Site icon ETHIO12.COM

ለጎረቤት ሀገራት ከ13 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚገመት የኤሌክትሪክ ሽያጭ ተከናውኗል

በተያዘው በጀት ዓመት ሁለት ወራት ለሱዳንና ለጅቡቲ ኤክስፖርት ከተደረገ የኤሌክትሪክ ኃይል ከ13 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ሽያጭ መከናወኑን በማርኬቲንግና ቢዝነስ ዲቨሎፕመንት መምሪያ የሽያጭና ደንበኞች አስተዳደር ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ገለጹ፡፡

ሥራ አስኪያጁ አቶ ምኒሊክ ጌታሁን እንደገለጹት ባለፉት ሁለት ወራት ለሱዳን እና ለጅቡቲ ከ349 ነጥብ 56 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ከ18 ነጥብ 55 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ሽያጭ ለማከናወን ታቅዶ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በሁለቱ ወራት 232 ነጥብ 76 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የ13 ነጥብ 04 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሽያጭ በማከናወን የዕቅዱን 70 ነጥብ 29 በመቶ ብቻ ነው ማሳካት የተቻለው፡፡

በሁለቱ ወራት ለሱዳን 112 ነጥብ 36 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት ኃይል በማቅረብ የ5 ነጥብ 61 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ለጅቡቲ 120 ነጥብ 39 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የ7 ነጥብ 42 ሚሊዮን ዶላር ሽያጭ ተከናውኗል፡፡

ለጅቡቲ ለማቅረብ በዕቅድ ከተያዘው ኃይል የ12 ነጥብ 29 በመቶ ብልጫ ያለው ኃይል የቀረበ ሲሆን ለሱዳን ደግሞ የዕቅዱን 46 ነጥብ 36 በመቶ ብቻ መሸጥ እንደተቻለ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

የተከናወነው ሽያጭ ከዕቅዱ አንጻር ሲታይ የ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወይም የ29 ነጥብ 71 ቅናሽ ያለዉ ሲሆን የተሸጠው ኃይል ደግሞ ከዕቅዱ 116 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት ወይም የ33 ነጥብ 42 በመቶ ቅናሽ ያለው ነው፡፡

ምንም እንኳን ለሁለቱ ሀገራት የተከናወነው ሽያጭ በጥቅል ሲታይ ከዕቅዱ በታች ቢሆንም ከጅቡቲ የተገኘው ገቢ ግን ከዕቅዱ የ15 ነጥብ 38 በመቶ ብልጫ ያሳየ ነበር፡፡

ከሱዳን ይገኛል ተብሎ ታቅዶ የነበረውን ሽያጭ ማሳካት ያልተቻለው በሁለቱ ወራት የሱዳን የኤሌክትሪክ ኩባንያ ኃይል የመግዛት ፍላጎቱ በመቀነሱ እንደሆነ አቶ ምኒሊክ አስታውቀዋል፡፡

በሁለቱ ወራት ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት በማድረግ ከተገኘው ገቢ በተጨማሪ ከሀገር ውስጥ የኃይል ሽያጭና ከፋይበር ኦፕቲክስ ኪራይ ከ2 ነጥብ 74 ቢሊዮን ብር በላይ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ ያመለክታል።
Via (ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version