው የአለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር፤ አለም አቀፉ ተቋም ለሁሉም ዜጋ በእኩል ማገልገል አለበት የሚለውን መሰረታዊ መርሁን ወደ ጎን በማለት ትግራይ ውስጥ ሰብአዊ እርዳታን ለማከፋፈል የሚውል ነዳጅ እጥረት አለ በማለት ሃሰተኛ ውንጀላ ሲያቀርብ እንደነበር ይታወቃል።

የትናንትናው የህወሓት የሽብር ቡድን ዝርፊያ ግን ቡድኑ ለሰብአዊ እርዳታ የሚገባን ነዳጅና የምግብ ድጋፍ ለጦርነት ዓላማ ሲዘርፍና ሲጠቀም የመቆየቱን ሃቅ ለመላው አለም በግልጽ ያሳየ ነው።

ከጦርነቱ ጅማሮ አንስቶ ይህንኑ የህወሓት የሽብር ቡድን እርዳታን ለወታደራዊ አላማ የመጠቀም ወንጀል መንግስት ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በተደጋጋሚ ሲያሳስብና ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል። መንግስት ሲገልጽ የቆየውንና የህወሃትን ሰብአዊ እርዳታን ለጦርነት የማዋል ወንጀል ገለልተኛ አለም አቀፍ ምርመራዎችም በተጨባጭ ያረጋገጡት ሃቅ ነው።

ሆኖም መላው ኢትዮጵያውያንን ባሳዘነ መልኩ ይህ የመንግስት ማሳሰቢያ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ሰሚ ሳያገኝ፤ ተገቢ የሆነ የተጠያቂነት እርምጃም በሽብር ቡድኑ ላይ ሳይወሰድ ቆይቷል።

ትናንት በሽብር ቡድኑ የተፈጸመው ለትግራይ ህዝብ የገባ የሰብአዊ እርዳታ ዝርፊያ ለመላው አለም ግልፅ በሆነ መልኩ የቡድኑን ማንነት ያሳየ ይሁን እንጂ ከሽብር ቡድኑ ታሪክ መረዳት እንደሚቻለው ህወሓት ከ1970ዎቹ ጊዜ ጀምሮ ለትግራይ ህዝብ ተብሎ የሚገባን ሰብአዊ እርዳታን መዝረፍ የለመደ ከሰብአዊነት ያፈነገጠ ወንጀለኛ ቡድን ነው።

ስለዚህ መንግስት

1) የተዘረፈው ነዳጅ እንዲመለስ

2) የሰብአዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች የቀረበላቸውን ማስረጃ ከግምት በማስገባት በሽብር ቡድኑ ላይ ግልጽ የሆነ ተጠያቂነትን እንዲያሰፍኑ

3) አለምአቀፉ ማህበረሰብ የህወሃት የሽብር ቡድን በፈጸማቸው ወንጀሎች ተጠያቂ እንዲያደርግ እንዲሁም ወደ ትግራይ የሚገባው ሰብአዊ እርዳታ ለታለመለት አላማ መዋሉንና ለትግራይ ህዝብ እየደረሰ መሆኑን ማስተማመኛ እንዲሰጥ ይጠይቃል።

መንግስት አሁንም ለሰላማዊ አማራጭ በሩ ክፍት መሆኑንና የህወሓት የሽብር ቡድንም ዳግም እየፈጸመ የሚገኘውን ጥቃት አቁሞ ወደ ሰላማዊ ምክክር እንዲመጣ ያሳስባል።

ሆኖም ህወሓት ይህንን የመንግስትን የሰላም ጥሪ የማይቀበል ከሆነ መንግስት ሃገራዊ ሉአላዊነትንና የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ ይወስዳል።

ሽብርተኝነት በምእራቡም ሆነ በተቀረው አለም ተቀባይነት እንደሌለው ሁሉ በኢትዮጵያም ፍጹም ቦታ የለውም!

ነሃሴ 19 ቀን 2014

አዲስ አበባ

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

Exit mobile version