Site icon ETHIO12.COM

የተመድ መርማሪ የሥራ ጊዜው ተራዘመ፤ አፍሪካ አገራት ሙሉ በሙሉ ድምጽ ነስተውታል

ሚዛናዊነት እንደሚጎድለው በማስረጃ በመጥቀስ ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው ያስታወቀችው የመርማሪዎች ቡድን ዕድሜው እንዲራዘም ተጠይቆ ነበር።አርባ ሰባት አባላት ካሉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት አባላት መካከል የመርማሪ ቡድኑን እድሜ እንዲራዘም ሃያ አንዱ አገራት ሲደግፉት አስራዘጠኙ ተቃውመውታል። የምክር ቤቱ አባል የሆኑ ሁሉም የአፍሪካ አገራት ውሳኔውን መቃወማቸው በኢትዮጵያ በኩል “ታሪካዊ” ተብሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ” ፍጹም ገለልተኛ አይደለም፣ የፖለቲካ አቋም አለው” በማለት በይፋ ያወገዘችውና እንደማትቀበለው ያስታወቀችው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ ኮሚሽን የሥራ ጊዜ የተራዘመው ለአንድ ዓመት እንደሆነ ታውቋል።

አርብ መስከረም 27/2015 ዓ.ም. ጄኔቫ ውስጥ የመንግሥታቱ ድርጅት ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ምክር ቤት አባላት ውሳኔውን በተመለከተ በሰጡት ድምጽ መርማሪ ቡድኑ ሥራውን እንዲቀጥል መወሰኑንን ቢቢሲ ነው በግንባር ዜናው ያስታወቀው።

ኢትዮጵያ መርማሪ ኮሚሽኑ ሲመሰረት ጀምሮ ተቃውሞዋን ስታሰማ የቆየች ሲሆን፣ ሦስት አባላት ያሉት ቡድን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ ያደረገውን ምርመራ የመጀመሪያ ሪፖርት ካቀረበ በኋላም የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃውሞውን አሰምቷል።

የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ ኮሚሽኑ ሥራውን እንዲቀጥል የተጠየቀበት የውሳኔ ሐሳብ የቀረበው የአፍሪካ ኅብረትን በመወከል በቼክ ሪፐብሊክ በኩል ሲሆን በተሰጠው ድምጽ በጠባብ ልዩነት ተቀባይነት አግኝቷል።

አርባ ሰባት አባላት ካሉት የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት አባላት መካከል የመርማሪ ቡድኑን ሥራ መቀጠል 21ዱ ሲደግፉት 19ኙ ተቃውመውታል። የምክር ቤቱ አባል የሆኑ ሁሉም የአፍሪካ አገራት ውሳኔውን ተቃውመውታል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ይህንኑ አስመልክተው በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት “ፖለቲካዊ ሚና ያለው “የባለሙያዎች” ኮሚሽን ሥራውን እንዲቀጥል አንድም የአፍሪካ አገር ድጋፉን አልሰጠም” በማለት ቡድኑን ተችተዋል።

Exit mobile version